ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በጋዛ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በጋዛ   (AFP or licensors)

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ከብርሃነ ልደቱ ቀደም ብለው ወደ ጋዛ መግባታቸው ተነገረ

የእየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ወደጋዛ አምርተው የቅድስት ቤተሰብ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሃዋሪያዊ ሥራዎችን እየጎበኙ ሲሆን፥ ብርሃነ ልደቱን አስመልክቶ እሁድ ዕለት የሚደረገውን መስዋዕተ ቅዳሴ ይመራሉ ተብሎም ይጠበቃል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የገና በዓል ከመድረሱ ቀደም ብለው ወደ ጋዛ በመጓዝ እዛ የሚገኘውን የቅድስት ቤተሰብ ቁምስናን እየጎበኙ ነው።

የእርሳቸው በስፍራው መገኘት ከምዕመናን ጋር በተስፋ፣ በአንድነት እና በጸሎት አብሮ ለመጓዝ ያላቸውን ፍላጎት ይገልጻል ተብሏል።

በዚህ የገና በዓል ባለፈው ዓመት እንደተከበረው ሁሉ፥ የቁምስናው ምዕመናን ከብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ድጋፍ እና ትብብር እንደሚያገኙ ተገልጿል።

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ የገና በዓልን ለማክበር ወደ ጋዛ የተጓዙት ከሞንሲኞር ዊሊያም ሾማሊ እና ከጥቂት ልዑካን ጋር እንደሆነ ተነግሯል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው የቅድስት ቤተሰብ ቁምስናን ሃዋሪያዊ ሥራዎች ለመጎብኘት እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህም መሰረት ታህሳስ 19፣ እሁድ ዕለት በሚከበረው የጎረጎሳዊያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓል ላይ የሚከናወነውን መስዋዕተ ቅዳሴ ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በእነዚህ ቀናት “የሰበካውን ነባራዊ ሁኔታ፣ የሰብአዊ እርዳታዎች፣ የእርዳታ ጥረቶች እና የወደፊት ተስፋዎችን ይገመግማሉ” ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ስለ ማህበረሰቡ ፍላጎት እና ሰበካውን ለመደገፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አስመልክቶ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ከአካባቢው የሃይማኖት አባቶች እና ምዕመናን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ተይዟል።

በመግለጫው መሰረት ይህ ጉብኝት “በመከራ ውስጥ የሚገኘው ማኅበረሰብ ዘንድ የገና አከባበር መጀመሩን የሚያመለክት ነው” የተባለ ሲሆን፥ በተጨማሪም በጋዛ በምትገኘው የቅድስት ቤተሰብ ቁምስና እና በዋናው ሃገረ ስብከት ማለትም በኢየሩሳሌም የሚገኘው የላቲን መንበረ ፓትሪያርክ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ያረጋግጣል ተብሏል።

22 Dec 2025, 14:36