ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ በጉባኤው ላይ ንግግር ሲያደርጉ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ በጉባኤው ላይ ንግግር ሲያደርጉ 

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከ181 ዓመታት በላይ በዘመናዊ ትምህርት ፈር ቀዳጅ ሆና ዛሬ በመላ ሀገሪቱ በ545 ትምህርት ቤቶች በላይ እና በ1 ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ ዜጎች ጥራት ያለዉ ትምህርት በመስጠት ላይ ትገኛለች። ቤተክርስቲያኗ እውቀትን ከሥነ ምግባር ጋር አጣምራ በመስጠት የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ማፍራቷን ቀጥላለች።

 አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት አዳራሽ ውስጥ ታህሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የትምህርት ተቋማት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚደንት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስን ጨምሮ ብፁዓን ጳጳሳት፣ የየሃገረ ስብከቶች የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቢሮ ተወካዮች እና የጠቅላይ ጽህፈት ቤት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፥ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመላው ሀገሪቱ በትምህርት ዘርፍ እያሳደረች ያለውን በጎ ተፅዕኖ ጠቅሰው፥ ለዚህ ሥራዋ እውቅና እንደተሰጣትና እያከናወነች ባለው መልካም ተግባር በርትታ እንድትቀጥል በመንግስት አካላት መጠየቋን ተናግረዋል።

ታህሳስ 10 በተካሄደው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የትምህርት ተቋማት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የ 2025 (እ.አ.አ.) ዓመት የትምህርት ዘርፍ አፈጻጸም፣ አዲሱ የትምህርት አዋጅ ዝርዝር እና ተግባራዊነት እንዲሁም በትምህርት አስጣጥ ሂደት ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ተነስተው ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በጉባዔው ላይ ከተጋበዙት የመንግስት ተወካዮች ጋር በተካሄደው ውይይት ከትምህርት አዋጅ ጋር ተያይዞ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምክረ ሀሳብ፣ የመፍትሔ አቅጣጫዎች እና በመንግስት በኩል የትብብር አማራጮች የተመላከቱ ሲሆን፥ ጉባዔው አዲስ የወጣው የትምህርት አዋጅን ከቤተክርስቲያኗ የትምህርት ተቋማት ህጋዊ ምዝገባ አኳያ በጥልቀት ተወያይቶ ቀጣይ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሃገር አቀፍ ደረጃ 295 አጸደ ህፃናት፣ 182 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 47 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 20 የሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች እና 1 ዩኒቨርሲቲ መስርታ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠች እንደሚገኝ ይታወቃል።

ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ አንድ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ፥ ከአጸደ ህፃናት እስከ መሰናዶ ያሉ 44 ትምህርት ቤቶች እንዳሏት ተገልጿል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ መደበኛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመጀመሩ 64 ዓመታት በፊት ፈር ቀዳጅ በመሆን በአሁኑ አጠራር በትግራይ ክልል፣ አዲግራት አውራጃ ጉአላ በተባለ አከባቢ በ 1836 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ያዕቆብ እና በላዛሪስት ሚሲዮናዊያን ጥረት የመጀመሪያውን ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከፍታ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረች የሚታወቅ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሥራዎቿን አጠናክራ በመቀጠል በሃገሪቷ ውስጥ በትምህርት ዘርፉ የማይተካ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።  

 

23 Dec 2025, 16:40