ፈልግ

እህት ኢዛቤል ቱርሲዮስ 'ፍሮንቴራ ጊግና' በተሰኘው የስደተኞች ማዕከል ውስጥ እህት ኢዛቤል ቱርሲዮስ 'ፍሮንቴራ ጊግና' በተሰኘው የስደተኞች ማዕከል ውስጥ  

ወደ ህልማቸው ለሚጓዙ ሰዎች ተስፋን መዝራት ይገባል ተባለ

የድንግል ማሪያም ፍራንቺስካዊያን እህቶች በእኩልነት መንፈስ በመነሳሳት የተሻለ ህይወትን ፈልገው ከሃገራቸው ለተሰደዱ በዩናይትድ ስቴትስ እና በሜክሲኮ ድንበር ላይ ለሚገኙ ስደተኞች በሙሉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ትልቅ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኝ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ካሚሎ የተባለ አንድ ወጣት ስደተኛ እንደተናገረው ከሃገራቸው የተሰደዱ ሁሉ እንደ ወንድም እና እህት እርስ በራሳቸው እንዲዋደዱ ያለውን ምኞት ገልፆ፥ ‘ጉድለት ያለብን ወይም የሌለብን ሁላችንም ሕያዋን ፍጥረታት ነን፥ ነገር ግን ሁላችንም እኩል ነን’ ብሏል።

የስደት ኑሮው ለእሱ ምን ማለት እንደሆነ የተጠየቀው ወጣቱ ስደትን እንዴት መረዳት እንዳለበት ያለውን እምነት ጠቅለል አድርጎ ገልጿል።

የድንግል ማሪያም ፍራንቺስካዊያን እህቶች በዩናይትድ ስቴትስ እና በሜክሲኮ ድንበር ላይ ይህንን ተልእኮ የሚያከናውኑት ‘ሞቪሊዳድ ሂማና’ በተባለው አገልግሎታቸው ነው።

ከሠላሳ ዓመታት በፊት በሜክሲኮ እና አሜሪካ ድንበር ላይ የሚገኘው የፒያድራስ ኔግራስ ሀገረ ስብከት ስደት ላይ ለሚገኙ ዜጎች መጠለያ የከፈተ ሲሆን፥ ከጊዜ በኋላ ሁኔታዎች እየተለዋወጡ መጥተው የተሻለ ህይወት ለመፈለግ ተስፋን ሰንቀው ለሚጓዙ ሰዎች መጠሊያ የሚሆን ‘ፍሮንቴራ ዲግና’ ወደ ተሰኘ ማዕከል መቀየሩ ተገልጿል።

ተልዕኮ ማለት በጣም ወሳኝ በሆነ ስፍራ ማገልገል ነው
መጀመሪያ ላይ በዋነኝነት የስደት አደጋዎችን በመከላከል ላይ በማተኮር ይሰራ የነበረው የኤልሳልቫዶር ሃይማኖታዊ ጉባኤ ውስጥ ይሰሩ የነበሩት እህት ኢዛቤል፥ በኋላ ላይ ጓቲማላ ውስጥ በሚገኙ ስምንት መጠለያዎች በኩል በማለፍ የስደትን መስመሮችን ያጠናቀቁ ሲሆን፥ በመጨረሻም ሜክሲኮ፣ ኢክስቴፔክ ከተማ ደርሰዋል።

እህት ኢዛቤል እ.አ.አ. በ 2018 ዓ.ም. ወደ ቦጎታ በመጓዝ ከሌሎች ገዳማዊያት እህቶች ጋር በመሆን በዚያን ወቅት በብዛት ወደ ኮሎምቢያ ይገቡ ለነበሩት የቬንዙዌላ ስደተኞች ልዩ አገልግሎት ሲሰጡ ነበር።

“ወደ ሳሊትሬ ተርሚናል የሚመጡትን ቬንዙዌላውያን ስደተኞችን ለመቀበል በየዕለቱ እሄድ ነበር” ያሉት እህት ኢዛቤል፥ ለስደተኞቹ አንዳንድ አቅጣጫዎችን እንደሚነግሯቸው፣ ጣፋጭ መጠጦችን እና ብስኩቶችን እንደሚሰጧቸው እንዲሁም የጌታን ቃል አብረው ይካፈሉ እንደነበር እና በተለይም ሴት ስደተኞቹን ያግዙ እንደነበር አስታውሰዋል።

ትንንሽ ሻንጣቸውን ይዘው ለሚመጡት ዓይናፋር ወጣት ሴቶች፥ ቦጎታ ውስጥ ሴቶች ለዝሙት አዳሪነት ተገዝተው እንደሚሸጡ ስለሚታወቅ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ምን እንደሆነ እየነገርናቸው ተርሚናሉን በሙሉ እንዞር ነበር ብለዋል።

እህት ኢዛቤል ከጥቂት ወራት በኋላ ከሌሎች ሁለት ገዳማዊያት እህቶች ጋር በመሆን ወደ ሜክሲኮ ሄደዋል።

አንድነት ተስፋን ያድሳል
የፍራንቺስካዊያን እህቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የተከሰቱትን የስቃይ ታሪኮችን ለስደተኞቹ ሲያካፍሉ እንደነበር እህት ኢዛቤል አክለው ገልጸዋል።

ለእሳቸው በየቀኑ ወደ 1,000 የሚጠጉ ስደተኞችን መርዳት የቻሉበት ምክንያት ለመግለጽ መለኮታዊ ጥበቃ ብቸኛ ማብራሪያ መሆኑን ገልጸው፥ በወቅቱም ምግብ፣ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ፣ የህክምና እርዳታ እና ለሁሉም ሰው መንፈሳዊ ማጽናኛ መስጠት መቻላቸውን አስረድተዋል።

ለዚህም በርካታ በጎ ፈቃደኞች፣ ደብሮችን፣ ድንበር የለሽ የዶክተሮች ቡድንን እና የፍራንቺስካዊያን የስደተኞች አገልግሎት ትስስርን በእጅጉ አመስግነዋል።
የፍራንቺስካዊያን ጸሎት እና መንፈሳዊነት ገዳማዊያቱ የስደተኞቹን ስቃይ እንዲሸከሙ እንደረዳቸውም ገልጸዋል።

ይህም ስቃይ ልጃቸው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከተወለደ ዜግነት ያገኛሉ በሚል የውሸት ተስፋ ወንዙን ለመሻገር እንደወሰኑ ነፍሰ ጡር እናቶች ያሉ ሁኔታዎችን ይጨምራል።

ሌሎች ደግሞ የጥቃት፣ የአፈና ወይም የባርነት ሰለባ የሚሆኑ ሲሆን፥ ነገር ግን በኋላ እራሳቸውን ነፃ አውጥተው ወደ ሰሜን እንደሚደርሱ እና አብዛኛዎቹ እነዚህ ገዳማዊያት በማስታወስ ለምስጋና እንደሚደውሉላቸው ገልጸዋል።

ስደት እና ብፅዕት ማሪያ ካሪዳድ ብሬደር
ካሚሎ ለእራሱ፣ ለእናቱ እና ለእህቱ የተሻለ ነገር ፍለጋ አገሩን ለቆ ለመሄድ መወሰኑን በመግለጽ፥ “ለመላው እናቶች [ገዳማዊያት እህቶች] ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ከሁሉም ስደተኞች ጋር በሚያደርጉት ውብ እና ታላቅ ሥራ ተስፋ እንዳይቆርጡ ነው” ካለ በኋላ፥ ሃገሩ የነጻነት ቀኗን ባከበረችበት ወቅት ከገዳማዊያቱ ጋር የነበረውን ልዩ የምሳ መርሃ ግብር መቼም እንደማይረሳው ገልጿል።

ስደት ገዳማዊያን እህቶች በወንድማማችነት እና በሲኖዶሳዊ አገልግሎት ምላሽ የሚሰጡበት እውነታ ነው።

የጉባኤው መስራች የሆነችው ብፅዕት ማሪያ ካሪዳድ ብሬደር በጊዜዋ የሚስዮናውያንን ሃሳብ በመቀበል የትውልድ ሀገሯን ስዊዘርላንድ በመተው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በኢኳዶር እና በኮሎምቢያ የተረሱ እና የተገለሉትን ህዝቦች አገልግላለች።

“እማሆይ ካሪዳድ በእያንዳንዱ ድንበር ላይ እህቶች እንዲገኙ ቤቶችን ወይም ቦታዎችን ትመሠርት ነበር ብዬ አስባለሁ” ያሉት እህት ኢዛቤል፥ ምክንያቱም ያደረገችውም ይህንኑ እንደሆነ ገልጸው፥ እማሆይ ካሪዳድ በጦርነቱ ጊዜ የቆሰሉትን ሰዎች ለመርዳት ትምህርት ቤቷን ዘግታ ወደ ሆስፒታልነት በመለወጥ እና እህቶች በነርስነት እንዲያገለግሉ ማድረጓን አስታውሰው፥ በአሁኑ ወቅት በፔድራስ ኔግራስ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ገዳማዊያትን የሚያበረታታው ይህ የእማሆይ ካሪዳድ ሚስዮናዊ መንፈስ እንደሆነ አስረድተዋል።

11 Dec 2025, 16:27