እግዚአብሔር ሰማይና ምድር ፈጠረ እግዚአብሔር ሰማይና ምድር ፈጠረ 

ሰማይና ምድር

እግዚአብሔር ምን ፈጠረ?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ 1፡1)። ቤተክርስቲያን በእምነት መግለጫዋ እግዚአብሔር የሚትየውንና የማይታየውን፣ መንፈሳዊያንና ሥጋውያንን ሁሉ ማለትም መላእክትንና ቁሳዊ ፍጥረታትን እንዲሁም ልዩ በሆነ መንገድ ሰውን የፈጠረ አምላክ መሆኑን ትሰብካለች።

መላእክት እነማን ናቸው?

መላእክት አካላዊ ያልሆኑ፣ የማይታዩ፣ የማይሞቱና የአእምሮና ነፃ ፈቃድ ያላቸው ግላዊና ሙሉ በሙሉ መንፈሳዊ ፍጡራን ናቸው። እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ያለማቋረጥ ያሰላስሉታል፣ ያሞግሱታልም፤ ያገለግሉታል፤ የማዳን ተልእኮውንም በመፈጸም ረገድ የእርሱ መልእክተኞች ናቸው።

መላእክት በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሚገኙት በምን ዐይነት መንገድ ነው?

ቤተክርስቲያን ከመላእክት ጋር ሆና እግዚአብሔርን ታመልካለች፣ የእነርሱንም እርዳታ ትለምናለች፣ በሥርዓተ አምልኮዋ ውስጥም አንዳንዶቹን ትዘክራለች። “በእያንዳንዱ ምእመን ጎን ጠባቂና ወደ ሕይወት የሚመራው እረኛ የሆነ መልአክ አለ” (ታላቁ ቅዱስ ባሲልዮስ)።

ስለሚትየው ዓለም መፈጠር መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

መጽሐፍ ቅዱስ “የስድስቱን ቀናት” የፍጥረት ታሪክ በማውሳት የተፈጠረው ዓለም ዋጋና ዓላማው እግዚብሔርን ለማመስገንና ሰውን እንድናገለግል ያስተምረናል። እያንዳንዱ ነገር ሕልውናውን ያገኘው ከእግዚአብሔር ነው፣ከእርሱም መልካምነትንና ፍጹምናን፣ ተገቢ ሕግጋቱንና በሥነ ፍጥረት ውስጥ ያለውን ተገቢ ስፍራ ያገኛል።

በፍጥረት ውስጥ የሰው ቦታ ምንድነው?

በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረ እንደመሆኑ መጠን ሰው (ወንድም ሆነ ሴት) የሚታይ ፍጥረት ቁንጮ ነው።

በፍጥረታት መካከል ምን ዓይነት ትስስር አለ?

እግዚአብሔር በፈቀደው መሠረት በፍጥረታት መካከል የእርስ በርስ መደጋገፍና መበላለጥ አለ። ከዚሁ ጋር የሁሉም ፈጣሪ አንድ ስለሆነና እርሱም ስለሚወዳቸውና ለክብሩ የተገዙ በመሆናቸው በፍጥረታት መካከል አንድነትና ህብረትም አለ። ስለዚህ፣ በፍጥረት ውስጥ የተጻፉትን ሕጎችና ከነገሮች ባህርይ የሚመነጩትን ግንኙነቶች ማክበር የጥበብ መርህና የግብረ ገባዊነት መሠረት ነው።

በፍጥረት ሥራና በደኅንነት ሥራ መካከል ያለው ግንኙነት ምንድነው?

የፍጥረት ሥራ የሚፈጸመው ተለቅ ባለው የደኅንነት ሥራ ነው፤ ሁሉም ነገር እውነተኛ ትርጉሙንና ፍጻሜውን መልሶ ለሚያገኝበት ለአዲስ ፍጥረት መነሻ የሚሆነውም እርሱ ነው።

ሰው

ወንድና ሴት «በእግዚአብሔር አምሳል» መፈጠራቸውን የምንገነዘበው እንዴት ነው?

ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነው ሲባል እርሱ ወይም እርሱዋ ፈጣሪያቸውን በፈቃደኝነት የማወቅና የመውደድ ብቃት አላቸው ማለት ነው። በምድር ላይ ስለእርሱነቱ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረው ሰው ብቻ ነው፤ እግዚአብሔርም በዕውቀትና በፍቅር በራሱ መለኮታዊ ሕይወት እንዲካፈል የጠራው እርሱን ነው። ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ በመሆናቸው ሰብአዊ ክብር አላቸው። ሰው ትንሽ ነገር ሳይሆን ራሱን የማወቅና ራሱን በፈቃዱ አሳልፎ የመስጠት እንዲሁም ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ጋር ህብረት የመፍጠር ችሎታ ያለው ሰብአዊ ፍጡር ነው።

እግዚአብሔር ወንድና ሴትን የፈጠረው ለምን ዓላማ ነው?

እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ለሰው ጥቅም ፈጠረ፤ ሰዎች የተፈጠሩት ደግሞ እግዚአብሔርን እንዲያውቁ፣ እንዲያገለግሉና እንዲወዱ፣ የዚህን ዓለም ፍጥረት ሁሉ መልሰው ለእርሱ በምስጋና መልክ እንዲያቀርቡና በሰማይ

ከእርሱ ጋር ወደ ሚኖራቸው ሕይወት ከፍ እንዲሉ ነው።

የሰው ልጅ ምስጢር እውነተኛ ትርጉም የሚኖረው ሥጋ በለበሰው ቃል ምሰጢር ብቻ ነው። ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ «የማይታይ አምላክ ፍጹም አምሳያ» (ቆላ. 1፡15) ነው። ወንድና ሴትም የዚህን አምሳያ ለመፍጠር ከመጀመሪያው የታጩ ናቸው።

የሰው ዘር አንድ የሆነው ለምንድነው?

የጋራ መገኛው እግዚአብሔር ስለሆነ የሰው ዘር በሙሉ አንድ ነው። እግዚአብሔር «ሕዝቦችን በሙሉ ከአንድ የዘር ሐረግ ፈጠረ» (የሐዋ. 17፡26)። ሁሉም አንድ አዳኝ ብቻ አላቸው፣ ሁሉም በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ደስታ እንዲካፈሉ ተጠርተዋል።

ነፍስና ሥጋ በሰው ውስጥ አንድ የሚሆኑት እንዴት ነው?

የሰው ልጅ በአንድ ላይ ሥጋዊም መንፈሳዊም ነው። በሰው ውስጥ መንፈስና ቁስ አንድ ባህርይ ይኖራቸዋል። ይህ አንድነት እጅግ መሠረታዊ ከመሆኑና ነፍስ ከሆነው ከመንፈሳዊው መምሪያ የተነሣ ቁሳዊ የሆነው ሥጋ ሕያው

የሰው አካል ሆኖ ከእግዚአብሔር አምሳል ክብር ይጋራል።

ነፍስ ከየት መጣች?

ረቂቅ ነፍስ የምትገኘው ከወላጆች ሳይሆን ወዲያውኑ በእግዚአብሔር የተፈጠረችና ዘለዓለማዊት ናት። ነፍስ በሞትጊዜ ከሥጋ ስትለይ አትጠፋም፣ በመጨረሻ ትንሣኤ ጊዜም ተመልሳ ከሥጋ ጋር ትዋሐዳለች።

እግዚአብሔር በወንድና በሴት መካከል የመሠረተው ወዳጅነት ምንድነው?

ሁለቱም ሰዎች በመሆናቸው ወንድና ሴት እኩል ክብር ያላቸው የእግዚአብሔር ፍጡራን ናቸው። ተባዕትና እንስት በመሆናቸውም የተፈጠሩት በመደጋገፍ እንዲኖሩ ነው። ሰብአዊ ህብረት ፈጥረው እንዲኖሩና አንዳቸው ለሌላው እንዲሆኑ እግዚአብሔር ፈቀደ። በተክሊል «አንድ ሥጋ» (ዘፍ.2፡24) ሆነው ሰብአዊ ሕይወትን ለሌላ እንዲያስተላልፉ ተጠርተዋል። እንደዚሁም እንደ እግዚአብሔር «ባለሟልነታቸው» ምድርን እንዲገዙ ተሰይመዋል።

በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት የሰው ልጅ የመጀመሪያ ሁኔታ ምን ነበር?

እግዚአብሔር ወንድና ሴትን ሲፈጥር በቅድስናና በጽድቅ በእሱ መለኮታዊ ሕይወት ውስጥ በልዩ ሁኔታ እንዲሳተፉ ፈቅዶላቸው ነበር። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት መሠቃየት ወይም መሞት አልነበረባቸውም። ከዚህ በተጨማሪ፣ በራሱ በሰው ውስጥ፣ በፍጥረትና በፈጣሪ መካከል፣ በወንድና ሴት መካከል፣ በመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስትና በመላው ፍጥረት መካከል ፍጹም ስምምነት ነበር።

 

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካጸደቁት፣ በአጭሩ ከተጻፈው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ከዋናው ከላቲን ቅጂ ከተተረጎመው መጽሐፍ ከአንቀጽ 340-384 ላይ የተወሰደ።

አቅራቢ፣ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን  

29 Jan 2026, 15:06