ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ  

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ለጋዛ የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን ማለታቸው ተነገረ

የእየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በስድስት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲሁም ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ ደግሞ የመጀመሪያው በሆነው በጋዛ ሰርጥ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ባደረጉት ንግግር አከባቢው ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለስ ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የጋዛን ሰርጥ በጎበኙ ማግስት ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት የጋዛ ህዝብ ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት እጅግ መዳከሙን ጠቁመው፥ ወደ አከባቢው የመጡት ለዚህ ህዝብ ድጋፋቸውን ለማሳየት እና በእርሳቸው በኩል የመላው ቤተክርስትያን ድጋፍ ለመስጠት እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ራሱን ችሎ አንድን ሉዓላዊ ክልል ሲጎበኙ የመጀመሪያው እንደሆነ ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ አከባቢውን በጎበኙበት ወቅት ስላስተዋሉት ነገር ሲናገሩ 80 በመቶው የመሰረተ ልማት መውደሙን እና ከጥቃት በከፊል የተረፉት አንዳንድ ህንፃዎችም ለመኖሪያነት የማያገለግሉ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ሆኖም ግን አንዳንድ ህንፃዎች በከፍተኛ ደረጃ ውድመት ቢደርስባቸውም ጥቂት ቤተሰቦች አማራጭ ስለሌላቸው ወደ ቤታቸው ለመመለስ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በአባ ገብርኤል ሮማኔሊ በሚመራው የቅድስት ቤተሰብ ደብር ቅጥር ግቢ ውስጥ አሁንም ድረስ አራት መቶ የሚሆኑ ሰዎች ተጠልለው የሚገኙ ቢሆንም፥ ነገር ግን አብዛኞቹ ነዋሪዎች በድንኳን ውስጥ መኖራቸውን እንደቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፥ ብፁዕ ካርዲናሉ በአከባቢው በነበራቸው ቆይታ አየሩ በጣም ቀዝቃዛ መሆኑም ጠቁመው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኙት ህፃናት በጣም እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

ይህ ሁሉ ነገር ቢሆንም ህዝቡ ወደ ቀደመው ሕይወት የመመለስ ፍላጎት እንዳለው ማየታቸውን የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ፥ ሱቆች አሁንም ድረስ መዘጋታቸውን እና ተግዳሮቶቹ እጅግ በጣም ብዙ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ነገር ግን አትክልት እና ፍራፍሬ በሚሸጡባቸው ድንኳኖች ውስጥ አንዳንድ ያልተለመዱ ነገሮችን ማየታቸውን አስታውሰዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ እንዳረጋገጡት የረሃብ አደጋው ያለፈ ቢመስልም ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ጥቂት የጋዛ ነዋሪዎች ምግብ የመግዛት አቅም እንደሌላቸው ገልጸው፥ ያለ ምንም ሥራ እና ገቢ አብዛኛው ሕዝብ በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ከመተማመን ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌለው እና ይህም ለዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ምስጋና ይግባውና በመጨረሻም እርዳታው እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

አስከፊ የኢኮኖሚ ሁኔታ
በአከባቢ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቆሙን የጠቆሙት ፓትርያርኩ ይሄንንም “አስከፊ ሁኔታ” በማለት በሃዘኔታ የገለጹ ሲሆን፥ በተመሳሳይ ጊዜ ክርስቲያኖች ከሁኔታው ለማገገም እና የገናን በዓል ለማክበር ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት ማየታቸው አስታውሰው፥ ትኩረታቸውን ወደ ህፃናት በማዞር የገና በዓል የልጆች በዓል በመሆኑ በእርግጥም ለልጆቹ እና ለወደፊት ህይወታቸው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

“በጎዳና ላይ ያሉ ህፃናት ብዛት ልቤን ነካኝ” ያሉት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ በማከልም ‘ህፃናቱ በዚህ ወቅት ትምህርት ቤት ውስጥ መገኘት እንደነበረባቸው’ ገልጸው፥ የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርኩ ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ጉዳዮች አንዱ የትምህርት ሂደቶችን እንደገና ማስጀመር እንደሆነ በአጽንዖት ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ በጉብኝታቸው ወቅት ያስተዋሉት ህፃናቱ ለትምህርት ያላቸውን ከፍተኛ ጉጉት መሆኑን አስታውሰው፥ እነዚህ ህፃናት አንድ ቀን የማህበረሰቡን ህይወት እንደሚያድኑ እና እንደሚቀይሩ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

የክርስቶስን ልደት ተስፋ መመስከር
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ መልሶ ግንባታው መቼ ሊጀመር እንደሚችል ያላቸውን ጥያቄ አንስተው፥ ጦርነቱ ቢቆምም ነገር ግን ግጭቱ አሁንም ድረስ መኖሩን ጠቁመዋል።

የዌስት ባንክን ጉዳይ እንዲሁም በፍልስጤማዊያን መንደሮች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች መካከል ያለውን ውጥረት በመጥቀስ ችግሮች በሁሉም ቦታ እንዳሉ የጠቆሙ ሲሆን፥ በዚህ አውድ ውስጥ ስለ ተስፋ መናገር አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን በዚህ የገና ሰሞን ይህን ማድረግ የእኛ ግዴታ ነው ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ በጦርነቱ ከባድ መከራ የደረሰባቸውን የክርስቲያን ማህበረሰቦችን ጥልቅ ድካም አስታውሰው፥ ሆኖም ግን ‘ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ወደዚህ ዓለም የመጣው ውስብስብ በሆነ እውነታ’ ውስጥ መሆኑን አስረድተው፥ ዛሬ፣ በተስፋ እንደገና ልንቀበለው እንደሚገባ እንዲሁም ለቤቶች መልሶ ግንባታ እና ለተስፋ ጠንክረው መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

መልሶ ለመገንባት ሁሉንም ነገር ማድረግ
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ከሁለት ዓመት በላይ በቆየው የሰብዓዊ ውድመት በኋላ በተቻለ መጠን ወደፊት መመልከት እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን፥የተፈጠረውን ነገር ችላ ማለት እንደማይቻል እና ነገም ቢሆን ሰላም ይመጣል ብለው ማመን እንደማይቻል ጠቁመው፥ “ነገር ግን ከተቃውሞ ሁኔታ ወደ ገንቢ ሁኔታ መሄድ አለብን” ብለዋል።

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ለጋዛ ህዝብ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው ጠቁመው፥ በአሁኑ ጊዜ የመድሃኒቶች እጥረት ያለባቸው የሆስፒታል መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው እንደሆነ እና የህክምና መሳሪያዎችም በአስቸኳይ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት እንዳለባቸው አሳስበው፥ ለዚህ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እና ህዝቡን ማገልገል እንደሚገባ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ በመቀጠል ለጋዛ ህዝብ ሊደረግ የሚገባውን መንፈሳዊ እና የሃዋሪያዊ አገልግሎት ድጋፍ በማብራራት “እንደ ቤተክርስትያን በማገልገል መቆየት አለብን” ያሉ ሲሆን፥ በመጨረሻም እንደ ቤተክርስቲያን ለጋዛ መረጋጋትን ለማምጣት የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ “ለድሆች እና በጦርነት ምክንያት ለሚሰቃዩ ሁሉ ድምጽ ለመሆን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን” በማለት አጠቃለዋል።

23 Dec 2025, 13:29