ፈልግ

Cry my Beloved Country Cry my Beloved Country  (ANSA)

በተገባደደው ዓመት ብቻ 17 የካቶሊክ ሚስዮናውያን መገደላቸው፥ ከእነዚህም ውስጥ አስሩ በአፍሪካ መሆኑ ተነገረ

የቫቲካን ኒውስ የዜና ወኪል የሆነው ፊደስ ኒውስ በተገባደደው የጎረጎሳዊያኑ ዓመት የተገደሉትን ሚስዮናውያን እና ሃዋሪያዊ ሰራተኞችን አስመልክቶ ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. በ 2025 ዓ.ም. ብቻ 17 ሚስዮናውያን በዓለም ዙሪያ የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 10 የሚሆኑት በአፍሪካ ውስጥ መገደላቸው እና ከእነዚህም ውስጥ ደግሞ አምስቱ በናይጄሪያ እንደሞቱ የጳጳሳዊ ተልዕኮ ማኅበራት አገልግሎት የሆነው ፊደስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የዓመቱ መገባደጃ በተቃረበበት እና የተስፋ ኢዮቤልዩ በተጠናቀቀበት በአሁኑ ወቅት ፊደስ ኒውስ ታህሳስ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርቱ በዓለም ዙሪያ ያሉ የሚሲዮናውያን እና ሃዋሪያዊ ሥራ ሠራተኞችን ሞት በሪፖርቱ ማካተቱ ተነግሯል።

በየዓመቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ቤተክርስቲያንን ለማገልገል በተለይም በዓመፅ፣ በድህነት እና በፍትህ መጓደል በሚታወቁ አከባቢዎች ውስጥ ሕይወታቸውን የሰጡ ካህናት፣ ገዳማዊያት፣ የሥነ መለኮት ተማሪዎች እና ምዕመናን ታሪክ ላይ አተኩሮ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያወጣ ይታወቃል።

በዚህም አግባብ የ 2025 ዓመትን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት መሠረት 10 ካህናት፣ 2 የሥነ መለኮት ተማሪዎች፣ 2 ካቴኪስቶች፣ 2 ገዳማዊያት እህቶች እና 1 ምዕመን መገደላቸውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ በዚህ ዓመት የሟቾች ቁጥር 14 ሚስዮናውያን ከተገደሉበት የ2024 ዓመተ ምህረት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሶ፥ ከ2000 እስከ 2025 ባሉት ዓመታት ብቻ 626 ሚሲዮናውያን ወይም ሃዋሪያዊ ሠራተኞች መገደላቸውን ገልጿል።

የፊደስ ኒውስ የጎረጎሳዊያኑ የ2025 ሪፖርት እንደሚያሳየው የሰዎቹ አሟሟት ለሰማዕትነት ጥብቅ መመዘኛዎችን ቢያሟላም ሆነ ባያሟላ፣ በሃዋሪያዊ ሥራ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተወሰነ መልኩ የተሳተፉ እና በአመጽ የተገደሉትን ሁሉንም ካቶሊኮች እንደሚያካትት በመግለጽ ‘ሚሲዮናውያን’ የሚለውን ሰፊ ትርጓሜ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን አስምሮበታል።

በአፍሪካ፥ በተለይም በናይጄሪያ በርካታ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ሞተዋል
የአፍሪካ አህጉር ለሚስዮናዊነት ሥራ በጣም አደገኛ ከሚባሉት አህጉራት አንዱ ሆኖ መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት በተገባደደው ዓመት በዚሁ አህጉር ውስጥ 10 ሰዎች መገደላቸው እና ከነዚህም ውስጥ 6ቱ ካህናት፣ ሁለቱ የሥነ መለኮት ተማሪዎች፣ እንዲሁም ሁለቱ ካቴኪስቶች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ሚሲዮናዊያኑ የተገደሉት በቡርኪናፋሶ፣ ኬንያ፣ ሴራሊዮን፣ ሱዳን እና ናይጄሪያ ውስጥ እንደሆነም ሪፖርቱ ገልጿል።

የቅድስት መንበር የወንጌል ስርጭት ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ናይጄሪያዊው ሊቀ ጳጳስ ፎርቱናተስ ንዋቹኩ ከፊደስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‘ይህ ሁሉ አደጋ ከባድ የሀዘን ምንጭ’ እንደሆነ ጠቅሰው አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ ናይጄሪያ በርካታ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ብሎም የተለያዩ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት ሀገር እንደሆነች አስታውሰው፥ በዓለም ላይ በርካታ ሃይማኖተኞች ካላቸው ሃገራት አንዷ መሆኗን ከገለጹ በኋላ፥ “ሁላችንም የሰላም ሰዎች ለመሆን እንፈልጋለን” በማለት ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳሱ እንዳሉት ህዝበ ሙስሊሙ በሃይማኖታቸው ስም የጥቃት ድርጊቶች ሲፈጸሙ ማውገዝ እና መቃወም እንደሚገባው፥ ይህም ይሆን ዘንድ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ሃይማኖትን ምክንያት አድርገን የሰውን ህይወት እስከማጥፋት ድረስ የሚወስዱ የአመፅ ድርጊቶችን በጋራ መቃወም እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ንዋቹኩ በቃለ ምልልሱ ወቅት እንደገለፁት እነዚህ ክርስቲያኖች ጀግኖች ለመሆን ሲሉ እንዳልሞቱ፥ ነገር ግን የሥነ መለኮት ወይም መደበኛ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ እና የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን ሲያራምዱ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው ገልጸው፥ የናይጄሪያ መንግስት ንፁሃን ዜጎችን ለመከላከል እና ለመጠበቅ እንዲሁም የሀገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ ለማሻሻል የበለጠ መስራት እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል።

በሌሎች አህጉራትም ውስጥ ጥቃቱ መፈጸሙ
የፊደስ ሪፖርት ከዚህ ቀደም ለብዙ ጊዜ በዚህ “አሳዛኝ ደረጃ” ላይ የነበረው አህጉር አሜሪካ እንደሆነ በመጥቀስ፥ በጎረጎሳዊያኑ 2025 በአጠቃላይ 4 ሚሲዮናውያን ማለትም 2 ካህናት በሜክሲኮ እና በዩናይትድ ስቴትስ፥ እንዲሁም 2 ገዳማዊያት እህቶች በሄይቲ የተገደሉ ሲሆን፥ ይህም ከአፍሪካ ቀጥሎ በዚህ ዓመት ጥቃት የተፈጸመበት ክልል መሆኑ ተረጋግጧል።

የኢስያ አህጉርን በተመለከተ በማይናማር አንድ ካህን እና በፊሊፒንስ የሚኖር አንድ መምህር የሆነ ምዕመን መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በመጨረሻም ከአውሮፓ አንድ ካህን በፖላንድ ሃገር ውስጥ መገደላቸው ተረጋግጧል።

ቤተክርስቲያንን እያገለገለ መገደል  
በፊደስ ሪፖርት አጽንዖት ከተሰጠባቸው ታሪኮች መካከል ናይጄሪያዊው የሥነ መለኮት ተማሪ የነበረው ኢማኑዌል አላቢ ታሪክ ሲሆን፥ ይህ ወጣት ሃምሌ ወር ላይ በግዳጅ በተሳተፈበት ሰልፍ ላይ በኢቪያኖክፖዲ ከተማ በሚገኘው ንዑስ ዘርዓ ክህነት ላይ ጥቃት በፈጸሙት ጠላፊዎች ተወስዶ መገደሉ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ መጋቢት ወር ላይ በሄይቲ ውስጥ በታጣቂ የወንበዴዎች ቡድን አባላት የተገደሉትን የሕፃኑ ኢየሱስ የቅድስት ቴሬሴ ታናናሽ እህቶች ማህበር አባላት የሆኑት የኢቫኔት ኦኔዛየር እና የጄን ቮልቴርን ታሪክ ጠቅሷል።

የፊደስ ሪፖርት በመጨረሻም ማይናማር ላይ ከባድ መከራ ባደረሰው ግጭት ውስጥ የተገደሉት የመጀመሪያው በርማዊ ካቶሊክ ካህን አባ ዶናልድ ማርቲንን ታሪክ አጉልቶ ያሳየ ሲሆን፥ ሪፖርቱ የካህኑ የተቆራረጠ አስከሬን የካቲት ወር ውስጥ በምዕመናን ጥረት በቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ መገኘቱንም ጭምር ገልጿል።

31 Dec 2025, 13:51