ፈልግ

ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት እንደሆነ የሚታውቅ ሥፍራ  ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት እንደሆነ የሚታውቅ ሥፍራ  

ከዮርዳኖስ ማዶ የምትገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀባት ቢታንያ

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ዘንድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት መታሰቢያ በዓል ጥር 3/2018 ዓ. ም. ተከብሮ ውሏል። በዮርዳኖስ አል-ማግታስ በተካሄደ የአርኪኦሎጂ ቁፋሮዎች የቤተ ክርስቲያናት፣ የጸሎት ቤቶች፣ የማምለኪያ ዋሻዎች እና የመጠመቂያ ሥፍራዎች እንዲሁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ጋር የተያያዙ የአምልኮ ቦታዎች ፍርስራሾችም ተገኝተዋል። ይህ ቦታ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ መመዝገቡ ይታወሳል። ሦስት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሥፍራው መንፈሳዊ ንግደት ያደረጉ ሲሆን፥ እነርሱም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ነበሩ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከዮርዳኖስ ማዶ በምትገኝ ቢታንያ በተባለች ሥፍራ መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳጠመቀው በዮሐ. 1: 28 ላይ ተጠቅሷል። እንዲሁም በዮሐ. 10፡40 ላይ “ዮሐንስ መጀመሪያ ያጠምቅበት ወደነበረው ሥፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ እንደገና ሄደ፤ በዚያም ኖረ” ይላል።

“ከዮርዳኖስ ማዶ የምትገኝ ቢታንያ” በደብረ ዘይት ተራራ አቅራቢያ የምትገኘው እና ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ይጎበኛት የነበረች ቢታንያ ሳትሆን ነገር ግን ሌላ ቢታንያ ናት። ኦሪገን በ3ኛው ክፍለ ዘመን፣ ዮሐንስ ክሪሶስቶም በ4ኛው ክፍለ ዘመን እና የዚያ ዘመን ክርስቲያኖች “ከዮርዳኖስ ማዶ የምትገኝ ቢታንያ በጊዜው ቤታባራ በመባል የምትታወቅ እንደ ነበረች አፅንዖት ሰጥተዋል። ይህ ስም “ከዮርዳኖስ ማዶ የምትገኝ ቢታንያ” የሚለውን በትክክል የሚገልጹ አንዳንድ መረጃዎች በዮሐንስ ወንጌል ቅጂዎች ላይ ይገኛል (ዮሐ. 1: 28)። በተጨማሪም በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተነደፈው የማዳባ ካርታ ሥፍራው  የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ቦታ መሆኑን በዚህ መንገድ ይገልጻል። ቤታባራ በታልሙድ ውስጥም የተጠቀሰ ሲሆን ዛሬ ይህ ቦታ አል-ማግታስ በመባል ይታወቃል። ትርጉሙም በአረብኛ “ጥምቀት” ወይም “መዘፈቅ” ማለት ነው።

የአርኪኦሎጂ ማስረጃ

እስከ 4ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ክርስትና በሮማ ግዛት ውስጥ ብዙ ጊዜ ስደት ደርሶበታል። ኦፊሴላዊ የአምልኮ ቦታዎችን መገንባት አልቻለም ነበር። ያም ሆኖ የመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ሕይወት ጋር የተያያዙ ቦታዎችን ትዝታ ከትውልድ ወደ ትውልድ አስተላልፈዋል።

በ5ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ6ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ መካከል የባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት አናስታሲየስ ቀዳማዊ ዲኮረስ በመጥምቁ ዮሐንስ ስም የመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን አሁን አል-ማግታስ በመባል በሚታወቀው ቦታ ላይ ገነባ። ይህች ቤተ ክርስቲያን በጎርፍ እና በመሬት መንቀጥቀጥ ወድማ የነበረች ብትሆንም ብዙ ጊዜ እንደገና ተገንብታ ነበር። ነገር ግን ምናልባት በ7ኛው እና 8ኛው ክፍለ ዘመን ፍርስራሾች ብቻ ቀርተው ይሆናል።

በወቅቱ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ530 ዓ. ም. አካባቢ ቴዎዶሲየስ የተባለ አንድ ነጋዲ ስለዚያች ቤተ ክርስቲያኑ እንዲህ ሲል ጽፏል። “ከሙት ባሕር በስተሰሜን አምስት ማይል ርቀት ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ቦታ የብረት መስቀል የተገጠመበት አንድ ብቸኛ አምድ አለ። በንጉሠ ነገሥት አናስታሲየስ የተገነባው የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተ ክርስቲያንም አለ። ቤተ ክርስቲያኑ በዮርዳኖስ ወንዝ ጎርፍ ምክንያት በጣም ከፍ ያለ በትላልቅ ክፍሎች ላይ የተገነባ ነው።”

በዚህ ቦታ ላይ የቅድስት ሥላሴ ባዚሊካ የተገነባ ሲሆን ስሙም በኢየሱስ ጥምቀት ወቅት ቅድስት ሥላሴ የተገለጠበትን እውነታ የሚያስታውስ፥ እግዚአብሔር አብ ከሰማይ ሲናገር፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ከኢየሱስ ክርስቶስ በላይ በእርግብ አምሳል ይታያል። ምንም እንኳን ዛሬ ጥቂት ፍርስራሾች ብቻ የቀሩ ቢሆንም የአርኪኦሎጂ ቁፋሮዎች እንደሚያሳዩት ቢያንስ 27 ሜትር ርዝመት እና ከ15 ሜትር በላይ ስፋት ያለው ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ነበር።

ከእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በታችኛው የባዚሊካ ክፍሎች፣ የመናኒያን ዋሻዎች፣ ጸሎት ቤቶች፣ በትናንች የባልጩት ድንጋዮች የተሠሩ መንፈሳዊ ምስሎች፣ የእብነ በረድ ወለሎች እና ግዙፍ የመስቀል ቅርጽ ያለው የጥምቀት ሥፍራ መኖሩን ለይተው ያወቁ ሲሆን ሁሉም አሁን ከዮርዳኖስ ማዶ በምትገኝ ቢታንያ - አል-ማጋታስ በመባል በሚታወቀው ቦታ እርስ በርስ ቅርብ ሆነው የተገነቡ ናቸው።

በአል-ማጋታስ አቅራቢያ በተደረጉ ቁፋሮዎች ከነቢዩ ኤልያስ ጋር የተገናኘውን የኤል አል-ካርራርን ኮረብታ የተገኙ ሲሆን፥ በባይዛንታይን ዘመን ምናልባትም በ5ኛው ክፍለ ዘመን ለክብሩ ሲባል በእዚያ ሥፍራ ገዳም ተሠርቶለት እንደ ነበር ይገመታል።

ለሰው ልጅ እጅግ የላቀ ዋጋ የሆነ ሥፍራ

“ከዮርዳኖስ ማዶ የምትገኝ ቢታንያ (አል-ማጋታስ) አካባቢ ቴል አል-ካርራንን ጨምሮ እንደ ጎርጎሮሳያኑ በ2015 ዓ. ም. በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። በኦፊሴላዊው የድርጅቱ ድረ-ገጽ ላይ እንዲህ ተጽፎ ይገኛል። “‘ከዮርዳኖስ ማዶ የምትገኝ ቢታንያ’ ለአብዛኞቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ይህንን ቦታ የናዝሬቱ ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ የተጠመቀበት ቦታ አድርገው ተቀብለዋል። ይህ ማጣቀሻ ትውልዶች መነኮሳት፣ መናንያን፣ ምዕመናን እና ካህናት በቦታው እንዲኖሩ እና እንዲጎበኙ እንዲሁም ከ4ኛው እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ የአምልኮአቸውን እና ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶቻቸው ምስክርነቶች እንዲተዉ አበረታተዋቸዋል።

ከዮርዳኖስ ማዶ ወደምትገኝ ቢታንያ ንግደት ያደረጉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት

ከዮርዳኖስ ማዶ ወደምትገኝ ቢታንያ (አል-ማግታስን) ሐዋርያዊ ጉብኝት ያደረጉት የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሲሆኑ ይህም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የኢዮቤልዩ ዓመት በተከበረበት በ2000 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል። ቀጥሎም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2009 ዓ. ም. ቦታውን ጎብኝተው የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት የሚያስታውስ የቤተ ክርስቲያን ግንባታ ማስጀመራቸው ይታወሳል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ​​በ2014 ዓ. ም. ቦታውን ጎብኝተው በዮርዳኖስ ጥገኝነት ካገኙ የሶርያ እና የኢራቅ ስደተኞች፣ ከታመሙ ሕጻናትን እና የአካል ጉዳተኞች ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።

በሥፍራው አዲስ የታነጸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥር 2025 ዓ. ም. ተባርኮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል። በወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመወከል ሥነ-ሥርዓቱን የመሩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን እንደ ነበሩ ይታወሳል። ቤተ ክርስቲያኑ በአሁኑ ጊዜ በዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኝ ትልቁ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን፥ ሌሎችን የክርስትና እምነት ተከታዮች አብያተ ክርስቲያናትንም እንደሚገኙ ታውቋል።

 

12 Jan 2026, 16:52