ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ የሰውን ልጅ የሕይወት፣ የክብር እና የፍትህ ፍላጎት መካድ እንደማይቻል ገለጹ

የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ ማክሰኞ ጥር 5/2018 ዓ. ም. በዮርዳኖስ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኢራን እየተካሄደ ያለው የመንግሥት ተቃውሞ ወደ ዓመፅ እና ደም መፋሰስ እንደማይቀየር ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ የጋዛን ሙሉ በሙሉ ውድመትንም አውግዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በማንኛውም የሰው ልጅ ልብ ውስጥ የሕይወት፣ የሰብዓዊ ክብር እና የፍትህ ምኞት እንዳለ እናያለን” ያሉት የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ በዮርዳኖስ ከቫቲካን ዜና ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

ከታህሳስ ወር መጨረሻ ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በኢራን ባለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ምክንያት መንግሥትን በመቃወም ለሞት መዳረጋቸውን አስመልክተው እንደተናገሩት ሕዝቡ ለረጅም ጊዜ ሲሰቃይ መቆየቱን አስታውሰው ተጨማሪ ዓመፅ እና ደም መፋሰስ እንደማይኖር ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “የእያንዳንዱ ሰው እና ማኅበረሰብ ማንነት አካል የሆነው የሕይወት፣ የሰብዓዊ ክብር እና የፍትህ ፍላጎት መካድ ወይም ችላ ማለት አይቻልም” ብለዋል።

በቴራን የተቀሰቀሰ የሕዝብ አመጽ
በቴራን የተቀሰቀሰ የሕዝብ አመጽ

ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ በሐሺማቲ ውስጥ ወደ 60 ከሚጠጉ ብጹዓን ጳጳሳት እና ካኅናት ጋር ቀናትን የወሰደ ስብሰባ ያደረጉ ሲሆን፥ ከዚህ በፊትም በየሁለት ወይም በሦስት ዓመታ ውስጥ የሚያገለግሉባቸውን ቁምስናዎች በተመለከተ መረጃን ለመለዋወጥ እንደሚሰበሰቡ ይታወቃል። “በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የላቲን ሥርዓት የሚከተሉ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች በርካቶች እንደሆኑ እና በእያንዳንዱ አገር ያለው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

የጋዛን ሁኔታ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ፥ አካባቢው ሙሉ በሙሉ መውደሙን ተናግረዋል። ባለፈው የጥቅምት ወር የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም፣ በዚህም ምክንያት በአካባቢው ላይ የሚፈጸሙ የቦምብ ድብደባዎች ቢያቆሙም የታለሙ የእስራኤል ጥቃቶች በሕዝቡ ላይ ሞትን እና በንብረት ላይ ውድመትን ማስከተላቸውን ቀጥለዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

በታኅሳስ ወር ጋዛን ከጎበኙ በኋላ “በብርድ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በመድኃኒት እጥረትም ጭምር ሰዎች መሞታቸውን ቀጥለዋል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ፥ በዌስት ባንክ ያለውን ችግር በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ፈቃድ የሚከለከልበት፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የተወሳሰበበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸው፥ በሠፋሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በማኅበረሰቡ መሠረታዊ ነገሮች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ በቤተልሔም በተደረገው የዑደት ሥነ-ሥርዓት ላይ
ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ በቤተልሔም በተደረገው የዑደት ሥነ-ሥርዓት ላይ   (AFP or licensors)

በሁከቱ መካከል ዮርዳኖስ አስቸኳይ እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ከጋዛ ለሚመጡ ፍልስጤማውያን የሕክምና ዕርዳታ መስጠቷን እንደቀጠለች ገልጸው፥ በዮርዳኖስ ሁኔታው ​​የበለጠ የተረጋጋ እንደሆነ እና ግጭቱ ዮርዳኖስን በቀጥታ እንደማይጎዳ ነገር ግን በእርስ በርስ ግንኙነት፣ በንግድ እንቅስቃሴዎች እና በድንበሮች ምክንያት በተዘዋዋሪ መንገድ ሊጎዳት እንደሚችል አስረድተዋል።

ዮርዳኖስ የላቲን ሥርዓት ከሚከተሉ ግዛቶች መካከል ትልቁን አካባቢ የያዘች ስትሆን ይህም ራቅ ያሉ አካባቢዎችን ጨምሮ አብላጫ የሙስሊም ማኅበረሰብ በሚገኙባቸው ቦታዎች ውስጥ የሚገኙ 30 ትምህርት ቤቶችን እንደሚያካትት ታውቋል። “ይህ በአንድ መንገድ የማንነታችን መሠረት፣ ለልጆቻችን የክርስትናን ትምህርት መስጠት አስፈላጊ እና ከሰፊው የሙስሊም ማኅበረሰብ ጋር ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በዮርዳኖስ ውስጥ ያለችውን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ከሚያጋጥማት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ቀጣይነት ያለው የውስጥ ፍልሰት እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ፥ “ይህንን ሁሉ እንቅስቃሴ መከታተል እና ማኅበረሰባችን በሚንቀሳቀስበት እና አዲስ የሕይወት አውድ በሚፈጥርበት ቦታ መገኘት ከባድ ነው” ብለው፥ ይህ ደግሞ ለሐዋርያዊ የእረኝነት እንቅስቃሴ እንቅፋት እንደሚሆን ገልጸው፥ በክልሉ ውስብስብ የሆኑ ችግሮች ቢኖሩም ደህንነቱ ፍፁም የተጠበቀ በመሆኑ ምእመናን ወደ ቅድስት አገር የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ንግደት እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ ም ዕመናን ወደ ቅድስት ምድር ንግደት እንዲያደርጉ ሲያበረታቱ

“ቅድስት አገር አምስተኛ ወንጌል ናት” ያሉት ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ “እንዲሁም ስምንተኛ ምስጢራት ብዬ ልጠራው እወዳለሁ” ብለው ምክንያቱም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በአካል መገናኘትን ስለሚያስችል ነው” ብለዋል። “ሁሉም ሰው ቅድስት ምድርን ሳይጎበኝ ፍጹም ክርስቲያን ሊሆን እንደሚችል፣ ነገር ግን ወደ ቅድስት ምድር ከሄዱ የክርስትና እምነት የበለጠ ጠንካራ እና ተጨባጭ ይሆናል” ሲሉ አክለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከታኅሳስ 29-30/2018 ዓ. ም. ድረስ በጠሩት ልዩ የብጹዓን ካርዲናሎች ጉባኤ የሲኖዶሳዊነት እና የተልዕኮ ጭብጦች ላይ በማስተንተን እንደተናገሩት፥ ስለ ራሳችን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እና አዲስ የጋራ ጉዞን ለመጀመር ብጹዓን ካርዲናሎች በተሻለ ሁኔታ በመተዋወቅ በጋራ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ መወያየት መቻላቸውን ገልጸዋል።

 

14 Jan 2026, 15:07