በቤተልሔም ከሁለት ዓመታት በኋላ የገና በዓል እንደሚከበር ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የክረምቱን ወቅት በጊዜያዊ ድንኳኖች ውስጥ ሆነው ቅዝቃዜውን እየተጋፈጡ ባሉበት እና አስቸኳይ መሰረታዊ እርዳታ በሚፈልጉበት፣ እንዲሁም በጋዛ ሰርጥ ደካማ የሆኑ የእርቅ ስምምነቶች በተደረገበት በአሁኑ ወቅት በመላው ዌስት ባንክ ክብረ በዓላት መከበራቸውን ቀጥለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከህዝቡ ጋር ያላትን ቅርበት እና አንድነት ለማሳየት በቅርቡ በአከባቢው ብቸኛው የካቶሊክ ደብር የሆነውን በጋዛ የሚገኘውን የቅድስት ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያንን ጎብኝተው መመለሳቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው ከኢየሩሳሌም ወደ ቤተልሔም የሚደረገውን ልማዳዊ ጉዞ በማድረግ የገና አከባበርን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ቦታ በሆነችው ቤተልሔም አስጀምረዋል።
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ መንገር አደባባይ ሲደርሱ እንደተናገሩት በቁጥር አነስተኛ ከሆነው እና ለመልሶ ግንባታ ከፍተኛ ጉጉት ካለው የጋዛ ክርስቲያን ማህበረሰብ የከበረ ሰላምታ ይዘው መምጣታቸውን ገልጸው፥ ማህበረሰቡ በብርሃን የተሞላውን የገና በዓል ለማክበር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በቤተልሔም የገና አከባበር እንደገና መጀመሩ በተለያዩ ደረጃዎች ትልቅ ትርጉም እንዳለው የተነገረ ሲሆን፥ በአንድ በኩል፣ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት የሚመራው እና በአሜሪካ የሚደገፈው የሰላም ተነሳሽነት ፍልስጤማውያን በመልሶ ግንባታ ዕቅዶች እንዲራመዱ እድል ሊሰጥ ይችላል የሚል ተስፋ ያለ ሲሆን፥ በሌላ በኩል፣ 85 በመቶው የአካባቢው ቤተሰቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጦርነቱ ወቅት የቆመው ቱሪዝም ላይ ጥገኛ ስለሆኑ የቤተልሔም ነዋሪዎች ቀስ በቀስ ወደ ሥራ ይመለሳሉ የሚለውን ተስፋ ያድሳል ተብሏል።
የሆቴል ባለቤቶች እና ሠራተኞች፣ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን የሚሸጡ ሱቅ ነጋዴዎች፣ የታክሲ ሹፌሮች፣ የምግብ ቤት ባለቤቶች እና አስጎብኚዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ የሚታወቅ ሲሆን፥ ቤተልሔም ጠንካራ የኢንዱስትሪ መሰረት፣ ጉልህ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የግብርና አቅም እና ትልቅ የሰው ሃይል ስለሌላት በዌስት ባንክ ክልል በጦርነቱ ምክንያት በጣም ከተጎዱ ከተሞች ውስጥ አንዷ መሆኗ ይነገራል።
እነዚህ ችግሮች እስራኤል ለአብዛኛዎቹ ወቅታዊ ፍልስጤማዊያን ሰራተኞች ወደ ግዛቷ እና የሰፈራ አከባቢዎቿ የመግባት ፈቃድን መሻሯን፣ እንዲሁም ለፍልስጤማዊያን አስተዳደር ሰራተኞች ከፊል ደመወዝ መክፈልን ጨምሮ ሰፊውን የዌስት ባንክ ግዛትን በሚነኩ ተግዳሮቶች መባባሳቸው ተነግሯል።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ህዝቡ ጽናትን እና ተስፋን ማሳየቱን ቀጥሏል።
የቤተልሔም ከንቲባ ማኸር ኒኮላ ካናዋቲ ከቫቲካን ረዲዮ ባልደረባ ዣን ቻርለስ ፑትዞሉ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ከሁለት ዓመት በኋላ የሚከበረው ይህ በዓል ተስፋን ለመመለስ እንደሚረዳ ገልጸው፥ “ከሁለት ዓመታት ዝምታ በኋላ የገናን መንፈስ እንደገና እንደምናቀጣጥለው እናምናለን፥ ምክንያቱም የቤተልሔም ሰዎች ተስፋ ያስፈልጋቸዋል፥ የተሻለ ነገን ተስፋ ማድረግ፥ ያደረግነውም ይህንኑ ነው” ብለዋል።
ከቤተልሔም እየተላከ ያለው መልዕክት ለፍልስጤማውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለምም ጭምር መሆኑን ያስረዱት ከንቲባው፥ የፍልስጤም ህዝብ ለሰላም ዝግጁ መሆኑን እና ህይወትን እንደሚወድ የሚገልጽ መልዕክት እንደሆነ ገልጸው፥ ቤተልሔም ሰላም መሆኗን እና ሆቴሎች ክፍት መሆናቸውን ጠቁመው ከተማዋ ጎብኝዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን በአጽንዖት ገልጸዋል።
ከንቲባ ካናዋቲ አክለውም የበዓሉ አከባበር ሁሉም ፍልስጤማውያን ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ሳይገድባቸው በጋራ እንደሚካፈሉ ገልጸው፥ በዓሉ “ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን የመላው ፍልስጤማውያን በዓል ይመስላል” ያሉ ሲሆን፥ በመጨረሻም “ክርስቲያኖች፣ እስላሞች እና ሳምራውያን እኛ ሁላችን አንድ ህዝቦች ነን። እርስ በርሳችን እንዋደዳለን፣ ሰላምን እንወዳለን፥ ፍትህን፣ ሰላምን እና ዘላቂ ሰላም በአገራችን ለማስፈን ዝግጁ ነን” በማለት አጠቃለዋል።