ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ቤተሰቦችን በተራራማ መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በመጎብኘት በጸሎታቸው አጋርነታቸውን ሲያሳዩ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ቤተሰቦችን በተራራማ መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በመጎብኘት በጸሎታቸው አጋርነታቸውን ሲያሳዩ  

በታይላንድ፥ ቺያንግ ማይ ከተማ መንደሮች ውስጥ የሚያገለግሉ ሚሲዮናዊያን በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ ተገለጸ

በሰሜናዊ ታይላንድ ከሚገኙት የሩዝ ማሳዎች እና ቤተመቅደሶች መካከል፣ የኢደንቴ ሚሲዮናውያን በየመንደሩ ከሚገኙ ቤተሰቦች ጋር አብረው የሚኖሩ ሲሆን፥ ገዳማዊያቱ ከማህበረሰቡ ጋር የጋራ ሕይወታቸውን ከወንጌል እና ከአካባቢው ባህሎች ጋር በማመሳሰል ለተሻለ ነገር እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከእነዚህም መካከል ዮሳያ የተባለች ሚስዮናዊት እንደተናገረችው በቁጥር አነስተኛ መሆናቸውን ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ ሰውን ማዳመጥ ብቻ በጣም ጥልቅ የሆነ የወንጌል ስብከት እንደሆነ አስረድታ፥ በታይላንድ ውስጥ እያገለገለ የሚገኘው የኢደንቴ ተልዕኮ በካረን፣ ላሁ፣ አካሃ፣ ህሞንግ እና ሊሱ መንደሮች ውስጥ ከሚገኙ ህዝቦች ጋር እየሰራ ያለውን በርካታ ሥራዎች አንስተው አብራርተዋል።

በእነዚህ መንደሮች ውስጥ ያለው ህይወት በዕለት ተዕለት ሥራዎች እና ሊገመት በማይችል የግብርና ስርዓት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ወጣቶች ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ቀደም ብለው ከትምህርት ገበታ የሚለቁ እንደሆነ፥ እንዲሁም አረጋውያን እና ህፃናት ለአየር ንብረት ብክለት፣ ለጎርፍ አደጋ እና ለተለያዩ አደጋዎች የተጋለጡ መሆናቸው ተገልጿል።

በዚህ ሁሉ ተግዳሮት መካከል የቡድሂስት እምነት ተከታዮች በሚበዙባት ሃገር ውስጥ በቁጥር አናሳ የሆኑ ካቶሊኮች መኖር ርህራሄን፣ ትኩረትን እና በሰላም አብሮ የመኖርን ባህል ያሳድጋል ተብሏል።

ወጣት ቤተክርስቲያን
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የወንጌሉ አዋጅ ወደ ሰሜናዊ ታይላንድ የተስፋፋ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተራራማ አከባቢ የሚኖሩ የአከባቢው ጎሳዎች ከወንጌል ጋር ሥር የሰደደ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።

በአሁኑ ወቅት በአከባቢው የካቶሊኮች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም፥ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ሚስዮናዊ ለመሆን የመረጠች ሲሆን፥ ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ያለው ግንኙነት በይፋዊ ግንኙነቶች ብቻ የተገደበ ሳይሆን ትናንሽ የግብርና፣ የጤና አጠባበቅ እና ትምህርታዊ ፕሮጀክቶች የተለያየ እምነት ካላቸው ሰዎች የቤተሰብ ሕይወት ጋር የተሳሰሩ የጋራ ቦታዎች በሆኑበት መንደሮች እና ትምህርት ቤቶች ውስጥም በመገኘት በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ቤተክርስቲያኗ በበዓላት፣ በሙዚቃ ዝግጅቶች እና በተለያዩ የአካባቢው ባህላዊ ዝግጅቶች ላይ የምትሳተፍ ሲሆን፥ ቤተክርስቲያኗ በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ የምትሳተፈው የአከባቢውን ማህበረሰብ ባህልና ወግ ለመተካት ሳይሆን ወዳጃዊ አቀራረብን በመምረጥ ማህበራዊ ትስስርን ለመጠበቅ እና ለማጠናከር እንደሆነ ተገልጿል።

የኢዴንቴ ሚሲዮናዊያን ካህን የሆኑት አባ ቲናኮርን በአከባቢው የምትገኘው ቤተክርስቲያን በታይላንድ ቋንቋ የሚመለክባት መሆኑን ገልጸው፥ ነገር ግን ሰዎች በቋንቋቸው መልስ እንደሚሰጡ እና መዝሙሮችም ምንም ትርጉም የማይፈልጉትን መንፈሳዊነት እንደሚያስተላልፉ የገለጹ ሲሆን፥ ሥርዓተ ቅዳሴ እና ትምህርተ ክርስቲያን ብዙውን ጊዜ የሚጠነክሩት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን በመጠቀም እና ለጎሳ ባህሎች ትኩረት በመስጠት እንደሆነ አብራርተዋል።

አብዛኛዎቹ ምዕመናን ጠንካራ የማህበረሰብ ስሜት ያላቸው የካረን፣ የላሁ፣ የአካህ፣ የሆሞንግ እና የሊሱ ጎሳ አባላት ሲሆኑ፥ ይህም ለክርስቲያናዊ አስተምህሮ ምቹ እንደሆነ እና ተልዕኮው በዋና ከተማው ውስጥ ያለው አገልግሎቱ ከዚህ የተለየ እንደሆነ ተነግሯል።

ክሪስቲና የተባሉ ሚሲዮናዊ በበኩላቸው በርካታ ወጣቶች ያለምንም ድጋፍ ብቻቸውን እንደሚመጡ ገልጸው፥ ዋነኛው የወጣቶቹ ፍላጎት ከልብ የሚያዳምጣቸው ሰው ማግኘት እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን፥ በቂ የሆነ የምግብ አቅርቦት ባይኖርም፥ ለወጣቶቹ የትምህርት ዕድል አግኝተው እንዲማሩ እና እንዲያድጉ እድል መስጠቱ አመኔታን ወደነበረበት ለመመለስ መንገድ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ተስፋን ማጣት ትክክለኛ መከራ መሆኑ 
ዮሳያ ስለአንዲት “ትምህርቷን ለመቀጠል የምትፈልግ ነገር ግን ቤተሰቧን ለመርዳት ትምህርቷን ማቋረጥ ግድ ስለሆነባት የ 14 ዓመት ታዳጊ ታሪክ አስታውሰው፥ ይህ ሁኔታ ‘ድህነት የገንዘብ እጦት ብቻ ሳይሆን የዕድል እና የወደፊት ተስፋ እጦት’ መሆኑንም ጭምር እንድረዳ አድርጎኛል” ብለዋል።

‘ተስፋ የለሽ መሆን እውነተኛው መከራ ነው’ ያሉት ዮሳያ፥ በመንደሩ ውስጥ የሚገኙ ህፃናት ያላቸውን ነገር እንደሚጋሩ እና ጎረቤቶች በችግሮቻቸው ውስጥ እርስ በርሳቸው እንደሚደጋገፉ፥ ሆኖም ግን የቋሚ ሥራ እጦት፣ የስደት፣ ወጣቶች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ መገደድ፣ አረጋውያን እና ህፃናት በአየር ንብረት ብክለትና በተፈጥሮ አደጋዎች መሰቃየትን ጨምሮ በርካታ አስተማማኝ ያልሆኑ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቁመው፥ እዚህ ያለው ድህነት የማይቻሉ ምርጫዎች እና የአስቸጋሪ ህይወቶች ተጨባጭ ገጽታ እንደሆነ አስረድተዋል።

ወደ መልካም ነገር የሚቀየሩ ቁስሎች
ኤስተርሊሺያ የተባሉ ሌላኛዋ ሚስዮናዊት ሁለት ልጆቻቸውን በሞት ስላጡ አረጋዊያን ባልና ሚስት ታሪክ በማስታወስ፥ አረጋዊያኑ መጀመሪያ አከባቢ ማንንም ማየት እንዳልፈለጉ፥ ማዕከሉን መጎብኘት ከጀመሩ በኋላ ግን ቀስ በቀስ ፈገግ ማለት እንደጀመሩ አስታውሰው፥ በተመሳሳይ ሁኔታ ሚስዮናውያኑ ቀለል ባሉ አቀራረቦችች ወደ ሰዎች በመቅረብ እንደሚያዳምጧቸው ብሎም ክብርን እና ድፍረትን የሚያድስ ታማኝ ወዳጅነትን እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

አዛኝ ልብ
በሰሜናዊ ታይላንድ በምትገኘው ቺያንግ ማይ ከተማ ያለው ተልዕኮ የእርስ በርስ ግንኙነቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ የሃዋሪያዊ ሥራ እንቅስቃሴው በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎች እና በጤና አጠባበቅ ማዕከላት እንዲሁም በግብርና ፕሮጄክቶች እና በተራራማ አከባቢዎች የሚኖሩ ጎሳዎች ውስጥ የሚካሄዱ የልማት ፕሮግራሞች ከሆኑት ማህበራዊ እና በጎ አድራጎት ቁርጠኝነቶች ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ልዩ እንክብካቤ የሚደረገው ለድሆች፣ ለስደተኞች፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች እና ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እንደሆነ ተነግሯል።
በካቶሊኮች፣ በቡድሃ እምነት ተከታይ መነኮሳት፣ በሙስሊሞች እና በአኒሚስት ማህበረሰቦች መካከል የሚደረግ ውይይት የዕለት ተዕለት እና ተፈጥሯዊ ክስተት ሲሆን፥ ይህ ውይይት የአካባቢ ጥበቃን፣ ሰላምን እና ትምህርትን የሚደግፉ የጋራ ተነሳሽነትን እንደሚያስከትል ተገልጿል።

“በእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል መኖር፥ ማገልገል ማለት ተግባራዊ ህይወትን በማስተማር ብቻ ሳይሆን በርኅራኄ በተሞላ ልብ መቅረብ ማለት እንደሆነ እንድንገነዘብ አድርጎናል” ሲሉ ሚሲዮናዊያኑ ያስረዳሉ።

የትህትና ኃይል
የኢዴንቴ ሚሲዮናውያን ቺያንግ ማይ ከተማ ከደረሱ ከ23 ዓመታት በኋላ በዝምታ እና በፅናት መገኘታቸውን በትህትና እና ቀላል በሆነ መንገድ ማቅረባቸውን የቀጠሉ ሲሆን፥ ቲናኮርን ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት ‘ጥቃቅን ነገሮችም እንኳን ቢሆኑ ምንጊዜም ለታናናሾች ቅርብ የሆነውን አምላክ ስለሚመሰክሩላቸው ትልቅ ዋጋ እንዳላቸው’ ገልጸው፥ የዋህ እና ሩህሩህ ልብ ሲኖረን የእግዚአብሔርን ፍቅር የመረዳት እና እንደ አንድ የአምላክ ልጆች የመኖር መንገድ እንደሆነ መረዳታቸውን በመግለጽ አጠቃለዋል።

18 Dec 2025, 13:39