ፈልግ

ታህሳስ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ በሚገኘው ቦንዲ ባህር ዳርቻ አይሁዳዊያን ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ህዝቡ አበባ እና ሻማ በማብራት አጋርነቱን እየገለጸ ይገኛል  ታህሳስ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ በሚገኘው ቦንዲ ባህር ዳርቻ አይሁዳዊያን ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ህዝቡ አበባ እና ሻማ በማብራት አጋርነቱን እየገለጸ ይገኛል  

የአውስትራሊያ ጳጳሳዊ ተልዕኮ በሲድኒ ከተማ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘ

ታህሳስ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ በሚገኘው ቦንዲ ባህር ዳርቻ ላይ ዓመታዊ ክብረ በዓላቸውን ሲያከብሩ በነበሩ አይሁዳዊያን ላይ በተፈጸመው የጅምላ ጥቃት ቢያንስ ከ15 ሰዎች በላይ መሞታቸውን እና 25 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተከትሎ፥ በአውስትራሊያ የጳጳሳዊ ተልዕኮ ማኅበራት ቡድን ጥቃቱን በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እሁድ ዕለት የተፈጸመውን ይሄንን ጥቃት ተከትሎ የካቶሊክ ተልዕኮ የሆነው የአውስትራሊያ የጳጳሳዊ ተልዕኮ ማኅበራት አስተዳደር በአውስትራሊያ ውስጥ ለእንዲህ ዓይነቱ ዘግናኝ ጥቃት የሚሆን ቦታ አለመኖሩን ገልፆ፥ በዚህ አደጋ ለተጎዱት ሁሉ የተሰማቸው ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

ፊደስ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው ድርጅቱ ይህ ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት የቦንዲ ባህር ዳርቻ ላይ ከነበሩት ሰዎች ጋር፣ ከሞቱት ወይም ጉዳት ከደረሰባቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው እንዲሁም ከመላው አውስትራሊያዊያን ጋር ያለውን አጋርነት ገልጿል።

ከተፈፀመው ጥቃት ጀርባ አባት እና ልጅ እንዳሉበት የአገሪቱ ባለሥልጣናት ይፋ ያደረጉ ሲሆን፥ ጥቃቱ የተፈፀመው አይሁዶች በሒብሪው ቋንቋ 'ሃኑካህ' ወይም 'ቻኑካህ' በመባል የሚታወቀውን በዓል እያከበሩ በነበረበት ወቅት እንደነበር እና በየዓመቱ የሚከበረው ሃኑካህ ብዙውን ጊዜ በኅዳር ወይም ታኅሳስ ወር ላይ የሚውል ሲሆን ለስምንት ቀናት እንደሚቆይም ይታወቃል።

‘የካቶሊክ ተልዕኮ ለሰላም፣ ለስምምነት፣ ለውይይት፣ ለጋራ መግባባት እና መከባበር መስራቱን ይቀጥላል’ ያለው መግለጫው፥ በድርጅቱ ፌስቡክ ገጽ ላይ የተለጠፈውንም ጸሎት አቅርቧል።

የአውስትራሊያ ብፁዓን ጳጳሳት መግለጫ
በአውስትራሊያ የሚገኘው የጳጳሳዊ ተልዕኮ ማኅበራት ትስስር የአውስትራሊያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባዔ ለሰጡት መግለጫ ያላቸውን ድጋፍ የገለጹ ሲሆን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው የአመፅ እና የሽብር ተግባሩ አውስትራሊያውያንን በእጅጉ እንዳስደነገጠ ገልጸው፥ የንጹሐን ሰዎች ሕይወት መጥፋት እጅግ አሳዛኝ ክስተት እንደሆነ ብሎም የሟች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በድርጊቱ ልባቸው እንደሚሰበር ገልጸዋል።

ይሄንን እጅግ አስከፊ ድርጊት የፈፀሙ ሰዎችን ያነሳሳው የተዛባ የፀረ-ሴማዊነት አስተሳሰብ ጋር በግልጽ የተያያዘ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፥ ‘በመቻቻልና በእውነተኛ እንግዳ ተቀባይነት በምትታወቀው ሃገር ይህ ጭፍን ጥላቻና የተዛባ አመለካከት በህብረተሰቡ ላይ ጥቁር ጠባሳን’ እንደሚጥል ያመላከቱ ሲሆን፥ “ይህም አይሁዳዊ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም የሚያስፈራ ድርጊት ነው” ብለዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ እንዲህ ያለውን አስከፊ ጥቃት የሚያወግዙትን ሁሉ እንደሚቀላቀሉ እና ሁሉም አውስትራሊያውያን ለጥላቻ እና ለጥቃት የሚገፋፋውን ሃሳብ እንዲተው በመጠየቅ፥ ከዚህም ይልቅ በቤተሰቦቻቸው፣ በጓደኞቻቸው እና በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ውስጥ የሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ተማጽነዋል።

ስለ ጥቃቱ
የሃገሪቱ ባለስልጣናት ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ የ50 ዓመት እና የ24 ዓመት እድሜ ያላቸው አባት እና ልጅ መሆናቸውን በማመላከት ድርጊቱ ‘አይ ኤስ ወይም እስላማዊ መንግሥት ተብሎ በሚጠራው ቡድን አነሳሽነት የተፈጸመ የሽብር ጥቃት’ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ ጥቃቱን የፈፀመው የ50 ዓመቱ ግለሰብ ጥቃት በተፈጸመበት ስፍራ በጸጥታ አስከባሪዎች ሲገደሉ፥ የ24 ዓመቱ ልጃቸው ግን በጽኑ ቆስሎ በሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገለት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቦንዲ የባሕር ዳርቻ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በአውሮፓውያኑ 1996 በአርተር ወደብ ላይ ከተፈፀመው እና 35 ሰዎች ከተገደሉበት ጥቃት ወዲህ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ሲሆን፥ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔስ ጥቃቱን "ሰይጣናዊ የሆነ ፀረ ሴማዊ ድርጊት" ብለውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስትራሊያውያን ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ እራሳቸውን አደጋ ውስጥ ሲከቱ ተመልክተናል ያሉ ሲሆን፥ እነዚህ አውስትራላዊያን ጀግኖች እንደሆኑ እና ጀግንነታቸው በርካታ ሕይወትን እንደታደገ በመግለጽ ጥቃቱን ለመከላከል የሞከሩ ግለሰቦችን አወድሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የ 24 ዓመቱ ተጠርጣሪ እ.አ.አ. ጥቅምት 2019 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የአውስትራሊያ የስለላ ድርጅት አይን ውስጥ የገባ የአውስትራሊያ ዜግነት ያለው ወጣት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔስ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ 25 ሰዎች በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 10 ያህሉ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ከእነዚህም መካከል በአውስትራሊያ አይሁዶች ላይ ጥቃት የፈጸመውን ታጣቂ መሳሪያውን የነጠቀው የ 43 ዓመቱ አህመድ አል አህመድ አንዱ ሲሆን፥ የሁለት ልጆች አባት እና የፍራፍሬ ሱቅ ባለቤት የሆነው አሕመድ እጁ እና ክርኑ ላይ በጥይት በመመታቱ የሕክምና እርዳታ እያገኘ እንደሆነ ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።

እሑድ ዕለት በተፈፀመው በዚህ ጥቃት ከሆሎኮስት ጥቃት የተረፉ አንድ የእድሜ ባለጸጋ እና የ10 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ 15 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 42 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ ገልጿል።

ከአደጋው በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጥቃቱ የተፈጸመበት የቦንዲን ባህር ዳርቻ በመጎብኘት አክብሮታቸውን ለመግለጽ በጊዚያዊ መታሰቢያ ቦታ ላይ አበባዎችን በማስቀመጥ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

17 Dec 2025, 12:58