ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ የሆንግ ኮንግ ሀገረ ስብከት 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ መገኘታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የሆንግ ኮንግ ሀገረ ስብከት የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ለማስታወስ የጸሎት፣ የመዝሙር እና የተለያዩ የአምልኮ ሥነ ስርዓቶች የተካሄዱ ሲሆን፥ በዚህ መርሃ ግብር ላይም ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የመጡ በርካታ ምዕመናን መገኘታቸው ተነግሯል።
ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ሆንግ ኮንግ በሚገኘው ‘ቻርተር ጋርደን’ ውስጥ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር “የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ፊት ሁል ጊዜ በሆንግ ኮንግ ላይ ይብራ” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ፥ በሥነ ስርዓቱ ላይ ለተገኙት ምዕመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግሌ ክርስቲያናዊ የበረከት ልምምድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመጣጥ እና ምንነት ያብራሩ ሲሆን፥ በማስከተልም ብፁዕነታቸው የሆንግ ኮንግ ጳጳስ ከሆኑት ጀሱሳዊው ብፁዕ ካርዲናል እስጢፋኖስ ቻው ሳኡያን ጋር በመሆን በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙትን በሙሉ እና መላውን ከተማ መባረካቸው ተነግሯል።
ከኢየሱስ ፊት ጋር መገናኘት
የቫቲካን የዜና ወኪል የሆነው ፊደስ ኒውስ እንደዘገበው የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪው በተለይ በዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ “ጌታ ፊቱን ያብራልህ ሰላምም ይስጥህ” ተብሎ ከተፃፈው የቡራኬ መልዕክት ላይ በመነሳሳት ህዝቡን እንደባረኩ የገለጸ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ሊሰጠን የሚፈልገው በረከት በዘመናት ሁሉ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በወንዶች እና በሴቶች ላይ ያበራ ዘንድ መሆኑን ብፁዕነታቸው መናገራቸውን ፊደስ ዘግቧል።
“እግዚአብሔር ለእኛ እና ለሆንግ ኮንግ የሚሰጠን በረከት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ቅዱስ ፊቱን እንድናይ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ፥ ይህ ፊት ሁለቱንም “ፍፁም መለኮታዊ እና ፍፁም ሰው” የሆነ ፊት ነው በማለት የገለጹ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው ከዚህም በተጨማሪ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፊት ህፃናት ‘ሁልጊዜ ለህብረተሰብ በረከት’ ስለሆኑ በእነሱ ፊት በኩል ማግኘት እንደሚቻል አስረድተው፥ “ማንኛውም ህፃን ወይም ወጣት በረከት እንጂ 'ችግር' አይደለም” ሲሉ በአፅንዖት ገልጸዋል።
የሆንግ ኮንግ እውነተኛው በረከት “በሃገሪቷ ላይ የሚያበራው የእግዚአብሔር ፊት” ነው ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ፥ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ሁል ጊዜ በሆንግ ኮንግ ላይ እንደሚያበራ እና ሆንግ ኮንግ ሁል ጊዜ በፊቱ እንደምትደሰት ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ በዚህ መንፈስ፣ ምዕመናን “ደፋር የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች” በመሆን “ለህብረተሰቡ ተስፋ እንዲያመጡ” አበረታተዋል።
ለሌሎች በረከት
በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ ባደረጉት ንግግር በሆንግ ኮንግ ውስጥ የሚገኝ ሰው በሙሉ ‘ለሌሎች በረከት’ የመሆን ችሎታ እንዳለው በመገንዘብ እነዚህን ‘በረከቶች’ እንዲያሳድጉ አበረታተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተለያዩ ዜግነት እና ማንነት ያላቸው ሰዎች እና ቡድኖች በተለያዩ ቋንቋዎች ማለትም በካንቶኒዝ፣ በፊሊፒንስ፣ ፈረንሳይኛ፣ ማንዳሪን፣ ኮሪያኛ እና በቬትናም ቋንቋዎች ለሆንግ ኮንግ መጸለያቸው ተነግሯል።
በአጥቢያው ሀገረ ስብከት ሳምንታዊ የሰንበት መርሃ ግብር መሠረት ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ በሆንግ ኮንግ ባደረጉት አጭር ቆይታ የፊሊፒንስ ሀገረ ስብከት የሃዋሪያዊ ሥራ አገልግሎት ማዕከል ውስጥ ከሚያገለግሉ ሁለት ገዳማዊያት እህቶች ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፥ ገዳማዊያቱ የስደተኞችን ውህደት ለማዳበር የተለያዩ ሃገረ ስብከት ቁምስናዎች እየሰሩ የሚገኙትን ተነሳሽነቶች እና ከዚህም በተጨማሪ ሀገረ ስብከቱ ከፊሊፒንስ ቆንስላ ጋር በመሆን ለጥገኝነት ጠያቂዎች እና ለስደተኞች ስላደረገው ድጋፍ ለብፁዕነታቸው አጋርተዋል።
ሆንግ ኮንግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፊሊፒንስ ማህበረሰብ መኖሪያ ስትሆን፥ ነሃሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ወደ 177,000 ፊሊፒናውያን በጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ እንደሚኖሩ ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት በርካታ ፊሊፒናዊያን ካቶሊኮች በክብረ በዓሉ ላይ መሳተፋቸው ተገልጿል።
በሆንግ ኮንግ ውስጥ ከሚገኙ ከ 7.4 ሚሊዮን በላይ ቋሚ ነዋሪዎች መካከል ከ400,000 በላይ የሚሆኑት ካቶሊኮች መሆናቸውን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።