ከቅድስት ሀገር በተላለፈ መልዕክት ‘ሰላም የሕይወታችን ምርጫ እንጂ ቅዠት አይደለም’ ተባለ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የአባ ኢብራሂም ፋልታስ መልዕክት እንደሚከተለው ይቀርባል፦
“ብርሃነ ልደቱ እየተቃረበ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የምናደርገው የስብከተ ገና ጉዞ ሰላምን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ እንድንዘጋጅ ያደርገናል።
ሰላም ይሰፍናል ተብሎ ጥልቅ ተስፋ በተደረገባት በቅድስት ሀገር ውስጥ፥ ሰላምን ለማግኘት ያለውን ፍላጎት ለመመለስ የተወሰኑ ጥያቄዎችን መመለስ ይጠይቃል።
ለዓመታት፥ በተለይም መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ሞትን እና ውድመትን ስላስከተለው ግጭት፥ እንዲሁም ጥላቻን እና መከራን ስለሚያስከትለው በቀል ብዙ ተናግረናል፣ ብሎም ጽፈናል።
የሰው ልጅ ለአብሮነት እና ለመረዳዳት መንገዱ የተዘጋበት፣ የበለጠ ክፋትን የሚያመጣው የክፋት ሰንሰለት መበጠስ የማይችልበት ጨለማ ገጽታው የበላይ የሆነበት ክፉ አዙሪት ውስጥ የገባ ይመስላል።
በጋዛ እና በጦርነት አረንቋ ውስጥ በሚገኙ ሃገራት የሚወጡ ዜናዎች እና ምስሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ንጹሐን እና ጠባቂ የሌላቸው ሰዎች አካላዊ እና ሥነ ምግባራዊ ስቃይ ያሳያሉ። አፋጣኝ ምላሾች በቁጣ እና በብዙ የሰው ልጅ ስሜታዊ ተሳትፎ እየተገለጹ ይገኛሉ።
ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ
የጥቃት እርምጃዎቹ ሊቋቋሙት ከሚቻልበት ገደብ በላይ አልፏል፥ በጋዛ ውስጥ የቦምብ ጥቃቶች፣ ግጭቶች፣ ፍንዳታዎች፣ እንዲሁም እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶች እና መድሃኒቶች እጥረትን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች ለሞት እና ለመጥፋት መንገድ ሲሆኑ አይተናል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና የተለያዩ ሀገር መሪዎች የሽምግልና ጥረቶችን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሰላም ጥሪዎች ይህንን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ መለወጥ ወይም መፍታት አልቻሉም።
ወደ ጋዛ የገባው ዕርዳታ እና አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን የማውጣት እድሉ ውስንነት ከውቅያኖስ ጠብታ ያነሰ ነው።
የሰው ልጅ በመከራ እንዲጸና የሚያነሳሳው ምንድን ነው? በተጨባጭ በሚደረጉ የእርዳታ እና የአብሮነት ተግባራት የረዳት-አልባነት ስሜትን እንዴት ማሸነፍ ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎች መልስ አላገኙም። ከብዙ ቃላት እና ከብዙ ስቃይ በኋላም ለዚህ አስከፊ ጦርነት የሚታየው ግድዬለሽነት እየጨመረ የመጣ ይመስላል። ፍርሃት ሰዎች በጦርነቱ ውስጥ ጣልቃ ሊገቡ ለሚችሉ አደራዳሪ አካላት ጥሪ እንዳያደርጉ የሚከለክል ይመስላል። ዝምታ ሁላችንም ተባባሪ እንደሚያደርገን ማወቅ አስቸጋሪ ሆኖብናል።
በጋዛ ዙሪያ እና የፍልስጤም ግዛት በሆነው ዌስት ባንክ “ያልተፈቀደላቸው” ተብለው የተሰየሙ ሰዎች ማለትም የሰብዓዊ ሰራተኞች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ጋዜጠኞች እና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እንዳይደርሱባቸው ለመከላከል አካላዊ እና ጎልተው የሚታዩ ግድግዳዎች ተገንብተዋል። በቅድስት ሀገር ውስጥ በሚገኙ የጦርነት ቀጠናዎች የትኛውንም ህይወት ለማዳን ፍትህ ማስፈን የሚችል እና በጦርነቱ ለደከመው ህዝብ ሰብአዊ ክብርን ለመመለስ የሚያስችል የእውነት መንገድ ለመዝጋት አጥር የተሰራ ይመስላል።
የሰው ልጅ ተስፋ የቆረጡ እና ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለመኖር የተገደዱ ሰዎችን እንዳይረዳ የሚከለክለው ማን እና ምን እንደሆነ መጠየቅ ይገባል።
ድክመታቸው አስፈርቷቸው ነው? የነሱ ተስፋ መቁረጥ ህሊናችንን አይረብሽምን?
ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ማስቀደም የሚመርጠው ማነው? ሞትን እና ውድመትን የሚያስከትለውን ወታደራዊ ወጪን ማብዛት የቀጠለው ለምንድነው?
በቀላሉ የጥቃት ኢላማ የሆኑትን ማለትም በሐዘን የተጎዱትን ወንዶችና ሴቶች፣ ሕፃናትን፣ አዛውንቶችን፣ አቅመ ደካሞችን እና የታመሙትን እንደ ጠላት የሚያያቸው ማን ነው?
ሀብቶች በብዛት እና በቀላሉ በሚገኙበት ጊዜ ለመመገብ፣ ለመፈወስ እና ልባዊ በሆነ ስሜት ለማቅረብ ያልተቻለው ለምንድነው?
ከመሻገሪያ ድንበር ወይም ከፍተሻ ቦታዎች ባለፈ በቀላሉ ሊደረስባቸው በሚችሉ መድኃኒቶች ላይ ጥገኛ ለሆኑ ሰዎች ለምን የሕይወት ዕድል አልተሰጣቸውም?
በጋዛ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለሦስተኛ ጊዜ የገባው የክረምት ቅዝቃዜ ልባዊ ያልሆነ የአብሮነት መንፈስ ከሌለ ልብን በግዴለሽነት እንዲቀዘቅዝ ያደርጋል።
ለማስታረቅ የመጣ ቅዱስ ህፃን
እነዚህ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ለሁሉም ሰው የሚቀርቡት ያለ ልዩነት ነው። ምክንያቱም ለዚህ ኢሰብአዊ ሁኔታ ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን። አሁንም ቢሆን መልስ ይኖራል።
በጨርቅ ተጠቅልሎ፣ በቀዝቃዛ ጨለማ በከብቶች በረት ውስጥ ሰላም ለሌላቸው ልቦች ሰላምን የሚያመጣ አንድ ህፃን ተወልዷል። ይህ ህፃን ወንድሞቹን እና እህቶቹን ለማስታረቅ፣ ንጹሐን እና የተጎዱትን ለመደገፍ እንዲሁም ባልንጀራን መውደድ ብቸኛው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ የመጣ ቅዱስ ሕፃን ነው። በገና ሰሞን ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ከቤተልሔም በረት የመጣውን መልዕክት በማስታወስ ህፃኑ ኢየሱስን እናክብረው። ይህ መልዕክት ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላም እውነተኛ እና ጠቃሚ መልእክት ነው።
ሰላም የሕይወታችን ምርጫ እንጂ ቅዠት አይደለም። ሰላም አንዴ ከተነገረ በኋላ ትርጉሙን የሚያጣ ቃል ብቻ አይደለም።
ሰላም ድፍረትን እና ጀግንነትን ይጠይቃል፥ የመርዳት እና የአዳኙን አምላክ እውነት ለመመስከር ድፍረትን ይጠይቃል” በማለት አጠቃለዋል።