ፈልግ

በከባዱ የባቡር አደጋ የተጎዱ ሰዎች በአዳሙዝ ከተማ በሚገኘው ኬሴታ ማዘጋጃ ቤት ተዛውረው ሲታከሙ በከባዱ የባቡር አደጋ የተጎዱ ሰዎች በአዳሙዝ ከተማ በሚገኘው ኬሴታ ማዘጋጃ ቤት ተዛውረው ሲታከሙ  

በስፔን የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁምስና በሃገሪቷ የደረሰው የባቡር አደጋ ተጎጂዎችን መርዳታቸው ተነገረ

በደቡባዊ ስፔን ኮርዶባ አካባቢ በደረሰ አስከፊ የሁለት ፈጣን ባቡሮች ግጭት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከአርባ በላይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ግጭቱ የደረሰው አንደኛው ባቡር ከሀዲድ ወጥቶ ተቃራኒ አቅጣጫ ከሚመጣ ሌላ ባቡር ጋር በመጋጨቱ እንደሆነ እና ስፔን ለተጎጂዎች መታሰቢያ የሚሆን የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ማወጇ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ይሄንን ተከትሎ በኮርዶባ ግዛት ሥር ያለችው አዳሙዝ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ አንድሬስ ቁምስና ካህን የሆኑት አባ ራፋኤል ፕራዶስ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት በባቡር አደጋው የተጎዱትን ሰዎች ለማገዝ ቁምስናቸው የሰሯቸውን ሥራዎች አብራርተዋል።

በደቡባዊ ስፔን በምትገኘው አዳሙዝ ከተማ በደረሰው ከባድ የባቡር አደጋ ምክንያት የቅዱስ አንድሬስ ቁምስና ከአደጋው ለተረፉት እና ቤተሰቦቻቸው መጠሊያ መሆኑን እና የቁምስናው በሮች አሁንም ድረስ ለድጋፍ ክፍት መሆናቸውን አባ ራፋኤል ፕራዶስ ገልጸዋል።

በአዳሙዝ ክልል፣ ኮርዶባ ከተማ አደጋው ከደረሰ ከሁለት ቀናት በኋላ የአደጋ ጊዜ ቡድኖች የማዳን እና ተጎጂዎችን የመለየት ሥራቸውን የቀጠሉ ሲሆን፥ የአከባቢው ባለስልጣናት 41 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠው፥ 43 ሰዎች ደግሞ አለመገኘታቸውን፣ 39 ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸውን እና ከእነዚህም ውስጥ 13ቱ በፅኑ ክትትል ውስጥ እንደሚገኙ ሪፖርቶች እንደደረሷቸው ገልጸዋል።

ሰኞ ዕለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለተጎጂዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ሀዘናቸውን መግለፃቸው ይታወሳል።

ከቫቲካን ዜና ቆይታ የነበራቸው አባ ፕራዶስ እንዳሉት የአደጋው መጠን ግልጽ በሆነበት ጊዜ ሰበካው የተጎዱትን ለመርዳት መንቀሳቀስ መጀመሩን ገልጸው፥ ከደብሩ ሰራተኞች እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን የተረፉትን ለመቀበል የደብሩን አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ክፍት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

“ስለአደጋው እንደሰማን ወዲያው የተረፉት ተሳፋሪዎች ወደዚህ እንደሚመጡ እናውቅ ነበር” ያሉት ካህኑ፥ የአከባቢው ነዋሪዎች በአስቸኳይ ውሃ፣ ምግብ እና ፍራሽ እንኳን ሳይቀር ይዘው መምጣት እንደጀመሩ ገልጸው፥ “አንዳንድ ሰዎች ወደ ቁምስናው የመጡትን ሰዎች ለመመገብ ሲሉ የራሳቸውን ማቀዝቀዣዎች ባዶ አድርገዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

በህመም ጊዜ የተገኘ ማስታገሻ
አባ ፕራዶስ እንዳብራሩት ሰበካው የህክምና አገልግሎት የማይፈልጉ ተሳፋሪዎችንም ጭምር መቀበሉን ገልጸው፥ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ተጎጂዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ወይም በተንቀሳቃሽ የህክምና መስጫ መታከማቸውን፣ ሌሎች ደግሞ ምግብ፣ ውሃ፣ ትኩስ ቡና እና ማረፊያ ቦታ እንደተሰጣቸው አብራርተዋል።

ጥር 11 አባ ፕራዶስ እና የኮርዶባ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጄሱስ ፈርናንዴዝ ጎንዛሌዝ ለተጎዱ ቤተሰቦች አጋርነታቸውን ለመግለጽ አዳሙዝን መጎብኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው አዲስ ዜና ከሚጠባበቁ የተጎጂ ዘመዶች ጋር ተገናኝተው ማጽናናታቸው እና የተጎጂዎቹ ቤተሰቦች ከጊዜ በኋላ አስከሬኖች በሚለዩበት ሬይና ሶፊያ የተሰኘው ሆስፒታል ወደሚገኝበት ኮርዶባ መዛወራቸው ተገልጿል።

“በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ፣ በተለያዩ ሁኔታዎች ቤተክርስቲያኒቷ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጠማቸውን ሰዎች በተቻለ መጠን ለመርዳት እና ለማጽናናት እየሞከረች ነው” ሲሉ አባ ፕራዶስ ተናግረዋል።

ማስታወሻ
የሰበካው ካህን በመጨረሻም ለተጎጂ ቤተሰቦች የሚያደርጉትን ቀጣይነት ያለው ጸሎት፣ መቀራረብ እና ተግባራዊ ድጋፍን በማረጋገጥ የተስፋ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ የሁሉም ተጎጂዎች ልየታ ከተጠናቀቀ በኋላ ሰበካው ለሟቾች ዘላለማዊ ዕረፍት መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚደረግ ገልጸው፥ “የምንጸልይላቸውን ሰዎች በሙሉ ስም ዝርዝራቸው ሲደርሰን፣ ነፍሳቸውን አምላክ እንዲቀበል መስዋዕተ ቅዳሴ እናዘጋጃለን” በማለት አጠቃለዋል።

21 Jan 2026, 15:04