በግሪንላንድ አንድ የኑክ ሃገረ ስብከት ካህን 'ሃገራችን አትሸጥም’ ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሃያ ሺህ ነዋሪዎች ያሏት የግሪንላንድ ዋና ከተማ የሆነችው የኑክ በረዶአማ አውራ ጎዳናዎች በጸጥታ የተሞሉ ሲሆን፥ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአርክቲክ ውቅያኖስ የሚገኘውን እና በዓለማችን ትልቁን የግሪንላንድ ደሴት 'ለመጠቅለል' ፍላጎት እንዳላቸው ማሳየታቸው ይታወቃል።
ይሄንን ተከትሎ ሃገሪቷ አሁን ያለችበትን ሁኔታ አስመልክተው ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ ያደረጉት አባ ቶማስ “የግሪንላንድን የወደፊት እጣ ፈንታ እራሳች መምረጥ እንፈልጋለን” ያሉ ሲሆን፥ ካህኑ ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል በግሪንላንድ፣ ኑክ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ብቸኛው የላቲን ካቶሊክ ደብር በሆነው ‘የንጉሱ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን’ ውስጥ ማገልገላቸውን ተናግረዋል።
የራሱ ታሪክ እና ባህል ያለው ህዝብ
56,000 ነዋሪዎች ያሏት ደሴትቷ በአሁኑ ወቅት ከምትገኝበት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንፃር እና ባሏት ማዕድኖች ምክንያት የዓለም ጂኦፖለቲካዊ የውድድር ማዕከል መሆኗ እየተነገረ ይገኛል።
አባ ቶማስ ማጅሴን በአሁኑ ወቅት በኑክ ያለው ድባብ ጸጥታ የተሞላበት መሆኑን አመላክተው፥ ነገር ግን ከተማዋ ውጥረት ውስጥ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
በጎረጎሳዊያኑ 2023 ዓ.ም. የበጋ ወቅት የኮፐንሃገን ጳጳስ በአርክቲክ ደሴት የሚገኘውን የካቶሊክ ማህበረሰብ በሃዋሪያዊ ሥራ እንዲያገለግሉ ያደረጉላቸውን ጥሪ ከተቀበሉ በኋላ ህዝቡን በሚገባ ማወቃቸውን የገለጹት ካህኑ፥ የግሪንላንድ ነዋሪዎች በጸጥታ የተሞሉ ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ህዝቡ ከመናገሩ በፊት በትኩረት እንደሚመለከት፣ እንደሚያዳምጥ እና እንደሚያስብ የተናገሩት ካህኑ፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሱቆች እና በቡና ቤቶች አከባቢ ስለ ፖለቲካ ማውራት በብዛት እየተለመደ መምጣቱን አስታውሰዋል።
ስሎቫኒያዊው ካህን የውጭ አገር ፖለቲከኞች ስለ ግሪንላንድ ‘ከስልጣን ወይም ከሃብት’ ጋር አገናኝተው ሲናገሩ በርካታ የሃገሪቱ ዜጎች ከመናደድም አልፈው ልባቸው እንደሚሰበር አስረድተው፥ ይህም በሃገራቸው ላይ ያላቸውን ኩራት እንደሚነካ እና ህዝቡ የራሱ የሆነ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል እና እምነት ያለው ሆኖ መታየት እንደሚፈልግ የገለጹ ሲሆን፥ ምንም ፍርሃት ባይኖራቸውም፥ ነገር ግን ህዝቡ ከሩቅ የሚሰሙ አንዳንድ ጠንካራ ድምፆች ስለ ግሪንላንድ በትክክል ሳይረዱ የሚነገሩ መሆኑን ያውቃል ካሉ በኋላ፥ ‘ይህ ደግሞ ሁለቱንም የደካማነት እና የአንድነት ስሜት ያመጣል’ ብለዋል።
በቁጥር አነስተኛ፥ ነገር ግን ንቁ የካቶሊክ ማህበረሰብ
ይህ የአንድነት ስሜት በእምነት ማህበረሰቡ ዘንድ የበለጸገ እና ሥር የሰደደ መሆኑን የገለጹት ካህኑ፥ 90 በመቶው የግሪንላንድ ነዋሪዎች በሕዝብ ታሪክ እና ማንነት ውስጥ ረጅም ታሪክ ባላት የወንጌላዊት ሉተራን ቤተክርስቲያን ተከታዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የካቶሊኮች ቁጥር በጣም ጥቂት መሆኑን የገለጹት አባ ቶማስ፥ በኑክ ከተማ ወደ 500 የሚጠጉ ካቶሊኮች የሚገኙ መሆኑን ጠቁመው፥ በመላው ግሪንላንድ ደግሞ 800 የሚያህሉ ከተለያዩ ብሔራት፣ ቋንቋዎችና አስተዳደግ የተውጣጡ ካቶሊኮች እንደሚገኙ እና በርካቶቹ ከፊሊፒንስ እና ከአውሮፓ እንደመጡ ገልጸው፥ “ደብራችን ትንሽ ቢሆንም ነገር ግን በጣም ጠንካራ ነው” በማለት አስረድተዋል።
በግሪንላንድ ያለችው የካቶሊክ ቤተክርስትያን ምንም እንኳን በቁጥር ትንሽ የሆነ ምዕመን ያላት ብትሆንም ‘መሬት መቼም ቢሆን መሬት ብቻ እንዳልሆነ’ በማሳሰብ ረገድ ትልቅ ሚና እንደምትጫወት የገለጹት ካህኑ፥ መሬት ሁልጊዜ ከሰዎች፣ ትዝታዎች፣ ቅድመ አያቶች እና የወደፊት ትውልዶች ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረድተዋል።
አባ ቶማስ አክለውም ዘወትር እሁድ ለዴንማርክ መንግሥት እና ለግሪንላንድ የራስ ገዝ አስተዳደር በሉተራን አብያተ ክርስቲያናት የተለያዩ ጸሎቶች እንደሚደረጉ ጠቁመው፥ በግሪንላንድ የወንጌላዊት ሉተራን ቤተክርስቲያን ጳጳስ በሆኑት ፓኔራክ ሲግስ-ታድ ሙንክ የተጀመረው ይህ የጸሎት ተነሳሽነት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ የጂኦፖለቲካዊ አውድ ውስጥም እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አብያተ ክርስቲያናት በጸጥታ የተሞሉ ነገር ግን እጅግ ጠቃሚ የሆኑትን ጸሎት፣ መገኘት፣ ማዳመጥ እና ሥነ ምግባራዊ መሠረቶችን እያቀረቡ እንደሚገኝ የገለጹት ካህኑ፥ “ፍጥረት የእግዚአብሔር ስጦታ እና የሰው ልጅ ክብር እንደሆነ ስናወራ፥ በሌላ መንገድ የግሪንላንድን ሉዓላዊነት የሚገልጽ በጣም ጠንካራ ነገር እየተናገርን መሆኑ ግልጽ ነው” ሲሉ አስረድተው፥ ግሪንላንድ ለዓለም አቀፍ ፍላጎቶች የመጫወቻ ሜዳ መሆን ዬለባትም ብለዋል።
የክብር ጥያቄ
አባ ቶማስ ወቅታዊ ክስተቶች የግሪንላንድ ነዋሪዎችን የነፃነት ፍላጎት ሊያጠናክሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፥ ሰዎች ነፃነት ህልም ብቻ ሳይሆን ትልቅ ሃላፊነትም ጭምር መሆኑን እንደሚረዱ የገለጹ ሲሆን፥ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ ትምህርት፣ ጤና እና የመሳሰሉት መሰረታዊ ነገሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጣም ግልፅ የሆነው ነገር በማንኛውም ሁኔታ የግሪንላንድ ነዋሪዎች የራሳቸውን ነፃነት ለሌላው አሳልፈው መስጠት እንደማይፈልጉ የጠቆሙት ካህኑ፥ “በሌላ ኃይል መገዛት ወይም መመራት የሚለው ሐሳብ በሰፊው ውድቅ ነው” ካሉ በኋላ ለበርካቶች ነፃነት ማለት የክብር፣ የባህል ህልውና እና ለራስ ክብር የመስጠት ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል።
አባ ቶማስ ማጅሰን ጥቂት የአውሮፓ እና የኔቶ ወታደራዊ ቡድኖች ወደ አከባቢው የመሄዳቸውን ጉዳይ አንስተው፥ ማንኛውም ወታደራዊ መገኘት ጥያቄዎችን ሊያስነሳ እንደሚችል፥ ነገር ግን ይህ በአጠቃላይ ከአላስፈላጊ የውጭ ፍላጎት በተለየ መልኩ እንደሚታይ የገለጹ ሲሆን፥ አብዛኛው ሰው ይሄንን ሁኔታ በትብብር ማዕቀፍ በአርክቲክ ክልል ውስጥ ደህንነትን ለማስጠበቅ የተደረገ እርምጃ አድርጎ እንደሚረዳ ጠቁመው፥ ለወታደራዊ ድጋፍ ምንም ዓይነት ጉጉት እንደሌለ፥ ነገር ግን አርክቲክ ስልታዊ ጠቀሜታ እንዳለው ግንዛቤው መኖሩን አብራርተዋል።
በበረዶአማ ክልሎች መካከል ሰላም
ይህ ሁሉ ነገር ወደ አየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች መመለሱ የማይቀር እንደሆነ የጠቆሙት ካህኑ፥ ይህ ንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን ወደፊት በግልጽ የሚታይ ነገር መሆኑን አመላክተው፥ የበረዶው መዋቅሮች እየተቀየሩ መምጣታቸውን እና ወቅቶች እየተለዋወጡ መሄዳቸውን፥ ተመራማሪዎችም ተፈጥሮ በቀድሞ ባህሪዋ እንደማትቀጥል መናገራቸውን አስታውሰዋል።
አባ ቶማስ በበረዶው መካከል ያለው ሕይወት ከመጠን በላይ የሆነውን ነገር እንደሚያስወግድ ጠቁመው፥ “ብዙ ጊዜ ይህች ምድር ራሷ ጸሎትን እንደምታስተምር ይሰማኛል” ያሉ ሲሆን፥ ዝምታው፣ ግዙፍነቱ እና ተጎጂነቱ ትህትናን እንደሚጋብዝ አስታውሰው፥ ለተፈጥሮ፣ ለአገሬው ተወላጆች እውቀት እና ለመጪው ትውልዶች አክብሮት በመስጠት የግሪንላንድ አካባቢን መጠበቅ አሁን መጀመር እንዳለበት አሳስበዋል።
‘ፍጥረት ልንጠቀምበት ብቻ ሳይሆን ልንንከባከበውም ጭምር ይገባል’ የሚለውን ሃሳብ መልሰን ማግኘት አለብን ያሉት ካህኑ በመጨረሻም በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው የሚወሰኑ ውሳኔዎች የተሰሉ፣ መጪውን ጊዜ ያገናዘቡ እና በረጅም ጊዜ ኃላፊነት ላይ የተመሰረቱ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፥ “ምክንያቱም ይህ መሬት አንዴ ከተጎዳ በቀላሉ መመለስ አይቻልም” በማለት አጠቃለዋል።