ፈልግ

በቅድስት ምድር ውስጥ ዮርዳኖስ አምስተኛው ወንጌል የሚጀምርባት አገር መሆኗ ተገለጸ

በዮርዳኖስ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮች ተከስተዋል። ሙሴ ከመራው ዘጸአት ጀምሮ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ድረስ የክርስትና እምነት መኖር በአገሪቱ ውስጥ እጅግ ጥንታዊ መነሻዎች አሉት።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ስለ ቅድስት ምድር ስናስብ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት፣ ቤተልሔምን፣ ናዝሬትን፣ ቅፍርናሆምን እና ኢየሩሳሌምን ጨምሮ በፍልስጤም እና በእስራኤል ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን እንጠቅሳለን።

ነገር ግን ክርስቲያናዊ ትዝታዎች በየቦታው የሚገኝበት እና ለመንፈሳዊ ንግደት መዳረሻ የሚሆን ሌላ አገር ዮርዳኖስ ነው።

ዮርዳኖስ ሙሴ የአይሁድ ሕዝብን ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራበት ሲሆን በርካታ የብሉይ ኪዳን እና የቅዱስ ወንጌል ታሪኮች የተከናወኑበት ነው። ሙሴ ከመሞቱ በፊት የከነዓንን ምድር ማየት የቻለበት ምድር ነው።

ዮርዳኖስ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበት ምድር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያዎቹን ሐዋርያት እንድርያስን እና ጴጥሮስን ያገኘበት፣ የታመሙትን የፈወሰበት እና ተአምራትን ያደረገበት ቦታ ነው።

በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በድንበር የሚያዋስናቸውን አገሮች ማለትም ሶርያን፣ ኢራቅን፣ ሳውዲ አረቢያን፣ እስራኤልን እና ፍልስጤምን ማሰብ በቂ ይሆናል። ዮርዳኖስ የተረጋጋ እና በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ወጎች ውስጥ በሰላም አብሮ የመኖር ባህል ጎልቶ የሚታይበት አገር ነው።

ዮርዳኖስ ውስጥ ክርስቲያኖች አናሳ ቁጥር ሲኖራቸው ከጠቅላላው ሕዝብ አራት በመቶ ይሆናሉ። ነገር ግን የአገሪቱ ሙሉ ዜጎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን ያስተዳድራሉ። የላቲን ሥርዓት በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ውስጥ በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ በሚመራው ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙት ትልቁን ቁጥር ይይዛሉ።

በሙት ባሕር እና በቀይ ባሕር ዳርቻዎች በሚገኙ የመዝናኛ ሥፍራዎች ምክንያት ዮርዳኖስ ለአገር ጎብኚዎች እና መንገደኞች ምቹ መድረሻ ናት። ዮርዳኖስ ከሁሉም በላይ ባልተለመደ ውበት ከድንጋይ የተቀረጸች “ፔትራ” የሚገኝባት እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1985 ዓ. ም. ጀምሮ ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የመዘገባት ጥንታዊት የናባታ ከተማ የሚትገኝባት ስትሆን በዛሬ ዘመን የክርስትና ቅርሷን የበለጠ ለማጉላት ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

አቃባ እና ፔትራ

ከ3ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተገነባው የአቃባ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ሆን ተብሎ ለክርስቲያናዊ አምልኮ የተገነባ እጅግ ጥንታዊ ሕንፃ ሆኖ ቀርቧል። ቤተ ክርስቲያኑ በአርኪኦሎጂስቶች የተገኘው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1998 ዓ. ም. ነበር።

ዳርቻዎቿ በሮማ ግዛት ውስጥ ያሉ በመሆናቸው ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅላጢያን እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ303 ዓ. ም. ቤተ ክርስቲያን እንዲገነባ በማወጁ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በተከሰተው ታላቅ ስደት ወቅት ከጥፋት እንዳዳናት ይታወቃል።

ቅሪቶቹ ቀይ ባሕርን በሚመለከት በዮርዳኖስ የባሕር ዳርቻ ከተማ ውስጥ እንደሚገኙ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ቡድን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሰኔ 1998 ዓ. ም. አረጋግጧል።

የቤተ ክርስቲያኑ አስደናቂነት ወዲያው የታየው በሥነ ሕንፃ ሥራው ሲሆን ይህም በታሪክ ምሁራን ዘንድ በዮርዳኖስ የመጀመሪያዎቹ የክርስትና አምልኮ ቦታዎች በ4ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የተገነቡ መሆናቸውን ይገልጽ ነበር።

የዚህ ጽሑፍ ደራሲ እሁድ ከሰዓት በኋላ መስዋዕተ ቅዳሴን እንዲያስቀድሱ የተፈቀደላቸው ጎብኚዎች ምዕመናን አባል ሲሆን፥ ሥነ-ሥርዓቱ የተፈጸመው ጎኖቹ ክፍት በሆነ ሸራ በተሸፈኑ ፍርስራሾች ውስጥ ነበር።

ክርስቲያኖች እንዲህ በመሰለ ሁኔታ እንዲያመልኩ በይፋ መፈቀዱ በአብዛኛው የሙስሊም ማኅበረሰብ አገር ዮርዳኖስ ውስጥ የተለያዩ እምነቶች አብረው የሚኖሩባት አገር መሆኗን ያረጋግጣል።

ታላቋ የፔትራ ከተማ የክርስትና እምነት ትዝታዎችን ጠብቃ አቆይታለች። በተለይም ከ5ኛው እስከ 6ኛው ክፍለ ዘመን የሕይወት እና የተፈጥሮ ትዕይንቶችን የሚያሳይ የባይዛንታይን ቤተ ክርስቲያን ከአረማዊ ጌጣጌጦች ወደ ክርስቲያናዊ ጭብጦች መሸጋገርን ያሳያል። ቀድሞ ከነበሩ ከውሃ ማጠራቀሚያዎች ከተሠሩ ትላልቅ ጥንታዊ መጠመቂያዎችን መካከል አንዱን ይዟል።

በአቅራቢያው የሚገኝ የባዚሊካው ጸሎት ቤትም “ሰማያዊ ቤተ ክርስቲያን” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በቀድሞ የናባቴያን የአምልኮ ቦታ ላይ የተገነባ እና በኋላም በእሳት ቃጠሎ እና በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ወድሟል።

የኔቦ ተራራ

የኔቦ ተራራ የክልሉን ልዩ ገጽታ የሚያጎላ ድንቅ ውበት ያለው ሲሆን ከዚህ ተራራ ጫፍ ላይ በመሆን የሙት ባሕርን እና የይሁዳ በረሃን፣ የዮርዳኖስ ሸለቆን እና የሰማርያ ተራሮችን ማድነቅ ይቻላል።

በጠራራ ቀናት ኢየሩሳሌምን እና ወደ ቅድስት ከተማ የሚወስደውን መንገድ ማየት ይቻላል። ቦታው የተገኘው እና ቁፋሮ የተጀመረው በቅድስት ምድር ተንከባካቢ በሆኑት በተለይም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1932 ዓ. ም. መሬቱን መግዛት በቻለው በወንድም ጂሮላሞ ሚሃይክ ብርታት ነው።

በ1930ዎቹ እና ከዚያም በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተካሄዱ የቁፋሮ ሥራዎች በወታደራዊ ግጭቶች ምክንያት ተቋርጠው የነበረ ቢሆንም በኋላም በ1970ዎቹ በአባ ሚሼል ፒቺሪሎ እንደገና ተጀምረው ልዩ የሆነ ቅርስን ግልጽ ለማድረግ አስችለዋል።

ቦታው በ4ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በቅድስት ምድር ውስጥ በነበሩት ነጋዲያን ኤጌሪያ እና በኋላም የጋዛ ጳጳስ በነበሩት ፒተር ኢቤሪያን ተጠብቆ ቆይቷል። ቁፋሮዎቹ ሙሉ በሙሉ የተጠበቁ በተለይም የባይዛንታይን በባለ ልዩ ልዩ ቀለማት ጠጠሮች የተሳሉ ውድ ምስሎችን አሳይተዋል።

ዛሬ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ430 ዓ. ም. የተገነባ የመጀመሪያው ባዚሊካ፣ በቀጣዮቹ ዓመታት የተገነቡ ገዳማት፣ በ500 ዓ. ም. የተገነባውን ታላቅ ባዚሊካ ሦስት ግማሽ ክቦች፣ ጥንታዊ መጠመቂያ ቦታዎች፣ ከዚያም የ6ኛው ክፍለ ዘመን ባዚሊካ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ቤት ቅሪቶችን መለየት ይቻላል።

በዘመናት ውስጥ መዋቅሮቹ በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የወደሙ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2016 ዓ. ም. ጀምሮ ነጋዲያን በእንጨት በጥንቃቄ ወደተገነባው ባዚሊካ ሲመጡ አቀባበል ይደረግላቸዋል። ይህም ዘመናዊው ግንባታ ጥንታዊውን ሳይሸፍነው ጎልቶ እንዲታይ ለማድረግ ያስችላል።

ማቻየረስ

በተራራው ላይ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ90 ዓ. ም. በንጉሥ አሌክሳንደር ያናየስ የተገነባ የሃስሞኒያን ምሽግ ይታያል። ወታደራዊው ምሽጉ በሮማውያን የወደመ ሲሆን፥ በ30 ዓ. ም. ታላቁ ሄሮድስ ክረምቱን ለማሳለፍ እዚያው የቤተ መንግሥት ምሽግ መገንባት ጀመረ።

ከዚህም ሥፍራ ሆኖ አንድ ሰው ዙሪያ ልዩ ውበት ያለውን ቦታ አይቶ መደሰት ይችላል። ከአካባቢው የተገኙት ቅሪቶች ወደ ተራራው ልብ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ለአገልጋዮች በተሰየመ መንደር የተከበበ ቤተ መንግሥትን ያመለክታሉ።

ከዚህ ቦታ ታላቁ ሄሮድስ በሙት ባሕር በኩል ሕክምናን ለማግኘት ይጓዝ ነበር። እንደሚባለው መጥምቁ ዮሐንስ በእነዚህ ግድግዳዎች ውስጥ ታስሮ ነበር። እዚህ ንጉስ ሄሮድስ የሰሎሜን ፍላጎት ተቀብሎ የመጥምቁ ዮሐንስ ጭንቅላት እንዲቆረጥ አዘዘ።

ምሽጉ እንደ ጎርጎርሳውያኑ በ37 ዓ. ም በንጉሥ አርጤስ አራተኛ ፈርሶ በ71 ዓ. ም በሮማውያን ሙሉ በሙሉ ወድሟል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት

እጅግ በጣም ጉልህ የሆነው ወንጌላዊ ቦታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት የተከናወነበት ቦታ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው እና “ከዮርዳኖስ ማዶ” የሚለው “ቢታንያን” የሚገልጽ ሲሆን፥ ይህ ሥፍራ በክርስትና ዘመን የመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት ቤተባራ በመባል የሚታወቅ እና ዛሬ አል-ማግታስ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በአረብኛ “ጥምቀት” ወይም “መዘፈቅ” ማለት ነው።

እንዲሁም በዮርዳኖስ ውስጥ ሌላ መታየት ያለበት ቦታ በሆነው በታዋቂው የማዳባ ካርታ ላይ ይታያል። ይህም ከ6ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተገኘ የሞዛይክ ካርታ ሲሆን የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎችም ይህን ያረጋግጣሉ።

በ5ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ6ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ መካከል የባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት አናስታሲየስ ዲኮረስ ቀዳማዊ ለመጥምቁ ዮሐንስ የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ መገንባቱ በወቅቱ በነበሩ ምዕመናን ተገልጿል።

በኋላ ላይ የቅድስት ሥላሴ ባዚሊካ በዚህ ቦታ የተገነባ ሲሆን ቢያንስ 27 ሜትር ርዝመት እና ከ15 ሜትር በላይ ስፋት ያለው ቤተ ክርስቲያን ነው። በዙሪያው በተደረጉ ቁፋሮዎች የገዳማውያን ዋሻዎች፣ ጸሎት ቤቶች፣ በባለ ልዩ ልዩ ቀለማት ጠጠሮች የተሳሉ ምስሎች፣ የእብነበረድ ወለሎች እና ትልቅ የመስቀል ቅርጽ ያለው የጥምቀት ሥፍራ ተገኝተዋል።

ከቦታው ብዙ ሳይርቅ ከነቢዩ ኤልያስ መታሰቢያ ጋር የተያያዙ ቅሪቶችም የተገኙ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. አካባቢው በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።

እዚህም ቢሆን ቦታውን ከወራሪዎች ጣልቃ ገብነት ለመጠበቅ የተደረገው ምርጫው አስገራሚ ነው። የጥምቀት ሥፍራው ዳይሬክተር ሩስተም ማክጂያን እንደገለጹት፥ አንዳንድ ቦታዎች በቀላል የእንጨት መዋቅሮች መሸፈናቸውን ገልጸዋል።

“ስምንተኛው ቅዱስ ምስጢር”

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ቅድስት ምድርን እንደ “አምስተኛ ወንጌል” እና ስምንተኛ ቅዱስ ምስጢር ብለው ለመጥራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ምክንያቱንም ሲገልጹ “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በአካል ለመገናኘት እና ለመንካት ስለሚያስችል ነው” ብለዋል። ወደ ቅድስት ምድር ሳይሄድ ሁሉም ሰው ፍጹም ክርስቲያን ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፥ “ነገር ግን ወደ ቅድስት ምድር የሚሄዱ ከሆነ የክርስትና እምነት የበለጠ ጠንካራ እና ተጨባጭ ይሆናል” ሲሉ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ከዮርዳኖስ ባቀረቡት ጥሪ፥ ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት የሚመሰክሩ ድንጋዮችን በገዛ እጃቸው እንዲነኩ እና “ሕያዋን ድንጋዮች” ከሚወክሉ የዛሬዎቹ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ጋር እንዲገናኙ ግብዣቸውን አቅርበው አክለውም፥ ሁሉም ሰው ቅድስት ምድርን እንዲጎበኝ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከሰብዓዊነቱ ጋር የመገናኘት አስደናቂ ተሞክሮ እንዲኖረው ብርታትን ተመኝተዋል።

 

17 Jan 2026, 16:10