ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ የ2018 ዓ/ም የገና በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
"በዚያም የበኩር ልጇን ወለደች በመታቀፊያም ጨርቅ ጠቀለለችው፤ በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ስላላገኙ በበረት በከብቶች መመገበያ ግርግም ውስጥ አስተኛችው" (ሉቃ 2፡7)።
በክርስቶስ የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት
ክቡራን ካህናት
ገዳማውያንና ገዳማውያት
መላው የአገራችን ሕዝቦች
ከአገራችሁ ውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና
ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የተወደዳችሁ ምዕመናን፣
እንኳን ለ2018 ዓ/ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
የእምነታችን ዐቢይ ቁም ነገር እግዚአብሔር የሰው ልጅን መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን ሁል ጊዜ ወደ ሰው ልጆች መምጣቱ ነው። የሰው ልጆች ሁኔታ ግድ የሚለው አምላክ በፍቅርና ስለ ፍቅር ራሱን ዝቅ አድርጎ የሰውን መልክ ወሰደ "ቃል ስጋ ሆነ"!
ይህንን ታላቅ ምሥጢር የተለያዩ የቤተክርስቲያን አባቶች በመንፈሳዊ አስተምህሮታቸው ገልጸውታል። ከእነኚህ አባቶች መካከል ከዛሬ 1700 ዓመት በፊት የተወለደው ቅዱስ ኤፍሬም ብዙ ያስተምረናል። ከዚህም ውስጥ “የክርስትና ሚስጥር ባህርይ በጣም አስገራሚ ነው። አምላክ ሰው ሆኖ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ሰው ሊበላው የተገባ እንጀራ መሆኑ ነው" በሌላ አነጋገር የቅዱስ ቁርባን ምስጢር የገና ፍሬ መሆኑን ያስረዳል።
እዚህ ላይ ክርስቲያን ሁሉ ሊያጤነው የሚገባው ቁምነገር ክርስቶስ እረኛም በግም ተብሎ መጠራቱ ነው። ባንድ በኩል መልካም እረኛ ነው። ማለትም ይመግባል፤ይመራል፤ ይጠብቃል። እንደ ዮሐንስ ወንጌል አቀራረብም መልካም እረኛው ክርስቶስ ነፍሱን ስለ ወገኖቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ የሰው ልጆች የወደቁበት አዘቅት ድረስ ወርዶ ሰውን ተሸክሞ ያወጣዋል። ታዲያ ይህ እውን የሆነው ቃል ሥጋ ስለሆነ ነው። ዛሬ የምናከብረው ይህንን በዓል ነው።
የልደት ወይም የገና በዓል የምሥራች የሁሉም መሠረት የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን በኛም መካከል ማደሩን ነው። እንደማርያም ግርግም መምረጡ ከሰው አእምሮ አድማስ በላይ የሆነውን ትሕትናውን እንድናስተውል ይጋብዘናል። የሕይወት ውሃ በመሆኑ ደግሞ እርሱን እንድንመስል በእርሱ እንድንለወጥ በፀጋው እንሞላለን።
የክርስቶስ መወለድና በእኛ መካከል ማደር የእኛን እንደገና መወለድ በማምጣት እንደገና እንድንፈጠር አደረገን። ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለውም አሮጌው ሰውነት አልፎ አዲስ ሰውነት መጣ። ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው የሚለው አረፍተ ነገር እራሳችንን እንድንመረምር የሚጋብዝ ነው። ስለዚህ እኛም አዲስ ፍጥረት መሆናችንን የሚያረጋግጡ ሐሳቦችና ተግባራት የትኞቹ ናቸው ብለን ልንጠይቅ ያሻል። በግልም ሆነ በጋራ ምን ስናስብና ምን ስንሠራ ይሆን አዲስ ፍጥረት መሆናችንን የምንመሰክረው?
የተወደዳችሁ ምዕመናን፣
ሁላችንም የምንገረምበት በዓል ተሰጥቶናልና ከልብ እናመሰግን። ምስጋናችንም ወደ ቤታችን፤ ወደ ጎረቤቶቻችን፤ ወደ እለታዊ ኑሮአችን፤ ወደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲደርስ እንፀልይ። ምስጋናችን የሐሳብና የተግባር ለውጥ ሲያመጣ ለንሰሐና ለመልካም ሕይወት መሠረት ሲጥል ፍሬያማ ሆነ ለማለት እንችላላን።
የልደት በዓል የሚያበስረን የዓለም መጋቢ ምግብን ከቅድስት ማርያም ማግኘቱን መለኮታዊ እሳት ሆኖ በእርሷ ማህፀን ማደሩን ነው። እኛም አሁን እንደ እረኛውና እንደበጉ ምሳሌ መለኮታዊ እሳት በቅድስት ማርያም ውስጥ ማደሩን እንድናደንቅ፤ እንድንመረምር በተለይም እንድናወድስ ተጠርተናል። ሌላውም አስደናቂ ነገር ”ቃል በእመቤታችን ማህፀን ውስጥ አድሮ ጸጥታ ሆነ”። እንደምናውቀው ቃልና ዝምታ በመሰረቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በልደት በዓል ግን ይህ እውን ሆነ።
የተከበራችሁ ምዕመናን፣
እንግዲህ በዚህ መንፈስ በመገረምና በምስጋና፣ በመደነቅና በውዳሴ የልደትን በዓል እናክብር። የልደት በዓል መሪያችን፤ መጋቢያችን፤ ጠባቂያችን እራሱን የሰጠበት በዓል ስለሆነ ስለ ወገኖችና ስለ ሰው ልጆች ክብር የምንሰራበት፣ ህዝቦች የሚከባበሩበት፣ የሚዋደዱበትና የሚተሳሰቡበት፤ የጦርነትና የግጭት መንፈስ ከአገራችን የሚወገድበት፤ ሰላም በአገራችንና በህዝቦቻችን መካከል የሚወርድበትን፤ ከጥፋት ይልቅ ወደ አንድነትና ህብረት የሚመጡበት፤ የተሰደዱትና የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ስፍራቸውና ቄያቸው የሚመለሱበት፣ ተማሪው በትምህርቱ፤ አርሶ አደሩ በግብርና ሥራው፤ ሠራተኛው በየሥራ መስኩ ተሰማርቶ፣ መገዳደል አብቅቶ ልጆቻችንም ጭንቀትንና ችግርን ሳይወርሱ በንጹህ ሃሳብና ህሊና መልካም ዜጎች ሆነው እንዲኖሩ ስለ ሰላም ሁሉም ተባብሮ እንዲሠራ ስንል በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን።
በዚህ የልደት በዓል ጊዜ ሁላችሁም በጦርነት ምክንያት ስለተፈናቀሉና ስለተሰደዱ፣ በተፈጥሮ ምክንያት ከቄያቸውና ከመንደራቸው ስለራቁ መጸለይና ማገዝ፣ እንደዚሁም ለአቅመ ደካሞች፤ ለህሙማን፤ አስታዋሽና ረዳት ለሌላቸው፣ በየጎዳናው ላሉ ወገኖች፣ ያለንን በመስጠትና በማካፈል በማብላትና በማጠጣት፤ የታረዙትን በማልበስ በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ ማድረግ ክርስቲያንያናዊ ግዴታችሁ ስለሆነ በደስታ፣ በትህትናና በፍቅር በመፈፀም የልግስና ሥራ እንድታደርጉና እንድትፈፅሙ አደራ ማለት እወዳለሁ።
በመጨረሻም በዚህ በጌታችን በመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶሰ የልደት በዓል ለታመሙት ምህረትን፤ በተለያየ ሁኔታ በሃሳብ፤በጭንቀት፤በመከራ ላይ ለሚገኙት ጌታ ሰላሙንና ፍቅሩን እንዲሰጣቸው፤ በማረሚያ ቤቶች ለሚገኙት የህግ ታራሚዎች ጌታ መጽናናትንና መፈታትን እንዲያድላቸው፤ በልዩ ልዩ በሽታ በተለይ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝባቸው ምዕመናን መንፈሳዊና ዘመናዊ ሕክምናን በአንድነት መውሰዳቸው በእምነት የሚደገፍ መሆኑን አውቀው እንዲታከሙ ማግለልም እንዳይደርስባቸው፤ እንዲሁም በሀገር በዳር ድንበር በውትድርና ተሰማረተው ለሚገኙ ሁሉ በዓሉን በሰላም እንዲያከብሩ ጸልዩላቸው።
ሁላችንም የሰላሙ ንጉስ ሰላማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ሰላሙን ለአገራችን እንዲሰጠን በፀሎት እንበርታ።
ልዑል እግዚአብሔር የተቀደሰና የተባረከ የልደት በዓል ያድርግልን።አሜን።
ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር