ፈልግ

በፖላንድ የተካሄደው የቤኔሜሬንቲ ሽልማት ሥነ ሥርዓት በፖላንድ የተካሄደው የቤኔሜሬንቲ ሽልማት ሥነ ሥርዓት 

በፖላንድ የቫቲካን መገናኛ ብዙሃን ሰላምን በማስፈን ረገድ ባደረጉት አስተዋጽዖ እውቅና እንደተሰጣቸው ተነገረ

በፖላንድ የሚገኘው ‘ፖሊሽ ሚሊታሪ ኦርዲናሪዬት’ የተሰኘው ተቋም በፖላንድ የቫቲካን ራዲዮ የፖላንድኛ ቋንቋ ስርጭት ክፍል እና ‘ላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ’ ጋዜጣ የሰላም እሴቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ላበረከቱት አስተዋፅዖ ‘ቤኔሜሬንቲ’ ተብሎ የሚጠራውን ሽልማት ያበረከተ ሲሆን፥ የክብር ሽልማቱ በተጨማሪም የጦር ኃይሎች ኦፕሬሽን ኮማንድ፣ የጦር ኃይሎች ድጋፍ ቁጥጥር እና የአየር ኃይል ኦርኬስትራ ለመሳሰሉ የፖላንድ የጦር ኃይል ክፍሎች መሰጠቱ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

‘ፖሊሽ ሚሊታሪ ኦርዲናሪዬት’ የተሰኘው ተቋም ተጠያቂነቱ ለቅድስት መንበር የሆነ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወታደራዊ አገልግሎት ተቋም ሲሆን፥ በፖላንድ ጦር ኃይሎች ውስጥ ለሚያገለግሉ የሮማ ካቶሊኮች እና ለቤተሰቦቻቸው የሃዋሪያዊ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

የቤኔሜሬንቲ ሽልማት “የሰላም እና የደህንነት እሴቶችን በማስተዋወቅ” ረገድ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የቫቲካን ዜና አካል ለሆነው የቫቲካን ረዲዮ የፖላንድ ቋንቋ ክፍል እና ስለ ቅድስት መንበር እንቅስቃሴ እንዲሁም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በዓለም ላይ እየተከናወኑ ያሉትን ክንውኖችን የሚዘግበው የቫቲካን ከተማ ዕለታዊ ጋዜጣ ለሆነው ‘ላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ’ የተበረከተ ሲሆን፥ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው ጥር 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በዋርሶ በሚገኘው የፖላንድ ጦር ሙዚየም ወታደራዊ አገልግሎት ተቋሙ 35ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ባከበረበት ወቅት እንደነበር ተገልጿል።

ሽልማቱን ያበረከቱት የፖላንድ ወታደራዊ የሃዋሪያዊ አገልግሎት ተቋም ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዊስላው ሌቾዊዝ የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ተወካዮች በመገኘታቸው የተሰማቸውን ልዩ እርካታ ገልጸው፥ ‘ይህ መገናኛ ብዙኃን ሰላም እና ደኅንነትን ለማገልገል እንደቆሙ የሚያሳይ ጥሩ ማረጋገጫ ነው’ ሲሉ ገልጸውታል።

ብፁዕነታቸው አክለውም የቅድስት መንበር የተግባቦት ጽህፈት ቤት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን እና የቤተክርስቲያንን ድምጽ እንደሚወክል እና የሰላም ንጉስ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል ጠቁመው፥ “በብዙ ግጭቶች በሚታወቀው አሁን ባለንበት ዓለም እውነት፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ፍትህ እና መተሳሰብን የመሳሰሉ እሴቶች ሁልጊዜ በማይመሰገኑበት ዓለማችን፥ የቫቲካን መገናኛ ብዙሃን እነዚህን እሴቶች ማስተዋወቅ እና መመስከራቸውን ቀጥለዋል” በማለት ሁሉንም የቫቲካን ጋዜጠኞች አመስግነዋል።

በሰላም አገልግሎት ውስጥ የሚገኝ ግንኙነት
“የእኛ ተልዕኮ የጴጥሮስን ተተኪ ድምፅ ወደ ዓለም ማዕዘናት ማዳረሱን መቀጠል ነው” በማለት በፖላንድ ቋንቋ ንግግር ያደረጉት የቫቲካን ሚዲያ ኤዲቶሪያል ዳይሬክተር አንድሪያ ቶርኔሊ፥ የፖላንድ ቋንቋ አዘጋጅ ቡድን ለመላው የመገናኛ ብዙኃን ሥርዓቶች አርአያ መሆኑን ጠቁመው፥ ታላቁ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካረፉ 21 ዓመታት በኋላ ፖላንድኛ የቫቲካን መገናኛ ብዙሃን ስርጭታቸውን ከጀመሩበት ሰባት ዋና ዋና ቋንቋዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ቶርኔሊ የቫቲካን ሬዲዮ የረዥም ዓመት ታሪክ እንዳለው እና ጄሱሳውያን ለዕድገቱ ያበረከቱትን አስተዋፅዖ ብሎም በአባ ፓዌል ራይተል የሚመራው ቡድን ያከናወኗቸውን ተግባራት በአጽንዖት ገልጸው፥ እውነተኛ መረጃዎችን ማስተላለፍ፣ ግንኙነትን መገንባት እና ኃላፊነት የተሞላበት ግንኙነት የካቶሊክ ሚዲያዎች መሰረታዊ ተግባራት መሆናቸውን አስምረውበታል።

በፖላንድም ሆነ በውጭ አገር ብዙ ታዳሚዎችን በመድረስ የፖላንድ ቋንቋ ክፍል በዚህ ተልዕኮ ውስጥ የተጫወተውን ቁልፍ ሚና አበክረው የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ባለፈው ዓመት ውስጥ ብቻ በቫቲካን ሚዲያ በፖላንድ ቋንቋ የተዘጋጁ ይዘቶች ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ እይታዎችን ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የፖላንድ ቋንቋ አስፈላጊነት
የቫቲካን ሚዲያ ምክትል ኤዲቶሪያል ዳይሬክተር እና የቫቲካን ሬዲዮ እንዲሁም የቫቲካን ዜና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ማሲሚላኖ ሜኒቼቲ የፖላንድ ቋንቋ በቫቲካን ሚዲያ ታሪክ እና በአሁኑ ጊዜ ተልዕኮ ውስጥ ያለውን ልዩ ቦታ በመጥቀስ፥ የፖላንድ ቋንቋ ሁል ጊዜ በቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ማዕከላዊ ሚና እንደሚጫወት እና በጨለማው የግዛት ዘመን እምነትን ጠብቆ ማቆየቱን አስታውሰው፥ ዛሬ በቫቲካን ረዲዮ፣ ቫቲካን ዜና እና በላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ አማካኝነት የወንጌልን ውበት እያወጀ እንደሚገኝ እንዲሁም እያንዳንዱን ዜና በቤተክርስቲያኑ ማህበራዊ አስተምህሮ መነጽር እንደሚተረጎም አብራርተዋል።

ሜኒቼቲ አክለውም በዓመፅ በተሞላው እና ኢፍትሐዊ በሆነው ዓለም ውስጥ የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን “የተስፋ አድማስ” እንደሚሰጡ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ብዙ ጊዜ እንደሚያስታዉሱት ትጥቅ የሚፈታ እና የሚያስፈታ የመገናኛ ዘዴን እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።

ሽልማቱን የኤዲቶሪያል ዳይሬክተር አንድሪያ ቶርኔሊ፣ ምክትላቸው ማሲሚላኖ ሜኒቼቲ እና የፖላንድ ቋንቋ ክፍል ኃላፊ ፓዌል ራይተል በጋራ የተቀበሉ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ዳይሬክተሮች እና የፖላንድ ክፍል ባልደረባዎች ሰላምን ለማስፈን ላደረጉት ቁርጠኝነት ‘ሚሊቶ ፕሮ ክሪስቶ’ የተሰኘ ሜዳሊያ መሸለማቸው ተነግሯል።

እውቅና የተሰጣቸው ሌሎች አካላት
የቤንሜሬንቲ ሽልማቶች ከቫቲካን መገናኛ ብዙሃን በተጨማሪ ለፖላንድ ጦር ሃይሎች ከፍተኛ ጄኔራሎች እና ቁልፍ ተቋማት፣ ለጦር ኃይሎች የዘመቻ ቁጥጥር ክፍል፣ የጦር ኃይሎች ድጋፍ ምርመራ ክፍል እና ለአየር ኃይል ኦርኬስትራ መበርከታቸው ተገልጿል።

በፖላንድ የሚገኘው ይህ ተቋም እ.አ.አ. በ 1919 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን፥ በተለይም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ትልቅ ሚና መጫወቱ ይገለፃል።

በኮሚኒስታዊ ሥርዓት ዘመን የክልል ባለስልጣናት ለወታደሮች ሲሰጥ የነበረውን ሃዋሪያዊ አገልግሎት ማገዳቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ከሠላሳ አምስት ዓመታት በፊት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አገልግሎቱን ዳግመኛ ማስጀመራቸው እና በአሁኑ ወቅት ከ 130 የሚበልጡ ወታደራዊ ካህናት በተቋሙ ውስጥ እያገለገሉ እንደሚገኝ ተገልጿል።

23 Jan 2026, 13:17