ፈልግ

በቤተልሔም የሚገኘው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ስፍራ በቤተልሔም የሚገኘው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ስፍራ  

በቤተልሔም የሚገኘው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቦታ እንደገና መታደስ 'የተስፋ እና የአንድነት ምልክት' መሆኑ ተነገረ

በኢየሩሳሌም የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ እና የቅድስት ሀገር ጥበቃ ጽህፈት ቤት በጋራ ባወጡት መግለጫ የክርስትና ሃይማኖት ምንጭ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን በቤተልሔም የሚገኘውን ስፍራ መልሶ የማቋቋም ሥራዎች መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

‘ግሮቶ ኦፍ ናቲቪቲ’ ተብሎ የሚታወቀው ይህ በቤተልሔም ውስጥ የሚገኘውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የውልደት ስፍራን እንደገና ለማደስ እየተደረገ ያለው ጥረት በ 600 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይሄንንም እንቅስቃሴ ለማሳካት ሁሉም ነገር ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል።

ይህንን ያስታወቁት የኢየሩሳሌም የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሀገር ጥበቃ ጽህፈት ቤት በጋራ ባወጡት መግለጫ ሲሆን፥ ሁለቱ አካላት በመግለጫቸው የአርመኒያው ሐዋርያዊ የኦርቶዶክስ መንበረ ፓትርያርክን ትብብር ባካተተው እና በፍልስጤም መንግሥት ፕረዚዳንታዊ ጽህፈት ቤት ድጋፍ እየተካሄደ ባለው ተነሳሽነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ሮምን በጎበኙበት ወቅት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ባደረጉት ውይይት እና “የቤተልሔም ዳግመኛ ውልደት” የተሰኘው ኤግዚቢሽን ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ወቅት ባደረጉት ንግግር የተሀድሶ ሥራዎች እንደሚካሄዱ ጠቅሰው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ፕረዚዳንቱ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቦታ መታደስ “ለመላው ቅድስት ምድር ታላቅ ተስፋና ዳግም የመወለድ ምልክት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ በመሆኑም ምክንያት ቀድሞውኑ ቦታውን መልሶ የማደስ ሥራዎችን አስመልክቶ በ 2016 ዓ.ም. የወጣውን ፕሬዝዳንታዊ ድንጋጌ እና በክርስትና ሃይማኖቶች በሙሉ የሚከበረውን ‘የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የውልደት ስፍራ ‘ግሮቶ’ን ጨምሮ ቅዱሳን ቦታዎች የሚተዳደሩበት ነባራዊ ሁኔታን በማክበር ይህ ስፍራ በመጨረሻም የሚፈልገውን እንክብካቤ እንደሚያገኝ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ ለጣሊያኑ ኩባንያ በአደራ ተሰጥቷል
ሥራዎቹ የሚከናወኑት ፕራቶ ከተማ በሚገኘው የጣሊያን ኩባንያ ሲሆን፥ ይህ ተቋም ከሁለት ዓመት በፊት ግዙፍ እና ጥንቃቄ በተሞላበት የእድሳት ፕሮጀክት የናቲቪቲ ባዚሊካን ማደሱ ተነግሯል።

እድሳቱን የሚያከናውነው ተቋምን የመምረጥ ሥራ የተመሰረተው የሂደቱን ቀጣይነት የማረጋገጥ አስፈላጊነት፣ የእጅ ጥበብ እና ለተቀደሱ ቦታዎች በሚሰጡ ጥበባዊ እሴቶች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፥ የቅድስት ሃገር ጥበቃ ጽህፈት ቤት ድህረ-ገጽ እንደገለጸው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን እና ሥራዎቹ አሁን እንደሚጀመሩ ተገልጿል።

በግሮቶ ውስጥ ከሚሰሩት ሥራዎች በተጨማሪ በባዶ ድንጋያማ ወለሎች፣ የእብነ በረድ ወለሎች፣ ዓምዶች እና ማስጌጫዎች፣ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ትክክለኛ ቦታ የሚያመለክተው ኮከብ፥ ብሎም ፕሮጀክቱ በአቅራቢያው ባሉ ክፍሎች ውስጥ የሚከናወኑ ቴክኒካዊ የማጠናከሪያ እርምጃዎችን እንደሚያካትት የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ ፕሮጄክት ሁለቱንም የቤተ መቅደሱን የሕንፃ አንድነት እና ለሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር የሚያበረክተውን የትብብር መንፈስ ያንፀባርቃል ተብሏል።

የእድሳት ሥራዎቹ በዚህ አስፈላጊ ፕሮጀክት ውስጥ ተቀጥረው ለሚሰሩ በርካታ በዘርፉ የሰለጠኑ የአካባቢው ሰራተኛ ቤተሰቦች ድጋፍ እንደሚያደርጉ እና በዚህም በቤተልሔም ከተማ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል።

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በተፈጠረው ግጭት እና መንፈሳዊ ንግደቶች በመቋረጣቸው ምክንያት የከተማይቱ ኢኮኖሚ ሁኔታ አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፥ ሆኖም ግን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን ‘ክፍል ሁለት’ የሰላም እቅድ ተከትሎ ቀስ በቀስ መሻሻሎችን እያሳየ መምጣቱ ይነገራል።

የአንድነት ምልክት
ይህ ፕሮጄክት የዳግም መወለድ ምልክት ብቻ ሳይሆን፥ በግሪክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች እና የግሮቶ ጠባቂዎች በሆኑት ፍራንቺስካውያን መካከል በነበረው የትብብር መንፈስ የሚታወቀውን ጠንካራ የክርስቲያናዊ አንድነት ተነሳሽነት መሆኑን መግለጫው ያመላከተ ሲሆን፥ “ይህ ፕሮጀክት የቅዱስ ግሮቶ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ እሴትን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም የክርስቲያን እምነት የሚታይበትን እና የሁሉም ሃገራት ምዕመናን በየዘመናቱ መንፈሳዊ ንግደት የሚያደርጉበትን ቦታ ክብር ለማስጠበቅ አንድ ወጥ የሆነ ክርስቲያናዊ ቁርጠኝነትን ያካትታል ተብሏል።

የግሮቶ አከባቢ ምስጢረ ሥጋዌ የተገለጠበት እና ክርስቲያናዊ ኑዛዜ ምድራዊ ጅማሬውን ያገኘበት ሥፍራ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይህንን የተቀደሰ ቦታ ማደስ ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ምድር ያለውን የእምነት፣ የትውስታ እና የታማኝነት እሴት መጠበቅ እንደሆነ መግለጫው አስረድቷል።

በዚህ የጋራ ጥረት የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናት በአደራ የተሰጣቸውን የወንጌል ቅርስ እንደሚጠብቁበት፥ እንዲሁም ከሁሉም ባሕሎች የተውጣጡ ምዕመናን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የትውልድ ቦታ በአክብሮት ማየታቸውን እንዲቀጥሉ ያረጋግጣሉ ያለው መግለጫው፥ በመጨረሻም፥ በቤተልሔም በክርስቶስ ልደት የተገኘው ብርሃን ዓለምን እያበራ እንደሚቀጥል እንዲሁም በቅድስት ምድር ዘላቂ ለሆነ ክርስቲያናዊ መገኘት እና አዳኝ ከተወለደበት ከተቀደሰው ዋሻ ለሚፈነጥቀው ተስፋ ምስክር ነው በማለት አጠቃሏል።

27 Jan 2026, 12:59