ፈልግ

በማይናማር የቅዱስ ካርሎ አኩቲስ ሃውልት ተሰርቶ ተተክሏል በማይናማር የቅዱስ ካርሎ አኩቲስ ሃውልት ተሰርቶ ተተክሏል  

በማይናማር የቅዱስ ካርሎ አኩቲስ ሐውልት የተስፋ ምልክት ሆኖ መሰራቱ ተነገረ

በማይናማር የቅዱስ ካርሎ አኩቲስ ሐውልት የተመረቀ ሲሆን፥ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ አንድ የሀገረ ስብከቱ ካህን እንደተናገሩት የቅዱሱ ህይወት ወጣቶች እምነታቸውን እንዴት መምራት እንደሚችሉ የሚያሳይ ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰው፥ በመከራ ጊዜም ቢሆን በተለይም ሃገሪቱ ባለችበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ወጣቶቹ የእርሱን አርአያ መከተል እንደሚገባቸው መክረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የጣሊያናዊው የቅዱስ ካርሎ አኩቲስ ሃውልት የካቺን ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በሚትኪና ሀገረ ስብከት በቅዱስ ኮሎምባነስ ካቴድራል ውስጥ ተሰርቶ መቀመጡ የተነገረ ሲሆን፥ ማይናማር በአስቸጋሪ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት፥ በሃገሪቱ የሚገኘው አጥቢያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዚያ ለሚኖሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ሃውልቱን እንደ ተስፋ እና የብርሃን ምልክት አድርጎ ማቅረቡ ተገልጿል።

በጦር ሜዳ መካከል ያለ ምስክር
የቫቲካን የዜና ወኪል የሆነው ፊደስ ኒውስ እንደዘገበው ይህ የምረቃ በዓል በማይናማር በዓይነቱ የመጀመሪያ ሲሆን፥ ይህ ሥነ ስርዓት የተካሄደውም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጆን ላ ሳም በክህነት ማዕረግ ከተቀቡ አስረኛ ዓመት እና በጵጵስና ከተሾሙ ደግሞ 1ኛ ዓመታቸውን በሚያከብሩበት ወቅት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

ከሀገረ ስብከቱ ካህናት አንዱ የሆኑት አባ ጆን አንግ ህቶይ ከዚህ ታሪካዊ ወቅት ጀርባ ያለውን ምክንያት ሲያብራሩ፥ ሐውልቱ የተሰራበት ዓላማ ቅዱስ ካርሎ አኩቲስ ወጣቶችን በመከራ ጊዜም ቢሆን፣ በተለይም አገሪቱ አሁን ባለችበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በሕይወታቸው ውስጥ ያለውን እምነት እንዴት መመሥከር እንደሚችሉ ለማስተማርና ለማስታወስ ታስቦ እንደሆነ አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሃውልቱ የተሰራው የሃገሪቱ ወጣቶች በይነ መረብን እና ማህበራዊ ድህረ-ገፆችን በአግባቡ በመጠቀም እምነታቸውን እንዴት እንደሚኖሩ ለማስታወስ እና ለማነሳሳት ታስቦ እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

አባ ህቶይ ቅዱስ ካርሎ የአውታረ መረብ ተጠቃሚ እንደነበር በማስታወስ፥ ቅዱሱ በእርስ በርስ ጦርነት በተከፋፈለችው ሃገር ውስጥ ለሚገኙ እና ከዚህ ቀውስ መትረፍ ለሚገባቸው የአገሪቱ ወጣቶች ምሳሌ እንደሆነ ገልጸዋል።

ካህኑ በተጨማሪም ወጣቶቹ እንደ ጥቃት፣ ወንጀል፣ አደገኛ ዕፆች፣ የቤተሰብ መበተን እና ማኅበራዊ ሚዲያን ያለ ሕግ ከለላ መጠቀምን የመሳሰሉ “ማኅበራዊና ሥነ ምግባራዊ ሥጋቶች” እንደሚገጥሟቸው ተናግረዋል።

እነዚህ ወጣቶች ሕይወታቸውን በክርስቶስ ላይ እንዲመሠርቱ ወደሚያበረታታቸው ወደ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና ጽኑ መሠረት ወዳለው አስተምህሮቶቿ ፊታቸውን ያዞሩት በዚህ አውድ ውስጥ እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

አባ ህቶይ እንደተናገሩት ወጣቶቹን ለመርዳት እና በጉዟቸው ለማጀብ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሃገረ ስብከቶች የወጣት ካምፖችን፣ የእምነት ምስረታ ፕሮግራሞችን እና የትምህርት ፕሮግራሞችን እንደሚያዘጋጁ ገልጸዋል።

“የጠፋ ትውልድ” የመሆን ስጋት
“በአሁኑ ጊዜ በማይናማር የሚገኙ ወጣቶች ድጋፍ፣ መመሪያ እና እምነት ያስፈልጋቸዋል” ያሉት የሀገረ ስብከቱ ካህን፥ በሌላ በኩል ለድርጊታቸውም ሀላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው እና ወጣቶች ለወደፊቱ ወሳኝ ግብአት ስለሆኑ እነርሱን መንከባከብ እንደሚገባ በአጽንዖት ገልጸዋል።

በመላው ማይናማር በተለይ ግጭቱ እና ሁከቱ ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ወጣቶች በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጡ የህዝቡ አካል መሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን፥ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ቤት የሌላቸው፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ወይም ቤተሰብ የሌላቸው ሲሆኑ ይህም “የጠፋ ትውልድ” የመሆን አደጋ ላይ እንደጣላቸው ተነግሯል።

እነዚህን ተግዳሮቶች ለመከላከል በሚል መንፈስ እ.አ.አ. በ 2014 በመንደሌይ ሃገረ ስብከት ውስጥ የተመሰረተው “ዶን ቦስኮ” የወጣቶች ማዕከል ከአስቸጋሪ የአስተዳደግ ሁኔታ ውስጥ ለመጡ እና ወላጅ አልባ ወይም በጎዳና ላይ ለነበሩ 60 የሚያህሉ ወጣቶች መጠሊያ የሆነ ሲሆን፥ በማዕከሉ ውስጥ ወጣቶቹ በሳሌዢያን ሚስዮናውያን አማካይነት እንክብካቤ፣ መኝታ፣ ምግብ፣ ትምህርት እና የጤና አገልግሎት፥ እንዲሁም ስፖርት፣ ሙዚቃ እና የባህል እንቅስቃሴ አገልግሎቶችን እንደሚያገኙ ተገልጿል።

አባ ህቶይ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት የሳሌዢያን ካህናት ተልዕኮ በወጣቶቹ እድገት ወቅት በደህንነት፣ በክብር እና በተስፋ ማገዝ እና አብሮ ለመጓዝ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአመለካከት ለውጥ
እ.አ.አ. በ 2021 ዓ.ም. የማይናማር ጦር ለአስር ዓመታት ያክል በመገንባት ላይ የነበረውን ደካማ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ያፈረሰውን መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ የሀገሪቱን መሪ ኡንግ ሳን ሱ ኪን በቁጥጥር ስር ማዋሉ የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሃገሪቷ በታሪኳ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ መግባቷ ይነገራል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ ታጣቂ ተቃዋሚዎች ከመቀላቀላቸው በፊት ዲሞክራሲ ወደነበረበት እንዲመለስ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፥ ከሦስት ዓመታት በኋላ ወታደራዊው ጁንታ 60,000 የሚያህሉ ወጣቶችን በማስገደድ ወደ ጦር ግንባር እንዲሄዱ የውትድርና ምዝገባ ሕጉን ተግባራዊ በማድረጉ፥ በዚህም ምክንያት ወደ 100,000 የሚጠጉ ወጣቶች በተለይም ወደ ታይላንድ መሰደዳቸው ይገለፃል።

ከማይናማር አጠቃላይ የህዝብ ብዛት 33 በመቶ የሚሆኑት ከ15 እስከ 35 ዓመት የሚሆናቸው ወጣቶች መሆናቸው የሚገለጽ ሲሆን፥ በዚህ የስነ ሕዝብ አወቃቀር ውስጥ ለብዙዎቹ የ 2021 ዱ መፈንቅለ መንግስት ወጣቶቹ በዲሞክራሲ እና ግለሰባዊ ነፃነቶችን አስመልክቶ በነበሯቸው ልምዶች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ በመሆኑ በቀላሉ እንደ ፖለቲካዊ ክስተት ሊገለጽ እንደማይችል ይነገራል።

22 Jan 2026, 13:11