በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ለሕጻናት የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ለሕጻናት የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት   (foto Facebook Br. Maciej Jabłoński - Misje)

የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጳጳሳት ሰላም መብት እንጂ ቅንጦት አይደለም ሲሉ አስታወቁ

የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በምልአተ ጉባኤያቸው መጨረሻ ላይ አዲሱ መንግሥታቸው ለዓመታት የዘለቀውን ዓመፅ፣ መፈናቀል፣ ድህነት እና መከፋፈልን በማስቆም በአገሪቱ ውስጥ ሰላምን እንዲያስጥብቅ ሲሉ ጠንካራ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የመካከለኛው አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ በምልአተ ጉባኤው መጨረሻ እሑድ ጥር 3/2018 ዓ. ም. ባስተላለፈው መልዕክት እያንዳንዱን ዓመፅ ለማስቀረት በፍትህ እና በፖለቲካዊ ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅርቧል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በታኅሳስ ወር በተካሄደው ምርጫ ፕሬዝደንት ፋውስቲን-አርሻንዥ ቱዋዴራ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ነው።

የፕሬዝዳንት ቱዋዴራ ዳግም መመረጥ ማረጋገጫ የመጣው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. በተካሄደው አወዛጋቢ ሕዝበ ውሳኔ አማካኝነት በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ከፀደቀ በኋላ ሲሆን፥ ይህም የሁለት ተከታታይ የሥልጣን ወሰን አስወግዶ የቆይታ ጊዜያቸውን ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት በማራዘም የፖለቲካ እና የተቋማዊ ሥርዓት ፕሬዝዳንታዊ ባህሪን ያጠናክራል።

የአካባቢ ባለስልጣናት ለ40 ዓመታት ያህል አለመመረጣቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በበርካታ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ከክልላዊ አስተዳደር ምርጫዎች ጋር ተካሂዷል።

ሰላም የጦርነት አለመኖር አይደለም

መንግሥት አገሪቱን ለማረጋጋት ከአንዳንድ የታጠቁ ቡድኖች ጋር እየተደራደረ ባለበት ወቅት ተቃዋሚ ቡድኖች የምርጫ ማጭበርበርን እና አፈናን አውግዘዋል፣

እንዲሁም ሚሊሻዎች ሕገወጥ ተግባራትን እንዲተዉ ለማበረታታት የሚያስችል የኢኮኖሚ እጥረት ምክንያት ሲሆን፥ በርካታ የታጠቁ ቡድኖች በተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ (MINUSCA) በመታገዝ ከብሔራዊ የጦር ኃይሎች (FACA) ጋር መዋጋታቸውን ቀጥለዋል።

የአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት በዚህ ደካማ እና ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ በተከታታይ በሰብዓዊ ቀውስ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ችግር እንዳይባባስ በማለት ለእግዚአብሔር ቤተሰብ እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

“የእግዚአብሔር ክብር ሰላም ነው” ያሉት ጳጳሳቱ፥ ሰላም ጦርነት እና ግጭት ባለመኖሩ ብቻ ሊቀንስ እንደማይችል ተናግረዋል። በድምጽ መስጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተሳተፉትን እና የምርጫ ሂደቱን የተከታተሉትን የመካከለኛው አፍሪካ ህዝቦች ብስለት በማመን እንዲሁም በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የተከሰቱትን አለመግባባቶች አጋልጠዋል።

የሰላም ጠላቶች ሙስና፣ የስልጣን አላግባብ መጠቀም እና ያለመከሰስ መብት ናቸው

ይህ ሁሉ እያደገ የመጣው የዜግነት ስሜት ምልክት መሆኑን አፅንዖት የሰጡት ጳጳሳቱ፥ ይህን ባሕል መጠበቅ፣ ማጠናከር እና ለወደፊት ትውልዶች ማስተላለፍ እንደሚገባ አሳስበዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ እንዲሁም ሰላም ለዓመታት በዓመፅ፣ በመፈናቀል፣ በድህነት እና በማንነት ላይ በተመሠረቱ ልዩነቶች የተመሰከረለት የአገሪቱ ጥልቅ ምኞት እንደሆነ አስታውሰዋል።

“ሰላምን ማግኘት ቅንጦት አይደለም” ሲሉ የጻፉት ጳጳሳቱ፥ ሰላም የእያንዳንዱ ዜጋ የማይገረሰስ መብት እና ግዴታ ነው” ብለው፥ የስልጣን አላግባብ መጠቀም፣ ሙስና፣ ወገንተኝነት እና ያለመከሰስ መብት የሰላም ጠላቶች ናቸው” ሲሉ በግልጽ አውግዘዋል።

የመካከለኛው አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ “ጠንካራ፣ ተዓማኒ እና ግልጽ ተቋማት ከሌሉ እውነተኛ ዕድገት ሊገኝ አይችልም” ሲሉ በማስጠንቀቅ፥ በድህረ-ምርጫ ወቅት ሁሉም ሰው የሌሎችን የፖለቲካ ምርጫዎች እንዲያከብር በማሳሰብ “የፖለቲካ ተቃዋሚ ጠላት አይደለም” ሲል አክሏል።

የአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት እንደሚሉት፥ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጥላቻ እና በዓመፅ ላይ የተገነባ ሳይሆን በውይይት፣ በወንድማማችነት እና በጋራ ጥቅም ላይ ብቻ የተገነባ ነው” ብለዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም የሃይማኖት ተቋማት ጸሎትን፣ ኅብረትን እና በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይትን እንደ እውነተኛ የእርቅ እና የሰላም መንገዶች አድርገው ቆጥረው እንዲያጠናክሩት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 

 

14 Jan 2026, 15:18