በሊባኖስ አብሮ የመኖር እና የመደጋገፍ ምልክት የሆነው ቅዱስ ቻርቤል ማክሎፍ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በደብረ ሊባኖስ ጅቤይል ክልል ውስጥ በ1200 ሜትር ከፍታ ላይ ካለው ኮረብታ ጫፍ ላይ፣ የሜዲትራኒያንን ባህርን በቅርብ ርቀት ማየት በሚቻልበት ቦታ ላይ በአናያ ከተማ የቅዱስ ቻርቤል ማክሎፍ ማረፊያ የሚገኝበት የቅዱስ ማሮን ገዳም ይገኛል።
እ.አ.አ. ከ1828 እስከ 1898 ዓ.ም. የኖሩት እኚህ ሊባኖሳዊ ማሮናዊ መነኩሴ እና ባህታዊ እጅግ በጣም የተቀደሱ እና ለእግዚአብሔር ያደሩ ህይወትን ሲኖሩ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፥ ዛሬ በአማላጅነታቸው ምክንያት በርካታ ተዓምራዊ ፈውሶችን በማድረግ በክርስቲያኖች እና በካቶሊኮች ብቻ ሳይሆን በሙስሊሞች እና በሌሎች እምነት ተከታዮች ዘንድም ክብርን አስገኝቶላቸዋል።
በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የዚህን ቅዱስ ማረፊያ ስፍራ የሚጎበኙ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሊባኖስ በሚያደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞዋቸው ህዳር 22 በቅዱስ ቻርቤል መቃብር ሥፍራ ላይ ተገኝተው የጸሎት ሥነ ስርዓት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠባቃል።
በገዳሙ ውስጥ ከሚኖሩት 16 የማሮናዊት መነኮሳት መካከል አንዱ የሆኑት አባ የሱፍ ማታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት ለሊባኖስ እንደ ሀገር፥ ለመካከለኛው ምስራቅ እና ለመላው ዓለም ብሎም የተለያዩ ግጭቶች ላሉባቸው አከባቢዎች ደግሞ ከመከፋፈል እና ከሙስና መፈወስን፥ እንዲሁም ከቅዱስ ቻርቤል የአካላዊ ፈውስ ተስፋን ወደ ሙሉ ፈውስ ተስፋ እንደሚያሸጋግር አስረድተዋል።
ቅዱስ ቻርቤል በሊባኖስ የተለያዩ ሃይማኖቶች በጋራ አብሮ የመኖርን ባህል የሚያጠናክር እና የመረዳዳት ምልክት መሆኑን የገለጹት ካህኑ፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት “ቅዱስ ቻርቤል በዓለም ላይ ያለውን ሚና የሚያሳይ ታሪካዊ እውቅና እንደሆነ እና በችግር ላይ ላለችው ሀገር ደግሞ የድጋፍ እና የተስፋ መልእክት ነው እንደሆነም ጭምር አስረድተዋል።
“ለሰው ልጆች ተዓምር ሰሪ”
አባ የሱፍ የቅዱስ ቻርቤል ‘ሃይማኖታዊ ውበት’ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳሉ ገልፀው፥ የመጀመርያው በአማላጅነቱ የተገለጹት በርካታ ተዓምራዊ ፈውሶች ሲሆኑ እነዚህም “በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ምንም ልዩነት እንደሌለው እንደ መለኮታዊ ጣልቃገብነት ተቆጥረዋል ሲሉ በአጽንዖት ከገለጹ በኋላ፥ ተጨባጭ ውጤቱ ጸጋ ከእምነትም ባሻገር መሆኑን እና ቅዱሱ ሃይማኖት ሳይለይ ለሰው ልጆች በሙሉ ተዓምር ሠሪ መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል።
ቅዱሱ እ.አ.አ. በ 1898 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም ካረፉ ከጥቂት ወራት በኋላ የተለያዩ ተዓምራት መከሰት የጀመሩ ሲሆን፥ በርካታ መነኮሳት መቃብሩ የተፈጥሮ ባልሆኑ መብራቶች ሲበራ እንዳዩ መናገራቸው እና በኋላም መቃብሩ ሲከፈት ሰውነቱ ሳይበላሽ ደምና ውሃ የሚያፈልቅ ሆኖ ማግኘታቸውን ገልጸው፥ ቀስ በቀስ ቅድስናው በሌሎች ዘንድ መስፋፋት እንደጀመረ እና ከዚያም በኋላ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እ.አ.አ. በ 1965 የብፁዕነት፣ በ 1977 ዓ.ም. ደግሞ ቅድስናቸው እንደታወጀላቸው ገልጸዋል።
ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆነ ሕይወት ግን ደግሞ በገለልተኛነት ይኖር ነበር
ቅዱስ ቻርቤል ሁለተኛው ተወዳጅነት ያተረፈበት ምክንያት “መናኝነቱ፣ ህይወቱን በሙሉ እንደ ባህታዊ እና በድህነት መኖሩ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ያለው ታማኝነት እንደሆነ አባ የሱፍ በአጽንዖት አስረድተዋል።
ቅዱስ ቻርቤል በ1851 ዓ.ም የሊባኖስ ማሮናዊት ማህበርን ተቀላቅሎ የመታዘዝ፣ የድህነት እና የንጽሕና ቃለ መሃላን በቅዱስ ማሮን ገዳም በ1853 ዓ.ም. በመፈጸም፥ በ 1859 ዓ.ም. ደግሞ ማዕረገ ክህነትን የተቀበሉ ሲሆን፥ ለ16 ዓመታት ያክል ከሌሎች ገዳማዊያት ጋር በገዳም ከኖሩ በኋላ ባህታዊ በመሆን እ.አ.አ. በ 1898 የገና ዋዜማ ላይ እስካረፉበት ዕለት ድረስ ለ 23 ዓመታት በምንኩስና መኖራቸውን ካህኑ ገልጸዋል።
አባ የሱፍ እንዳብራሩት ቅዱስ ቻርቤል በጸሎት እና በሥራ ላይ ያተኮረ ህይወት እንደነበራቸው የገለጹ ሲሆን፥ ይህም በሁሉም የምስራቅ ሃይማኖታዊ ባህሎች በሆኑት የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የድሩዝ እንዲሁም ምስራቃዊ ባልሆኑም ጭምር የተከበረ የመንፈሳዊ ንጽህና ሀሳብ ነው ብለዋል።
ቅዱስ ቻርቤል “ከሃይማኖታዊ ክፍፍል ያለፉ” እና “ለሁሉም የሊባኖስ ቤተ እምነቶች ያልተለመደ የግንኙነት መስመርን እና የጋራ ተስፋን ይወክላሉ ያሉት አባ የሱፍ ማታ፥ በእርግጥ ባለፉት አስርት ዓመታት በሀገሪቱ በተከሰቱት ተከታታይ ቀውሶች እና ግጭቶች ሊባኖስ የገጠማትን አስቸጋሪ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ‘ቅዱስ ቻርቤል ተስፋን የሚያመጣ፥ ምድራዊ መፍትሄዎች ሲከሽፉ ከላይ ባለው እርዳታ መተማመንን እንደሚወክል በጽኑ ከተናገሩ በኋላ፥ ቅዱሱ መንፈሳዊ ጥንካሬ ፖለቲካ የከፋፈላቸውን የተለያዩ ሃይማኖቶች አንድ እንደሚያደርጋቸው በማሳየት አብሮ የመኖር እና የሰላም ብርቅዬ ምልክት ሆነዋል ብለዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት ሊባኖስ እንዳልተተወች ያሳያል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅዱስ ቻርቤልን መቃብርን የጎበኙ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በመሆናቸው “በሊባኖስ ታላቅ ደስታና ኩራት” መሆኑን አባ የሱፍ ማታ ጠቁመው፥ ብፁዕነታቸው በዚህ ቅዱስ የማረፊያ ቦታ ላይ የሚያቀርቡት ጸሎት ‘ከተስፋም የሚሻገር ነገር መሆኑን’ መልዕክት የሚያስተላልፍ እንደሆነ እና ይህ የሚያሳየው ሊባኖስ እንዳልተተወች፣ ከፖለቲካ ያለፈ መለኮታዊ ኃይል እንዳለ እና ቀውሶችን መፍታት የሚችል እንደሆነ ነው ብለዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት “መንፈሳዊ አንድነትን ያሳያል” ያሉት ካህኑ፥ “የቅዱስነታቸው ጸሎት ቅዱስ ቻርቤል በሁሉም እምነት ተከታዮች ዘንድ የተከበረ በመሆኑ የአብሮ መኖር ምልክት መሆኑን ከፍ ከፍ እንደሚያደርገው፥ ብሎም ለቀላል እምነት የተደረገ ጠንካራ ጥሪ እንደሆነ እና ለሊባኖስ ሥነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ተሃድሶ የአብሮነት ምልክት መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ብፁዕነታቸው መቃብሩን መጎብኘታቸው “አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለምትገኘው ሃገር” እንዴት ብርሃን እንደሚያፈነጥቅባት እና ትኩረት እንድታገኝ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በገዳሙ የሚገኙ መነኮሳት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን ለመቀበል በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ያስታወሱት ካህኑ፥ በጉብኝታቸው ወቅት የተለያዩ የሀይማኖት እና የፖለቲካ ባለስልጣናት እንደሚሳተፉ ጠቁመው፥ ከሌሎች ጉዳዮች በተጨማሪ በተሳታፊዎች መካከል ሰላምታ፣ የጋራ እና የግል ጸሎት ጊዜያት እንዲሁም የጠቃሚ ስጦታዎች ልውውጥ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር የሊባኖስ መንግስት ህዳር 22 እና 23 ህዝቡ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የጉብኝት መርሃ ግብሮች ላይ እንዲሳተፉ ለማስቻል ህዝባዊ በዓላት እንደሚሆኑ ይፋ አድርጓል።
የጳጳሱ ጉብኝት ክብርን እና ተስፋን ያድሳል
ለአባ የሱፍ በአጠቃላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት ዓላማ የሕዝቡን ክብር እና ተስፋ መመለስ የሆነ መንፈሳዊ እና ሥነ ምግባራዊ አበረታች እንደሆነ ገልጸው፥ ብፁዕነታቸው ለደከመው ህዝብ መጽናናትን እና የሞራል ፈውስን እንደሚያመጣ እንዲሁም ከሊባኖስ ህዝብ ጋር የመቀራረብ ምልክት በመሆን ለሀገሪቱ ተዓምራዊ ጉብኝት እንደሚሆን አብራርተዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ሃዋሪያዊ ጉብኝቱ ሊባኖስ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል የውይይት መድረክ እንዲሁም ለአካባቢው እና ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሰላም ምንጭ እንድትሆን ያላት ሚናን ያጠናክራል ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት ካህኑ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ “በችግር ውስጥ ላለችው ሃገር ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እንደሚሰጥ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሃገሪቱን እንዳይረሳ በመጠየቅ፥ በሊባኖስ ብቻ ሳይሆን በመካከለኛው ምስራቅ ላይ የውስጥ መረጋጋትን የሚያበረታታ እንደሆነ አስረድተዋል።
በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉዞ ለማሮናዊት ካቶሊክ ብቻ ሳይሆን ለሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ለመላው የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት እና ለክርስቲያኑ ማኅበረሰብ በተለይም በስደት ላይ የሚገኙትን በሙሉ የሚያበረታታ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
“በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የእነዚህን ማህበረሰቦች ታሪካዊ ጠቀሜታ በድጋሚ ያረጋግጣል” ያሉት ካህኑ፥ ምክንያቱም በርካታ ወጣት ሊባኖሶሳዊያን በሕይወት ለመቆየት ወደ ሌላ ቦታ ሥራ ለመፈለግ ሃገሪቱን ለቀው የሚሄዱ ናቸው” ብለዋል።
የአንድ ትልቅ የሊባኖስ ቅዱሳን ቤተሰብ ቅርስ
ቅዱስ ቻርቤል ማክሎፍ የትልቅ የሊባኖስ ቅዱሳን ቤተሰብ አካል መሆኑን የጠቆሙት ካህኑ፥ ለአብነትም የማሮናዊት ቤተ ክርስቲያን መስራች የሆኑት ቅዱስ ማሮን፣ በሕመም ፊት በጽናት በመቆም የምትታወቀው መነኩሴ ቅድስት ራፍካ፣ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን የመሰረተው የካፑቺን አርበኛ ብፁዕ ዣክ ጋዚር ሃዳድ እንዲሁም ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ ሢመተ ቅድስናቸውን ያገኙት ማሮናዊው ፓትርያርክ እስጢፋኖስ ኤል ዱዋሂ እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የቅዱስ ቻርቤል መቃብር ጉብኝትም ይህንን የሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን ቅርስ እንደሚያጎላ የጠቆሙት አባ የሱፍ ማያ፥ የእነዚህ ቅዱሳን ትሩፋት ‘በመከራ ውስጥ ብርታትን እንደሚሰጥ’ ምክንያቱም የማሰላሰል ጸሎት እና እምነት በታላቅ አለመረጋጋት እና የህመም ሁኔታዎች ውስጥም ጽናት እንዳላቸው ትልቅ ምስክር ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በምስራቅ እና በምዕራብ አቢያተ ክርስቲያናት መካከል እንደ ድልድይ ሆነው ሊያገለግሉ ስለሚችሉ፥ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ብልጽግናን እና ለሮም ያላቸውን ታማኝነት ያሳያል ብለዋል።
ልክ እንደ ቅዱስ ቻርቤል ተምሳሌትነት፥ የእነዚህ ቅዱሳን እና ብፁዓን ሕይወት የሚያሳየው ቅድስና በተለይም በተዓምራት በኩል፣ ከኑዛዜ መለያየትም ያለፈ የአንድነት ምክንያት እንደሚሆን እና ከክልላችን ጋር እንድንጣበቅ የሚጋብዘን ነው ብለዋል።
“ይህ የቅዱሳን ትስስር ሊባኖስ አሁን ባለችበት አስቸጋሪ የሕይወት መስመር ማስጠንቀቂያ ነው” ያሉት ካህኑ በመጨረሻም፥ የሚቋቋም ማንነት እና ቅድስና የሊባኖስ እውነተኛ ጥንካሬ በመንፈሳዊ መሰረቶቿ ላይ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ካሉ በኋላ፥ “የጻድቃኑ የሞራል ተምሳሌትነት፣ የድህነት እና የጽድቅ ሕይወታቸው፥ ሀገርን እና ህዝቡን ያራራቀውን ሙስና ለመቃወም የሚያስችል ጠንካራ ማስታወሻ ነው፥ ስለዚህም በእነዚህ ቅዱሳን እንመካለን” በማለት አጠቃለዋል።