በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ገዳማዊያት እህቶች ህፃናትን በርህራሄ በተሞላ ተልዕኮ እያገለገሉ እንደሚገኝ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የቅዱስ ቪንሴንት ማህበር አባቶች የሩሲያ ከተማ ወደ ሆነችው ኒዚንጅ ታጊል ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ክርስቲያኖች ለማገልገል ወደ ከተማዋ የዘለቁት እ.አ.አ. በ 1997 ዓ.ም. ሲሆን፥ በአከባቢው የተራቡ ህፃናትን በመርዳት የተጀመረው ተልዕኮዋቸው በሂደት ለረጅም ጊዜ የቆየ የርኅራኄ አገልግሎት ወደመሆን ተሸጋግሯል።
ከስሎቫኪያ የመጡት የቅዱስ ቪንሴንት ዴ ፖል የበጎ አድራጎት ሴት ልጆች ማህበር አባል የሆኑት እህት አንቶኒያ ሌድኒካ በ30 ዓመታት የገዳም ህይወታቸው ውስጥ በሩሲያ ለ23 ዓመታት አገልግለዋል።
ወደ ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጡት አባቶች ውስጥ አንዱ የሆኑት አባ ቶማዝ ማቭሪች በረሃብ እና በብርድ የተጠቁ እንዲሁም የተረሱ ህፃናት ልጆች በመንገድ ላይ ሲዘዋወሩ በማየታቸው እና በዚህም ችግር ልባቸው በመነካቱ ጉዳዩን ከምዕመናን ጋር መወያየታቸውን፥ ቀጥሎም በስፍራው ከነበረው ትምህርት ቤት ዋና አስተዳዳሪ ጋር በመነጋገር እና ከካቶሊክ ሰበካዎች እና ከመንግስት ተቋማት ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎችን መጀመራቸውን በመግለጽ የጉባኤውን አመሰራረት እህት አንቶኒያ አስታውሰዋል።
በዚህም ሁኔታ ገዳማዊያቱ ምሳ መግዛት ለማይችሉ ህፃናት ትኩስ ምግብ ማቅረብ እንደጀመሩ፥ ይህም ፍቅር እና እምነት በተግባር ወደሚታይበት ፕሮግራም መሸጋገሩ የተገለጸ ሲሆን፥ በወቅቱ ምዕመናን እና ካህናት ከ 50 እስከ 80 ለሚሆኑ ህፃናት የትምህርት ቤት ምሳ በመክፈል የእርዳታ ሥራው እንደተጀመረ አስታውሰዋል።
በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ የበጎ አድራጎት ሴት ልጆች
ይሄንንም ተከትሎ አባ ቶማዝ እህቶች ወደስፍራው መጥተው እንዲያገለግሉ መጠየቃቸውን ያስታወሱት እህት አንቶኒያ፥ እርሳቸው እ.አ.አ. በ 2000 ዓ.ም. ከስሎቫኪያ መጥተው በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአካባቢ ልጆች መጠሊያ እና ሁለተኛ ቤት በሆነው የህፃናት እንክብካቤ መስጫ ክለብ ውስጥ አገልግሎት መጀመራቸውን ገልጸው፥ ከሳምንታዊ ስብሰባዎች ጀምሮ በአሁኑ ወቅት በየሳምንቱ ለአምስት ቀናት በማገልገል ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
እህት አንቶኒያ ከ1,500 በላይ ህፃናት ከዚህ ክለብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ለአንዳንዶች ቆይታቸው አንድ ዓመት ብቻ ሲሆን ለሌሎች ግን ሙሉ የትምህርት ህይወታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
የክለቡ ዋና ተልዕኮ ምንም ለሌላቸው ልጆች ፍቅር፣ መረጋጋት እና መመሪያ መስጠት እንደነበር የገለጹት እህት አንቶኒያ፥ አብዛኞቹ ህፃናት አማኞች እንዳልነበሩ እና ቀስ በቀስ ኦርቶዶክሶችንም ሆነ ሙስሊሞችን መርዳት መጀመራቸውን አስታውሰው፥ ነገር ግን የሃይማኖት ጉዳይ አጀንዳቸው እንዳልነበረ እና ገዳማዊያቱ ለህፃናቱ ማሳየት የፈለጉት አንድ ሰው እንደሚወዳቸው ለማረጋገጥ ብቻ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኡሊያና ምስክርነት
የማዕከሉ ተጠቃሚ የነበረችው የ34 ዓመቷ ኡሊያና የልጅነት አስደሳች ትዝታዎች እንዳልዋት በማስታወስ’ የቪንሴንሺያኖቹን እንክብካቤ ያረጋገጠች ሲሆን፥ ‘ሁላችንም በክረምት ወራት ተራራ ላይ ለመንሸራተት ከገዳማዊያቱ ጋር በጋራ አብረን እንሄድ ነበር፥ በዚህም ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ደስተኛ ነበርኩ’ ብላለች።
“ከተፋቱ ቤተሰብ ነው የመጣሁት” ያለችው ኡሊያና፥ ይህም በመሆኑ ደግነትን እና ፍቅርን ከቤተሰቧ እንዳልተማረች ጠቁማ፥ ነገር ግን ማዕከሉ በሥነ ምግባር እንድታድግ እንደረዳት ብሎም የፈጠራ ችሎታዋን እና ክህሎቷን እንዳሳደገላት፥ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት ንድፍ አውጪ እንደሆነች እና የህፃናት መርጃ ማዕከሉን ከልብ እንደምታመሰግን ገልፃለች።
ሰፋ ያለ ተልዕኮ
የበጎ አድራጎት ሴት ልጆች ማህበር ከዚህም በተጨማሪ በኒዚንጅ ታግል ከተማ ውስጥ የሚገኙ ቤት አልባ ሰዎችን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፥ በየቀኑ በአካባቢው የሚገኙ መጠለያዎችን በመጎብኘት የንፅህና ቁሳቁሶችን በማቅረብ እና ቤት የሌላቸው ሰዎች የሚኖሩባቸውን ሕንፃዎች መልሶ በመገንባት እንደሚረዱ ተገልጿል።
ከዚህም ባሻገር ገዳማዊያቱ በሃገሪቱ የሳንባ ነቀርሳ ህክምና መስጫ ሆስፒታል ውስጥም እንደሚያገለግሉ የገለጹት እህት አንቶኒያ፥ ወደዚህ ሆስፒታል የሚመጡት በርካታ የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች ቤት የሌላቸው እና ምንም ሰነድ የሌላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ምክንያት ማህበራዊ ጥቅማጥቅሞችን እንዲያገኙ ወይም ከሆስፒታሉ ከወጡ በኋላ ወደ ሌሎች ተቋማት እንዲዛወሩ ህጋዊ ሰነዶችን እንዲያገኙ እንደሚረዷቸው እና ገዳማዊያቱ መኪናዎቸውን ተጠቅመው ህሙማኑን ወደተለያዩ ቢሮዎች በማጓጓዝ እና ሁሉንም ወጪዎች በመሸፈን እንደሚረዱ አስረድተዋል።
ገዳማዊያቱ ለታካሚዎች መደበኛ የህክምና ምርመራ እንዲያደርጉ ለማበረታታት በወር አንድ ጊዜ ለሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች ምግብ የሚሰጡ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ በየደብሩ ለሚገኙ ምዕመናን የሃዋሪያዊ አገልግሎት እና ትምህርተ ክርስቲያን እንደሚሰጡ፣ እንዲሁም በዓመት ውስጥ ብዙ ጊዜ በተለያዩ አጋጣሚዎች እና በዓላት ከምዕመናን ጋር ስብሰባ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ የተደረገ ድጋፍ
የገዳማዊያቱ የበጎ አድራጎት ፕሮግራሞች ስሎቫኪያ ከሚገኘው የቅዱስ ቪንሰንት ማህበር ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን፥ እንዲሁም በየዓመቱ የ‹ቅዱስ ቪንሴንት ቦርሳ› ተብሎ በሚካሄደው የምግብ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ወቅት ከአካባቢው ሰዎች በሚያገኙት የገንዘብ ስጦታዎች ፕሮግራሞቻቸውን እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።
“የሚሰበሰበው ምግብ ለድሆች እንደሚውል ስለሚያውቁ ህዝቡ ከልቡ ይለግሳል” ያሉት እህት አንቶኒያ፥ የገና፣ የትንሳኤ እና የአረጋውያን የክብር ቀንን የመሳሰሉ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት ልገሳ እንደሚያሰባስቡም ጭምር ገልጸዋል።
ኦምስክ ከተማ የሚገኙ ገዳማዊያን
የኖቮሲቢርስክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጆሴፍ ቨርዝ እ.አ.አ. በ 2010 ዓ.ም. ገዳማዊያት እህቶችን ወደ ኦምስክ ከተማ እንዲመጡ መጋበዛቸው የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም በሳይቤሪያ ከተማ ውስጥ የቪንሴንሺያን እህቶች በሁለት ደብሮች ውስጥ ለህፃናት እና ለአዋቂዎች ትምህርተ ክርስቶስን በማስተማር እያገለገሉ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ለበጎ አድራጎት ሰራተኞች፣ ቤተሰቦች እና ልጆች መንፈሳዊ እርዳታ በመስጠት፥ እንዲሁም በኦምስክ በሚገኘው የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ቤት የሌላቸውን እና የሳንባ ነቀርሳ ህሙማንን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።
እህት አንቶኒያ ከካህናት ጋር በመሆን ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ በሚራራቁ በዙሪያው ወደሚገኙ ደብሮች ሄደው እንደሚያገለግሉም ጭምር አስታውሰዋል።
ደስታ እና የህይወት ትግል
እህት አንቶኒያ በማህበረሰባቸው ውስጥ ስላለው ጥልቅ የሆነ የህይወት ትግል እና በጸጥታ የተሞላ ተስፋ፣ ፍርሃት፣ ድህነት እና የቤተሰብ ችግሮች የማያቋርጡ ተግዳሮቶች ሆነው መቀጠላቸውን አስታውሰው፥ የካቶሊኮች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም፣ በስፍራው የሚገኙ እህቶች ሁሉንም ሰው በግል እንደሚያውቁ እና በአንድ ወቅት ያገለግሉዋቸው የነበሩት ልጆች አድገው ሲያዩ ታላቅ ደስታ እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
ከሃያ ዓመታት በላይ በሩሲያ ውስጥ የሚገኙት የቅዱስ ቪንሴንት ገዳማዊያት እህቶች ተልዕኮ በትናንሽ የፍቅር ድርጊቶች እና በእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳሳ ተልዕኮ መገኘት ላይ የተመሰረተ እንደሆነም ተገልጿል።