ፈልግ

የማፑቶ ሊቀ ጳጳስ ጆአዎ ካርሎስ ሃቶአ ኑነስ - (ሞዛምቢክ) የማፑቶ ሊቀ ጳጳስ ጆአዎ ካርሎስ ሃቶአ ኑነስ - (ሞዛምቢክ) 

በሞዛምቢክ የማፑቶ ሊቀ ጳጳስ በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች ያላቸውን ቅርበት እና አንድነት ገለጹ

በሞዛንቢክ የማፑቶ ሊቀ ጳጳስ ጆአዎ ካርሎስ ሃቶአ ኑነስ በሃገሪቷ ላይ በደረሰው ከባድ የጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች ቤተክርስቲያኗ ያላትን ቅርበት እና ድጋፍ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሞዛምቢክ በቅርቡ በጣለው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቷ ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ በዚህም አደጋ በርካታ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸው እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል።

ይሄንን ተከትሎ የማፑቶ ሊቀ ጳጳስ ጆአዎ ካርሎስ ኑነስ ለምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ በአደጋው ለተጎዱት ሁሉ ያላቸውን “አንድነት፣ ቅርበት እና ተስፋ” ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ኑነስ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የተፈናቀሉ ቤተሰቦች፣ ንብረታቸውን፣ ኑሯቸውን እና የሚወዷቸውን ሰዎች ያጡ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አፅንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ “ያለቀሱትን ታጽናና ዘንድ፣ ሁሉን ነገር ያጡትን እንድታበረታ፣ የተጎዱትን ለመርዳት እየሰሩ የሚገኙትን እንድትደግፍ የተስፋ እና የመጽናናት እናት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም አማላጅነት አደራ” ብለዋል።

ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ በደቡብ አፍሪካ በተለይም በሞዛምቢክ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በዚምባብዌ ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን፥ በሦስቱ ሃገራት ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው፣ በተለይም ደቡባዊ እና ማዕከላዊ የሞዛምቢክ ክልሎች በጣም መጎዳታቸው እና በሀገሪቱ የጋዛ ግዛት ውስጥ ብቻ ከ300,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ጎርፍ የተፈጥሮ ክስተት ብቻ አይደለም
“መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል” በማለት በመጀመሪያው የሳሙኤል መጽሐፍ ላይ ከሚያስታውሰን የእግዚአብሔር ቃል በመነሳሳት፥ ሊቀ ጳጳስ ኑኔስ ይሄው ተመሳሳይ ቃል እየኖርን ባለው እውነታ በኩል እንደሚናገረን አበክረው ገልጸዋል።

“የጎርፍ መጥለቅለቅ የተፈጥሮ ክስተት ብቻ ሳይሆን፤ እነዚህ አደጋዎች እንደ ግለሰብ፣ ማህበረሰብ እና ህብረተሰብ እንደሚገዳደሩን ጠቅሰው፥ ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ክስተቶች ኃላፊነት እንዲሰማን፣ ማስተዋል እንዲኖረን፣ የጋራ ቤታችንን እንድንንከባከብ እና በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ትኩረት እንድንሰጥ ጥሪ ያደርጉልናል በማለት በአጽንዖት ተናግረዋል።

እግዚአብሔር የሚናገረን በድሆች እና ስቃይ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ጩኸት አማካኝነት እንደሆነ የጠቆሙት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይህን ድምፅ ችላ ማለት ከፍተኛ መዘዝ እንደሚያስከትል አሳስበዋል።

እምነትን ወደ የአንድነት ምልክቶች መተርጎም
የማፑቶ ሊቀ ጳጳስ አሁን ያለንበት ወቅት የባዶ ውንጀላዎች ወይም ከፋፋይ ንግግሮች ጊዜ አለመሆኑን አስታውሰው፥ ነገር ግን ወቅቱ “የግንዛቤ፣ የመለወጥ እና የቁርጠኝነት ጊዜ እንደሆነ፥ እንዲሁም እምነትን ወደ ተጨባጭ የፍቅር እና የአብሮነት ምልክቶች የምንተረጉምበት” ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም መንፈስ በአደጋው የተጎዱ ቤተሰቦችን ስቃይ ለመቅረፍ ካሪታስ ማፑቶ በክርስቲያኖች እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ልግስና ላይ በመተማመን ድጋፎችን የማሰባሰብ ዘመቻ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ኑነስ፥ ቁምስናዎች፣ ማህበረሰቦች፣ ቡድኖች እና ሁሉም የሃገረ ስብከት ምዕመናን ቅስቀሳቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታቱ ሲሆን፥ ይህም ቀላል ግን ውጤታማ የወንድማማችነት አጋዥ ምልክቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

“ትንሽም ቢሆን ሁሉም ሰው የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላል” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ እያንዳንዱ የድጋፍ ምልክት ትልቅ ቦታ እንዳለው፣ እያንዳንዱ የማካፈል ተግባር ሁሉንም ነገር ላጡ ሰዎች የተስፋ ምልክት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ቤቶችን ብቻ ሳይሆን፥ ኃላፊነቶችንም ጭምር መልሶ መገንባት
ሊቀ ጳጳስ ኑነስ በመጨረሻም ከጎርፍ አደጋው በኋላ ያለውን ጊዜ በማስታወስ፥ እኛ የተጠራነው ቤቶችን ለመገንባት ብቻ ሳይሆን ግንኙነቶችን፣ አመለካከቶችን እና ኃላፊነቶችን ለመገንባት በመሆኑ፥ በዚህም ህዝቡ ለወደፊት ተመሳሳይ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ የተሻለ ዝግጁነት፣ ትጋት እና መደጋገፍ እንደሚያሳይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ይህ አስቸጋሪ ጊዜ የበለጠ ንቁ፣ ወንድማማችነት የነገሰባት እንዲሁ ለሰው ልጅ ህይወት እና ለፍጥረት ተቆርቋሪ የሆነች አዲስቷ ሞዛምቢክ የምትወለድበት አመቺ ጊዜ እንዲሆን በመመኘት አጠቃለዋል።

21 Jan 2026, 13:54