በባንቴይ ሜንቼይ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የቀድሞ ገበያ ቦታ ላይ በተዘጋጀው ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚያገለግል ጊዜያዊ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች - ታኅሣሥ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ፣ ካምቦዲያ በባንቴይ ሜንቼይ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የቀድሞ ገበያ ቦታ ላይ በተዘጋጀው ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚያገለግል ጊዜያዊ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች - ታኅሣሥ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ፣ ካምቦዲያ  (AFP or licensors)

በካምቦዲያ እና ታይላንድ መካከል ግጭቱ ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የካምቦዲያ ወጣቶች የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው ተነገረ

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በካምቦዲያ እና በታይላንድ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ በካምቦዲያ የባታምባንግ ሐዋርያዊ አስተዳደር ወጣቶች የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛን የሰላም ጥሪ በመቀበል የአካባቢው ማህበረሰብ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች ለእግዚአብሔር አደራ በመስጠት የስብከተ ገናን ወቅት እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው አሳይተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከአራት ወራት በፊት የተቀሰቀሰው የታይላንድ እና የካምቦዲያ የድንበር ግጭት በማሌዥያ እና በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥረት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበሩት ሁለቱ አገራት ወደ አዲስ ግጭት አምርተዋል።

ታይላንድ ጦርነቱ የተጀመረው የካምቦዲያ ጦር በድንበር አካባቢ የታይላንድ ወታደሮችን ለመሰለል ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ባሰማራችበት ጊዜ እንደሆነ ስትገልጽ፥ ካምቦዲያ በበኩሏ የታይላንድ ወታደሮች ወደ ክመር-ሂንዱ ቤተመቅደስ በመውጣት የቀደመውን ስምምነት ጥሰዋል በማለት ትከሳለች።

በሁለቱም ሃገራት መካከል የተከሰተው ግጭት ተጠናክሮ በመቀጠል፥ ታህሳስ 4 ቅዳሜ ጥዋት ላይ ሁለቱም ወገኖች የቦምብ እና የከባድ መሳሪያ ልውውጦችን ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ጦርነቱ እንደገና ከተቀሰቀሰ በኋላ ከሁለቱም ወገኖች ቢያንስ 21 ሰዎች መገደላቸው እና 700,000 ሰዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።

በካምቦዲያ የባታምባንግ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ኤንሪክ ፊጋሬዶ ሁኔታውን አስመልክተው እንደተናገሩት “ከፍተኛ የውጥረት ጊዜ” መሆኑን ገልፀው፥ ህዝቡ በስጋት ውስጥ እንደሚገኝ እና ከ 200,000 በላይ ካምቦዳዊያን መፈናቀላቸውን ገልፀዋል።

አባ ፊጋሬዶ የቫቲካን ዜና ወኪል ከሆነው ፊደስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ ታኅሣሥ 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ባደረጉት ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ያቀረቡት የሰላም ጥሪ ትልቅ መጽናኛ እና ተስፋ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

የተከሰተው ነገር ምንድነው?
የሁለቱ አገራት ውዝግብ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ፈረንሳይ ካምቦዲያን በወረረችበት ወቅት የሁለቱ አገራት ድንበር ማስመሯን ተከትሎ የመጣ እንደሆነም ይነገራል።

እ.አ.አ. እስከ 1953 ዓ.ም. ድረስ ካምቦዲያ በፈረንሳይ ቁጥጥር ሥር እንደነበረች የሚታወቅ ሲሆን፥ ፈረንሳይ በ 1907 ዓ.ም. ይፋ ያደረገችውን የሁለቱ አገራት የድንበር መስመር ተከትሎ ሁለቱ ወገኖች በግዛት ይገባኛል ሲጋጩ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።

የድንበር ውጥረቱ እንደገና ማገርሸቱ በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ የግዛት ይገባኛል ውዝግብ ያባባሰው ሲሆን፤ በተለይም በጥንታዊ የቤተመቅደስ ቦታዎች ዙሪያ ያለው አለመግባባት ዋነኛው ነው ተብሏል።

ጥቅምት ወር ላይ በማሌዥያ እና በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥረት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበሩት ሁለቱ ሃገራት ህዳር 28 ዳግም ወደ አዲስ ግጭት አምርተዋል።

አባ ፊጋሬዶ የህዝቡን ጭንቀት እና ስቃይ በመጥቀስ የአጥቢያ ቤተክርስትያን ህዝቡን ለመርዳት እያደረገች ያለውን ጥረት አስታውሰው፥ ህዝቡ ግጭቱ የተባባሰበትን ምክንያት ሁሌ እንደሚጠይቅ በማንሳት በእሳቸው አመለካከት የፖለቲካ እንቅስቃሴው የታይላንድ ጦር ከውጭ ጠላት ጋር እያደረገ ባለው በዚህ ጦርነት ወቅት እንኳን ሳይቀር የሃገር አንድነትን ለማስጠበቅ በሚል ምክንያት ተጨማሪ ቦታዎችን እንዲፈልግ ማድረጉን ጠቅሰው፥ የሃገር ውስጥ ፖለቲካ ለግጭቱ መባባስ ሁነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም ግን የታይላንድ ወጣቶች ይህን አካሄድ እንደማይደግፉ እና የሰላም ጥሪ እያቀረቡ እንደሆነም አስታውሰዋል።

በታላቅ ስቃይ መካከል ያለው የገና ተስፋ
አባ ፊጋሬዶ በቅርቡ በባንቴይ ሚንቼይ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የስደተኞች ካምፕ መጎብኘታቸውን አስታውሰው፥ ሕፃናትን ጨምሮ በካምፑ ውስጥ የሚገኙት 800 የሚሆኑ ሴቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች የተረሱ ሆነው እንደሚሰማቸው በመግለጽ፥ የዓለም ህብረተሰብ እየደረሰባቸው የሚገኘውን ስቃይ ችላ ማለቱን በሃዘኔታ እንደነገሯቸው አስታውሰዋል።

“በዚህም ምክንያት የቅዱስ አባታችን የሰላም ጥሪ የተስፋ ምልክት ነው” ያሉት ካህኑ፥ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የሰላም ጥሪ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በካምቦዲያ የምትገኘው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መረጋጋት ያቃተው እና በጥርጣሬ ውስጥ የሚገኘው ህዝቡ ችግሩን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ለመስጠት አሁን ያለንበትን የስብከተ ገና ወቅት እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀመችበት መሆኑን የገለጹት አባ ፊጋሬዶ፥ ህዝቡ በመከራ ወቅት በጸሎት መተባበር፣ መግባባት እና መተሳሰብ የበለጠ አንድ እንደሚያደርጋቸው አሳስበው፥ ይህም ብርሃነ ልደቱን ከማክበራቸው በፊት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ተስፋ ሊሰጣቸው እንደመጣ ያስታውሳቸዋል ብለዋል።

ግጭቱ ሰብዓዊነት ላይ ያደረሰው ጉዳት
ከህዳር 28 ጀምሮ የተባባሰው ግጭት ከፍተኛ የሰብአዊ ጉዳት እንደነበረው የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም ግጭት 13 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው፣ 60 ሰዎች መቁሰላቸው፣ እንዲሁም ከ190,000 በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ከአከባቢው የሚወጡ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይሄንን ተከትሎ ካሪታስ ካምቦዲያ በስድስት ግዛቶች ውስጥ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ እና ድጋፍ ለማቅረብ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በጋራ እየሰራች መሆኑን የጠቀሱት የካሪታስ ካምቦዲያ ዋና ዳይሬክተር ኪም ራታና፥ ተቋማቸው ‘ለ3,200 ቤተሰቦች የምግብ፣ የውሃ፣ የትምህርት፣ የጥበቃ እና የስነ-ልቦና ድጋፍ’ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአራት ግዛቶች ውስጥ ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚያገለግሉ 20 አዳዲስ ካምፖችን መገንባታቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፥ ካምፖቹ “1,500 ጊዜያዊ መጠለያዎች፣ የምግብ ድጋፍ እና ለ5,000 ቤተሰቦች የንፅህና አጠባበቅ አገልግሎቶች እንዲሁም ለህፃናት እና ለአዋቂዎች የስነ-ልቦና ድጋፍ እና ጥበቃ” እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

15 Dec 2025, 13:32