በቤተልሔም የሚገኙ ገዳማዊያት እህቶች ቤተሰብ የሌላቸውን ህፃናት እያገለገሉ እንደሚገኝ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በቤተልሔም የሚገኘው እና በቅዱስ ቪንሰንት ዴ ፖል የበጎ አድራጎት ሴት ልጆች ማህበር የሚመራው “የቅድስት ቤተሰብ” ወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ክፍሎችን የሞላው ስሜት ህፃናት ለፍቅር ያላቸው ፍላጎት ሲሆን፥ በቀለማት ባሸበረቁ መፃፊያ ቁሳቁሶች እና መጫወቻዎች መካከል ደምቃ በምትታየው የህፃናቱን ሕይወት፥ በማዕከሉ የሚገኙ ህፃናት ጎብኚዎችን በየዋህ ልባቸው አቅፈው ሲቀበሉ ማየት የስሜት እንባዎችን መቆጣጠር እንደሚያዳግት ገዳማዊያቱ በመግለጽ፥ ከስድስት ዓመት በታች የሆኑትን እነዚህን ህፃናት የሚንከባከቡት ገዳማዊያት የህክምና እንክብካቤ ዋስትናን ጨምሮ ለህፃናቱ የምግብ እና የትምህርት አገልግሎት እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።
እንደ ኢየሱስ ያሉ ልጆች
በአከባቢው የቅዱስ ቪንሰንት ማህበር የበላይ አለቃ የሆኑት አባ ካሪም ማሮን ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት “በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙት ህፃናት ወላጅ አልባ የሆኑ፣ የተጣሉ ወይም በጎዳናዎች ላይ የተገኙ መሆናቸውን ጠቁመው፥ አብዛኛዎቹ ህፃናት የተወለዱት በከፋ ድህነት ውስጥ ከሚገኙ ቤተሰቦች እንደሆነ እና ብዙውን ጊዜ ወጣት ብቸኛ እናቶች ልጆቻቸውን በቤተሰቦቻቸው እንዳይገደሉ በመፍራት ለማዕከሉ አሳልፈው ለመስጠት እንደሚገደዱ ጠቁመው፥ ከሁሉም እይታ አንጻር ሲታይ ይህ አስደናቂ እውነታ እንደሆነ ገልጸዋል።
ገዳማዊያት እህቶቹ አዲስ የተወለዱ ህፃናትን በፍቅር ተቀብለው እንደሚያሳድጉ የገለጹት አባ ካሪም፥ እነዚህ ህፃናት በችግር፣ በመረሳት እና በተጎዳ ማህበረሰብ ውስጥ የተወለዱ መሆናቸውን አስታውሰው፥ ህፃናቱ ልክ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆናቸውን የጠቆሙ ሲሆን፥ ይህም በመሆኑ ብዙ ፍቅር እና ርህራሄ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፥ ቤት፣ ምግብ፣ እንክብካቤ እና ፍቅር የሚሰጣቸው ቢሆንም፥ ነገር ግን የእናት እና የአባት ናፍቆት እንደሚቀራቸው ተናግረዋል።
የህፃናት ማሳደጊያው ድርጅት
በቤተልሔም ህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ አርባ አምስት ህፃናት በቋሚነት የሚኖሩ ሲሆን፥ ተቋሙ ከድሃ ቤተሰብ የመጡ ለሌላ 35 ህፃናት የመዋለ ህፃናት አገልግሎት እንደሚሰጥ እና በጠቅላላው ዕድሜያቸው ከስድስት ዓመት በታች ለሆኑ ወደ 80 የሚጠጉ ህፃናትን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ማዕከሉ ማድ ቤት፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ አነስተኛ የጸሎት ክፍል እና ቤተ ክርስቲያን፣ መኝታ ቤቶች፣ የመማሪያ ክፍሎች እና የመጫወቻ ስፍራዎች ያሉት በጥንቃቄ የተደራጀ ሲሆን፥ የመኝታ ክፍሎቹ ከጨቅላ ህፃናት እስከ 9 ወር ድረስ ለሚገኙ ህፃናት፣ ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል ለሚሆኑ ህፃናት፣ ከ 3 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት እና በመጨረሻም ትንሽ ከፍ ላሉ ህፃናት ማደሪያ የሚያገለግል በእድሜ የተከፋፈሉ መሆናቸው ተገልጿል።
የትምህርት አሰጣጡ እንዲሁ በዕድሜ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፥ መማሪያ ክፍሎቹ ለጨቅላ ህፃናት፣ መካከለኛ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ እና ትንሽ ከፍ ላሉት ህፃናት ለየብቻ የተዋቀረ እንደሆነ እና ይሄንን መዋቅር የሚመሩ እህቶች፣ መምህራን፣ ዶክተሮች እና በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ ወደ 70 የሚጠጉ ሰዎች ያሉት ቡድን እንዳለ ተገልጿል።
የተተውትን እና የተጣሉትን መቀበል
“በቤተልሔም የገና በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ይመጣል፣ እዚህ ግን ሕያው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በየቀኑ እናከብራለን” ያሉት ላለፉት 20 ዓመታት የህፃናት ማሳደጊያው ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩት እህት ላውዲ ፋሬስ፥ ትምህርተ ክርስቲያንን በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር እንደሚገልጹ ጠቁመው፥ እኛነታችን የሚገለጸው በማንነታችን እና በምንሰራው ነገር እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ እነዚህ ህፃናት በህብረተሰቡ የተጣሉ በመሆኑ ይሄንን በማድረጋቸው ክርስቶስን በእቅፋቸው እንደሚቀበሉ ጠቁመው፥ “ህፃናቱ በማዕከሉ ውስጥ እንክብካቤን፣ የተዘረጉ እጆችን እና ፍቅርን ያገኛሉ” ብለዋል።
ይህ ድጋፍ ግን በጊዜ የተገደበ መሆኑን ያስታወሱት እህት ላውዲ፥ ከህፃናቱ ጋር አብረው መጓዝ የሚችሉት ስድስት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ብቻ እንደሆነ ገልጸው፥ ህፃናቱ ዕድሜያቸው ደርሶ ከማዕከሉ ሲወጡ ስሜቱ ከባድ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ከህፃናት ማሳደጊያ ተቋሙ ከወጡ በኋላ ቀሪ ህይወታቸው ምን እንደሚሆን እና ወደፊት ምን እንደሚጠብቃቸው እንደማያውቁ ጠቁመው፥ በየቀኑ ህፃናቱን መንከባከብ እስከቻሉ ድረስ በቤተልሔም መገኘታቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እና ከዚያም ለፍልስጤም መንግሥት ተላልፈው እንደሚሰጡ አስረድተዋል።
የእግዚያብሔር ጥበቃ ጣልቃገብነት
አባ ማሩን ይሄንን እውነታ በአንድ በኩል “የተከፈተ ቁስል” በሌላ በኩል ደግሞ “የዕለት ተዕለት ተአምር” በማለት የገለጹ ሲሆን፥ አስገራሚው ጎኑ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ብቻቸውን የሆኑ እና የቤተሰብ ድጋፍ የሌላቸው እናቶች በአካል በመገኘት እንዲሁም በድህረ ገጽ በኩል በሆስፒታል ውስጥ እርዳታ የሚጠይቁ እናቶች መኖራቸውን፥ ከወለዱ በኋላም የልጁን መብት በሙሉ ክደው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደሚመለሱ እና ህፃኑ ከገዳማዊያቱ ጋር መኖር እንደሚቀጥል ልጸዋል።
አወንታዊ ጎኑ ከኢኮኖሚያዊ እይታ አንፃር ማዕከሉ የሚደገፈው በእንግዳ ማረፊያው ውስጥ የሚቆዩ ክርስቲያን መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ እስራኤላውያን እና እህቶችን ለመርዳት ገንዘብ በሚሰበስቡ ፍልስጤማዊያን ቤተሰቦች በሚያደርጉት የግል ልገሳ ብቻ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በእግዚያብሔር ጥበቃ እና ‘ነጫጭ እጆች’ ብለው በሚጠሩት የተለያዩ ልገሳዎች እንደሆነ እህት ፋሬስ ገልጸው፥ ወደ ማዕከሉ የሚገባ ሰው ሁሉ የሚችለውን እንደሚያደርግ እና አንድ ሳንቲም ብትሆን እንኳን ለማዕከሉ ሀብት እንደሆነ ጠቁመው፥ “ጌታ ፈጽሞ አይተወንም” ብለዋል።
ርህራሄ እና ፍቅር
የማዕከሉ ግብ ለእነዚህ ህፃናት ክብር፣ ፍቅር እና የወደፊት እድል መስጠት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ማዕከሉን የሚጎበኙ መንፈሳዊ ነጋዲያን ከህፃናቱ ጋር በጣም እንደሚቀራረቡ እና ፍቅሩ የጋራ እንደሆነ እህት ፋሬስ ገልጸዋል።
አንድ ጊዜ በህፃንነቷ የተጣለች ነገር ግን ወደ አንድ ቤተሰብ የመቀላቀል መልካም እድል ያገኘች ሴት የነበረችበት ከፈረንሳይ የመጣ አንድ ቡድን ማዕከሉን መጎብኘቱን ያስታወሱት እህት ፋሬስ፥ ልጅቷ ህፃናቱን ስትመለከት በጣም እንደተነካች እና እሷ የሚንከባከባት ቤተሰብ ስላገኘች አድጋ ማግባት እንደቻለች፥ ነገር ግን እዚያ ከተማ ውስጥ ህፃናትን በጉዲፈቻ መቀበል የተከለከለ በመሆኑ እነዚህ ህፃናት የወደፊት ተስፋ እንደሌላቸው መናገሯን አስታውሰዋል።
“ከእነዚህ ህፃናት መካከል አንዱ ልሆን እችል ነበር” ያለችው ጎብኚዋ፥ ሁል ጊዜ የሚጎድል ነገር መኖሩን እና ይህም የቤተሰብ ናፍቆት እንደሆነ ገልፃለች።
በእነዚህ ትንንሽ ህፃናት ዙሪያ ምግብ፣ ወተት፣ አልባሳት፣ መጫወቻዎች፣ ዳይፐር እና ብርድ ልብስ የሚያመጡ በጎ ፈቃደኞች፣ ዶክተሮች፣ ለጋሾች፣ መንፈሳዊ ነጋዲያንን እና ጎረቤቶችን ያቀፈ የአንድነት ሰንሰለት መኖሩን የጠቆሙት እህት ፋሬስ፥ በዚህ መንገድ ርህራሄ፣ ህይወት እና ከሁሉም በላይ ፍቅር ወደ ማዕከሉ ህፃናት ይደርሳል ብለዋል።