ፈልግ

በሰሜን አሜሪካ የተካሄደ የ “SEEK 2026” ጉባኤ በሰሜን አሜሪካ የተካሄደ የ “SEEK 2026” ጉባኤ  

በሰሜን አሜሪካ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የወጣቶቿን ጠንካራ ድምጽ አሰማች

ከ26,000 በላይ የአሜሪካ ወጣት ካቶሊካውያን የተሳተፉበት “SEEK 2026” የተባለው ጉባኤ በሦስት የአሜሪካ ከተሞች ተካሂዷል። በርካታ የአሜሪካ ወጣቶች የተሳተፉበት የኮሎምበስ ኦሃዮ ጉባኤ ወጣቶች የጊዜያቸውን ተግዳሮቶች ለመቋቋም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡበት ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለጉባኤው ተካፋዮች መልዕክታቸውን ልከዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሦስት የአሜሪካ ከተሞች እነርሱም በኮሎምበስ፣ በዴንቨር እና ፎርት ዎርዝ እና በቴክሳስ ከታኅሳስ 23-27/2018 ዓ. ም. በተመሳሳይ ጊዜ የተካሄደው የ “SEEK 2026” ጉባኤ ላይ ከ26,000 በላይ ወጣቶችን የሳበ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት በ24 በመቶ መጨመሩ እና በኮሎምበስ ብቻ ከ16,000 በላይ ወጣቶዎችን በማስተናገድ ከተማዋን የጉባኤው ዋና ማዕከል ማድረጉ ተነግሯል።

ጉባኤው በዋናነት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እና ወጣት ጎልማሶችን ያካተተ ሲሆን እንዲሁም ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የምዕመናን መሪዎች እና ጳጳሳት ተሳትፈዋል። በተለይም ከመላው የአሜሪካ ግዛቶች የተውጣጡ 58 ጳጳሳት የተሳተፉ ሲሆን ጉባኤውን የተካፈሉ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ቁጥር 43 በመቶ ጨመሩ ታውቋል።

የ “SEEK 2026” ጉባኤ
የ “SEEK 2026” ጉባኤ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት

በ “SEEK 2026” ላይ የተነበበው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክት የጉባኤ ዋና አካል ሆኖ የቀረበ ሲሆን ጭብጡም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት ማድረግ መሆኑን አስረድቷል። ቅዱስነታቸው  ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙት ሆነ ቋሚ ግንኙነት ያላቸው ወጣቶች ጊዜያቸውን ከእርሱ ጋር እንዲያሳልፉ በመልዕክታቸው ላይ አሳስበዋል።

በአሜሪካ የኮሎምበስ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ኤርል ፈርናንዴዝ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክት ለጉባኤው ተልዕኮ ባለው ማዕከላዊ አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል።

“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ምስል በትልቅ ‘ስክሪን’ ላይ ሲታይ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ጉጉት ፈጥሯል” ያሉት አቡነ ኤርል፥ ቅዱስነታቸው ለአንድ ደቂቃ ብቻ ሳይሆን ለአምስት ደቂያ ያህል መናገራቸውን ገልጸዋል። “በርካታ የ ‘SEEK 2026’ ጉባኤ አዘጋጆች እና የ ‘FOCUስ’ ማኅበረሰብ አባላት ቅዱስነታቸው የ ‘SEEK’ ጉባኤን ትርጉም ከራሳቸው በተሻለ ሁኔታ ጠቅለል አድርገው እንዳቀረቡ ነግረውኛል” ያሉት አቡነ ኤርል፥ ይህም በብዙ ወጣቶች ልብ ውስጥ ዘር ዘርቶ በጥሪያቸው እንዲያሰላስሉ እና ኢየሱስ ለእንድርያስ እና ለሚወደው  ደቀ መዝሙር፥ ‘ምን ትፈልጋላችሁ?’ ብሎ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ መርዳቱን አስታውሰዋል።

አቡነ ኤርል ፈርናንዴዝ የ “SEEK 2026” ጉባኤ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ስለምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ያለውን የተዛባ አመለካከት እንደሚቀይር አፅንዖት ሰጥተው፥ በ ‘SEEK 2026’  ላይ የታየው አበረታች ምልክት የቤተ ክርስቲያኗን ወጣትነት እና ጉልበት በግልጽ እንደሚያሳይ እና ወጣቶች የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ዋና ማዕከል እንደሆኑ የጉባኤው መልዕክት ማስረዳቱን ተናግረዋል።

የኮሎምበስ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ኤርል ፈርናንዴዝ ለጉባኤው ተካፋዮች የቀረበውን መስዋዕተ ሲያሳርጉ
የኮሎምበስ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ኤርል ፈርናንዴዝ ለጉባኤው ተካፋዮች የቀረበውን መስዋዕተ ሲያሳርጉ

የወጣቶች ድምፅ

ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል በሚቺጋን ሂልስዴል ኮሌጅ ተማሪ እና በጄምስታውን ኮሎራዶ ካምፕ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ማዕከል በጎ ፈቃደኛ ሜሪ ብሬኮውንት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር በነበራት ቆይታ ለዝግጅቱ የመንፈሳዊነት ገጽታ አፅንዖት በመስጠት እንደተናገረችው፥

“ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶች በውስጣቸው ጥልቅ ረሃብ እንዳላቸው፣ የህልውናቸውን ዓላማ እና የአምላካቸውን ልብ ለማወቅ እንደሚናፍቁ እና በእውነት ሊያረካቸው የሚችል ነገር በኅብረት የሚሹ 17,000 ተማሪዎችን መሰብሰቡ አስደናቂ ተሞክሮ ነው” በማለት ከገለጸች በኋላ የ “SEEK 2026” ጉባኤ ወጣቶች ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተላቸው ብቻቸውን እንዳልሆኑ ነገር ግን ሕያው፣ ታማኝ እና ቁርጠኛ የምዕመናን ማኅበረሰብ አካል መሆናቸውን ማስገንዘቡን አስረድታለች።

ወጣት ሜሪ ብሬኮውንት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክት ላይ በማሰላሰል እንደተናገረችው፥ መልዕክታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት የሚያስታውስ አባታዊ ምክር እንደሆነ ገልጻ፥ “እኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳንሆን ሕያው እና ንቁ ልቧ ነን” በማለት ይህም አሁን እየታየ ያለ ነው” ስትል ተናግራለች።

በኮሎምበስ ሀገረ ስብከት የ “SEEK 2026” ጉባኤ የተካሄደበት ሥፍራ
በኮሎምበስ ሀገረ ስብከት የ “SEEK 2026” ጉባኤ የተካሄደበት ሥፍራ

ቀጣይነት ያለው ማኅበረሰብ

“FOCUS” ተብሎ በሚታወቅ ማኅበረሰብ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የ “SEEK 2026” ጉባኤ፥ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን፣ የአምልኮ እና የስግደት ሥነ-ሥርዓቶችን፣ ኑዛዜን እና በጥሪ ግንዛቤ ላይ የተደረጉ የውይይት ጊዜዎችን ያካተተ እንደ ነበር ተነግሯል።

የጉባኤው አዘጋጆች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2027 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደው የ “SEEK” ጉባኤ በኮሎምበስ እና በተመሳሳይ ጊዜም በሳን አንቶኒዮ እና ቴክሳስ ውስጥ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

 

08 Jan 2026, 13:34