የታኅሳስ 26/2018 ዓ.ም 4ኛ ስብከተ ገና ሣምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ምንባባት
1. ት.ኢሳያስ 7፡10-14
2. መዝ 23
3. ሮም. 1፡1-7
4. ማቴ 1፡18-24
የእለት ቅዱስ ወንጌል
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ታሪክ እንዲህ ነው፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳይገናኙ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ስለ ነበርና ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊተዋት ወሰነ። በዚህ ሐሳብ ሳለ፣ የጌታ መልአክ በሕልም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፤ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፤ እጮኛህን ማርያምን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፤ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና። ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና።”
ጌታ በነቢዩ እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ፤ “እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤” ትርጕሙም፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ማለት ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቃ፤ ከዚያም የጌታ መልአክ እንዳዘዘው ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት። ይሁን እንጂ የበኵር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ የተወለደውንም ሕፃን፣ “ኢየሱስ” ብሎ ጠራው።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
የስብከተ ገና አራተኛ እና የመጨረሻ እሑድ ላይ እንገኛለን። በዚህ ዕለት ከማቴ. 1: 18-24 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ይናገራል። ቅዱስ የሴፍ በዕድሜው ለጋብቻ የደረሰ ቅና ፍትሃዊ ሰው ነበር። ከዚህ አኳያ ስለ ወደፊት ሕይወቱ ምን እንደሚመኝ ወይም እንደሚያልም መገመት እንችላለን፥ ጥሩ ሰዎች እንደሚመኙት ሁሉ፣ ቅዱስ የሴፍም መልካም ቤተሰብ፣ አፍቃሪ ሚስት እና ብዙ ድንቅ ልጆች እንዲኖሩት እንዲሁም ጥሩ ሥራ እንዲኖረው እንደሚመኝ መገመት ይቻችላል። ነገር ግን በድንገት እነዚህ ሕልሞች የተለዩ እና ግራ የሚያጋቡ ገጠመኞችን ይዘው መጡ። ለእርሱ የታጨችው ማርያም ልጅ ትጠብቅ ነበር። ልጁም የእርሱ አይደለም! ይህ ሲሆን ዮሴፍ ምን ይሰማው ነበር? ድንጋጤ፣ ሕመም፣ ግራ መጋባት፣ ምናልባትም ብስጭት ተሰምቶት ይሆናል። ባጠቃላይ ዓለም እየፈራረሰ እንደሆነ ተሰማው! ነገር ግን ይህ በሆነበት ሰዓት ዮሴፍ ምን ማድረግ ነበረበት?
ሕጉ ለዮሴፍ ሁለት አማራጮችን ይሰጠዋል። የመጀመርያው ማርያምን መክሰስ እና ታማኝነትን በማጉደሏ ገንዘብ እንድትከፍለው ማድረግ ነው። ሁለተኛው ማርያምን ለከባድ መዘዝ ሳያጋልጣት የሚደርስበትንም ውርደት በመሸከም በድብቅ መተጫጨታቸውን መሻር ነው። ስለዚህ ዮሴፍ የምሕረት መንገድ የሆነው ይህን ሁለተኛውን አማራጭ መርጧል። በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆኖ ይህን ጉዳይ ሲያስብ፣ ሲያወጣ ሲያወርድ እያለ እነሆ እግዚአብሔር በዮሴፍ ልብ ውስጥ አዲስ ብርሃን እንዲበራ አደረገ። ማርያም ልጅ ለመውለድ የምትጠብቀው ለዮሴፍ ያላትን ታማኝነት በማጉደል ወይም በመካድ ሳይሆን ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደሆነ፣ የሚወለደውም ሕፃን የዓለም አዳኝ እንደሆነ ዮሴፍ በህልም ተነገረው። “እርሱ ይህን ሲያስብ ሳለ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለው ‘የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከእርሷ የተጸነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኝህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።’ (ማቴ. 1: 20-21) ማርያምም የመሲሑ እናት ትሆናለች እርሱም ጠባቂው ይሆናል። ዮሴፍ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የመሲሁ አባት ለመሆን ያላው ታላቅ ህልም ፍጹም ባልጠበቀው መንገድ ለእርሱ እየተፈጸመ መሆኑን ተረዳ።
ይህን ህልም እውን ለማድረግ ከዳዊት ዘር መወለድ እና ለሕጉ ታማኝ መሆን ብቻውን በቂ አልነበረም። ነገር ግን ከሁሉ በላይ ራሱን ለእግዚአብሔር አደራ መስጠት፣ ማርያምን እና ልጇን ከተጠበቀው በተለየ፣ ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ መቀበል ያስፈልገው ነበር። በሌላ አነጋገር፥ ዮሴፍ ሊያረጋጉት የሚችሉ እርግጠኝነቶቹን፣ እቅዶቹን እና ሕጋዊ ምኞቶቹን በመተው፣ ሙሉ በሙሉ ሊገለጥ ላለው የወደፊት ጊዜ እራሱን ክፍት ማድረግ ይኖርበታል። እናም ዮሴፍ እቅዱን በሚቀይር እና ታማንነቱን በሚጠይቀው በእግዚአብሔር ፊት ስምምነቱን ገልጿል። ዮሴፍ ደፋር እና ዝምታን የሚመርጥ፥ ድፍረቱም ምንም ተጨማሪ ዋስትናን ሳይጠይቅ በእምነት መቀበል እና ፈቃደኛ መሆን ነው።
ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ቅዱስ ዮሴፍ ዛሬ ለእኛ ምን መልዕክት ይነግረናል? እኛም ህልሞች አሉን፣ ምናልባት ስለ ህልሞቻችን ብዙ እናስብ ይሆናል። በብርሃነ ልደቱ ወቅትም ስለ ህልሞቻችን እንነጋገር ይሆናል። ምናልባት ያልተሳኩ ሕልሞቻችንን በማሰብ እናዝን ወይም እንጨነቅ ይሆናል። የምንጠብቀው ወይም ተስፋ የምናደርገው ነገር ብዙውን ጊዜ ካልተጠበቁ እና ግራ ከሚያጋቡ ሁኔታዎች ጋር አንድ ላይ መሆን እንዳለባቸው እናያለን። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ቅዱስ ዮሴፍ መንገዱን ያሳየናል። ያሰብነው ሳይሳካ ሲቀር ቁጣ ወይም ብቸኝነት በመሳሰሉ አሉታዊ ስሜቶች መሸነፍ የለብንም። ይህ የተሳሳተ መንገድ ነው! ይልቁንስ አስደናቂ ነገሮችን፣ በሕይወት መካከል የሚያጋጥሙ አስገራሚ ነገሮችን እና ችግሮችን በትኩረት ተመልክተን መቀበል አለብን። ችግሮች ሲያጋጥሙን ፈጣን ውሳኔዎችን ማድረግ ወይም በደመ ነፍስ መወሰን የለብንም። ነገር ግን ቅዱስ ዮሴፍ እንዳደረገው ማሰብ እና ሁሉን ነገር መለየት ያስፈልጋል። (ማቴ. 1: 20) እራሳችንን በእግዚአብሔር ምሕረት እርግጠኝነት ላይ መመሥረት አለብን። አንድ ሰው በችግር ወቅት ራሱን ለብቸኝነት ሳያጋልጥ፣ ለቁጣ እና ለፍርሃት እጅ ሳይሰጥ፣ ነገር ግን ለእግዚአብሔር በሩን ክፍት አድርጎ የሚጠብቅ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ጣልቃ ሊገባበት ይችላል። እርሱ ችግሮችን ወደ ህልም የመቀየር ጥበብ አለው። ከዚህ በፊት አስበነው በማናውቀው መንገድ፣ ምናልባትም እኛ እንደምንጠብቀው ሳይሆን እርሱ በሚያውቀው ሌላ መንገድ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚችል ያውቃል። ስለሆነ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እነዚህ አስገራሚ የእግዚአብሔር እይታዎች እኛ መገመት ከምንችለው በላይ ታላቅ እና ውብ ናቸው!
በዚህ በአራተኛውና በመጨረሻው የስብከተ ገና ሰንበት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ማቴ 1፡18-24) በሁለተኛ ደረጃ ዮሴፍ ያስቀመጠውን እቅድ ተሞክሮ በመመርመር ክርስቲያኖች ሁሉ በእርሱ ጥበባዊ አመለካከት ተሞለተው ወደ ገና በዓል እንዲያመሩ ያደርጋል። እርሱ ከአጥማቂው ዮሐንስ እና ከማርያም ጋር በእዚህ በስብከተ ገና ሰሞን ስረዓተ አምልኮ ውስጥ እንዲካተት ከተደረጉ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው፣ ሦስቱም ትክክለኛ የነበሩ ሰዎች ናቸው። የማይሰብክ ሰው አይናገርም፣ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ይሞክራል። በቅዱስ ወንጌል መንገድ በመጓዝ እና በብጽዕና ይህም “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው ፣ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ናትና” (ማቴ 5፡ 3) የተባለውን በተግባር ይፈጽማል። ዮሴፍ በጣም ድሃ የነበረ ሰው ነበር፣ ምክንያቱም እሱ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ብቻ በሟሟላት ይኖር የነበረ ሰው ነው፣ ይህ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ መታመን እንደ ሚገባቸው ጠንቀቀው የሚያውቁ እና መተማመናቸውን በእርሱ ላይ ብቻ ያደረጉ ሰዎች የሚያሳዩት ድህነት ነው።
የዛሬው ቅዱስ ወንጌል በሰው ልጅ አመለካከት ሲታይ የሚያሳፍር እና የሚጋጭ ሁኔታን ያቀርባል። ዮሴፍ እና ማርያም ታማኝ እጮኛሞች ነበሩ። እነሱ ገና አብረው መኖር አልጀመሩም ነበር፣ ነገር ግን እርሷ በእግዚኣብሔር ድንቅ ሥራ የተጸነስ አንድ ልጅ በመጠባበቅ ላይ ነበረች። ዮሴፍ በዚህ ፊት ለፊቱ በተጋረጠበት አስገራሚ ሁኔታ ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ ተጨንቆ ነበር፣ የተፈጠረውን ነገር ስሜታዊ በሆነ መልኩ እና መቀጣጫ በሆነ መልኩ ለክስተቱ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሰብዓዊ መብትን ከግምት ባስገባ መልኩ እና ተወዳጅ እጮኛው የነበረችውን ማርያምን ባካተተ መልኩ መፍትሄ ይፈልጋል። ቅዱስ ወንጌል “እጮኛዋ ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ስለ ነበርና ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊተዋት ወሰነ” (ማቴ 1፡19) በማለት ይናገራል። በእውነቱ ዮሴፍ በሁኔታው የተነሳ ማርያምን ከሱዋት ቢሆን ኖሮ በእርሷ ላይ ከባድ መዘዞች እንደ ሚከተሉ፣ አልፎ ተርፎም እስከ ሞት ድረስ የሚያደርሳት ተጋላጭነት እንደ ሚያጋጥማት በደንብ ይገነዘባል። እርሱ እጮኛ አድርጎ በመረጣት በማርያም ላይ ሙሉ እምነት አለው።
ሆኖም ይህ ሁኔታ በእዚህ እንዳለ አሁን የተፈጠረው በቃላት ሊገለጽ የማይቻል ሁኔታ የነበራቸውን ግንኙነት እንዲጠራጠሩ ያደርጋቸዋል፤ ስለሆነም በሁኔታው የተነሳ ታላቅ ስቃይ ውስጥ የገባ ሲሆን በማርያም ላይ ከፍተኛ የሆነ አደጋ በማያስከትል መልኩ ከእርሷ ለመራቅ ወሰነ። ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ እርሱ ማለትም ዮሴፍ ለራሱ ያቀረበው የመፍትሄ ሐሳብ የእግዚኣብሔር ፈቃድ እንዳልሆነ ጣልቃ በመግባት ይነግረዋል። በተቃራኒው ጌታ ለእርሱ የኅብረት ፣ የፍቅር፣ የደስታ እና አዲስ አንድነት መፍጠር የሚያስችል መንገድ ይከፍታል-“የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፤ እጮኛህን ማርያምን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፤ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና” (ማቴ 1፡21) በማለት ይነግረዋል።
በዚህ ጊዜ ፣ ዮሴፍ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔርን አመነ፣ ለመላእክቱ ቃል በመታዘዝ ማርያምን ወሰዳት። በትክክል ይህ በእግዚአብሄር ላይ የነበረው የማይለዋወጥ መታመን በሰው ልጅ አስተሳሰብ አስቸጋሪ እና ለመረዳት አዳጋች የሆነውን ሁኔታ እንዲገነዘብ ፈቃድ ሰጥቶታል። በማርያም ማህፀን ውስጥ ተጸንሶ የሚገኘው ሕጻን ልጅ የእርሱ ልጅ አለመሆኑን በእምነት አማካይነት የተረዳ ሲሆን ነገር ግን ልጁ የእግዚኣብሔር ልጅ መሆኑን አውቆ እርሱ ማለትም ዮሴፍ ምድራዊ አባቱ በመሆን ሙሉ በሙሉ ለሕጻኑ እንክብካቤ እንደ ሚያደርግ ተረዳ። ይህ የዋህ እና ጥበበኛ የሆነ ሰው ያሳየን መልካም አብነት እይታችንን ከፍ እንድናደርግ እና አሻግረን እንድንመለክት ያሳስበናል። ራሳችንን አዲስ ለተከፈተው አድማስ ለክርስቶስ እና ለቃሉ ክፍት በማደረግ ከትናንሽ ይሁን ከትላልቅ ስሌቶች በጣም ሩቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን አስገራሚ አመክንዮ መልሶ የመቀበል ጉዳይ ነው።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ንጹህ የሆነው እጮኛው ዮሴፍ፣ የሚመጣውን ኢየሱስ ለማዳመጥ፣ እንዲሁም በራሳችን እቅዶስች እና በምርጫዎቻችን ውስጥ ሳይቀር እርሱን እንድንቀበል እንዲረዱን ልንማጸናቸው ይገባል።
ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንስኮስ በታኅሳ 12/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደርጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ ነው።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን