የዩናይትድ ስቴትስ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ለሃገሪቷ የጸሎት ጥሪ ማቅረባቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ፖል ኮክሌይ ሰዎች ከልባቸው እንዲቀየሩ እና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ውስጥ መታደስ እንዲኖር የጸሎት ጊዜ እንዲኖራቸው የጠየቁ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ ባደረጉት የጸሎት ግብዣ ላይ በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ኢፍትሃዊ እና ብጥብጥ ውስጥ ምን ያህል ሰዎች አቅም የማጣት ስሜት እንደሚሰማቸው ጠቁመው፥ ታማኝነት፣ ጸሎት፣ የፍቅር ሥራ እና የፍትሕ ሥራ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የትኛውም የምሕረት ተግባር ትንሽ አይደለም
የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት መልዕክት ካቶሊኮች እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች እርስ በርሳቸው ለመተሳሰብ እንዲሁም ሰላም እና ፍትህ እንዲሰፍን ላሳዩት ቁርጠኝነት ያላቸውን አድናቆት ገልፀው፥ እነዚህ ድርጊቶች የተራቡትን በመመገብ፣ እንግዳን በመቀበል፣ የታመሙትን በመንከባከብ መልክ እንደተገለጡ የጠቆሙ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ምንም ያህል ትልቅም ይሁን ትንሽ እያንዳንዱን የምሕረት፣ የፍትህ እና የፍቅር ተግባር እንደሚያይ ሊቀ ጳጳስ ኮክሌይ አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች እንደተከሰቱ እና እየተካሄዱ እንዳሉ ሊቀ ጳጳሱ ያስታወሱ ሲሆን፥ የምሕረት ሥራዎች፣ በሰላማዊ መንገድ መሰብሰብ እና በአካባቢያችን ያሉትን መንከባከብ የተስፋ ምልክቶች እንደሆኑ ጠቁመው፥ ‘ከቁጣ ወይም ተስፋ መቁረጥ ይልቅ እነዚህ ተግባራት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሰላምን ይገነባሉ’ ካሉ በኋላ፥ሆኖም ግን ትክክለኛ ህጎች መከበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የፍትሕ መጓደል ሁኔታዎች
ሊቀ ጳጳስ ኮክሌይ በመቀጠልም የአሜሪካ የስደት እና የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ተቋም (አይስ) በሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ ሲያካህድ በነበረው ዘመቻ የሁለት ሰዎች (ሬኒ ጉድ ታህሳስ 29 እና አሌክስ ፕሪቲ ጥር 16) ሞትን እና በቴክሳስ ስለታሰረው ሰው ጉዳይ አስመልክተው እንደተናገሩት፥ እነዚህ ክስተቶች “በህብረተሰባችን ውስጥ የእያንዳንዱን ሰው ህይወት ክብር ለማክበር አለመሳካቱን የሚያሳዩ አሳዛኝ የጥቃት ምሳሌዎች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።
በሁለቱ ሰዎች ህይወት ማለፍ እጅግ ማዘናቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ ኢፍትሃዊነትን እና ግዴለሽነትን የሚወክለውን ይህንን ድርጊት ያወገዙ ሲሆን፥ በሃገሪቷ ውስጥ አሁን እየታየ ያለውን “የፍርሃት እና የጽንፈኝነት” ሁኔታ የሰው ልጅ ክብር ሲጣስ የሚዳብር እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ያስቀመጠውን መስፈርት የማያሟሉ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ለመታደስ የሚሆን የተቀደሰ ሰዓት
ሊቀ ጳጳስ ኮክሌይ ወደ ፈውስ አንድ እርምጃ ለመራመድ በዩናይትድ ስቴትስ ዙሪያ ያሉት ሁሉም ብፁዓን ጳጳሳት እና ካህናት በመጪዎቹ ቀናት ለሰላም የሚሆን ቅዱስ ሰዓት እንዲያዘጋጁ የጋበዙ ሲሆን፥ በዚህ የተቀደሰ ሰዓት መለያየት ባለበት እርቅ እንዲወርድ፣ መሠረታዊ መብቶቻቸው ለተጣሰባቸው ፍትህ እንዲሰፍን እና በፍርሃት ወይም በኪሳራ ለተጎዱት መፅናናት እንዲሆን እንፀልይ ብለዋል።
ይህ የጸሎት ጥሪ ለሁሉም ካቶሊኮች መሆኑን የጠቀሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ “በቁምስናዎች፣ በጸሎት ቤቶች፣ ወይም በጸጥታ ውስጥ በልባቸው በጌታ ፊት በሚያቀርቡት ጸሎት ለሀገራችን እና ለማህበረሰባችን ፈውስ ያስገኛሉ” ያሉ ሲሆን፥ ይህች ቅድስት ሰዓት “ለልባችን እና ለሃገራችን የመታደስ ጊዜ እንደምትሆን ተስፋ አለኝ” በማለት ገልጸዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ሊቀ ጳጳስ ኮክሌይ በመጨረሻም ሁሉም ሰው ተስፋውን እና ፍርሃቱን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ልብ እንዲሰጥ እንዲሁም “ለእያንዳንዱ ሰው ተፈጥሯዊ ክብር” እያንዳንዱን ሰው የሰላሙ መሳሪያ እና ምስክሮች ያደርግ ዘንድ አምላክን እንዲጠይቅ በማበረታታት መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።
“እግዚአብሔር የሕዝቡን ጩኸት ሰምቶ ወደሚሹት ሁሉ እንዲቀርብ በመተማመን አብረን እንጸልይ”