ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሕግ ታራሚዎች ኢዮቤልዩ ላይ መስዋዕተ ቅዳሴ ሲመሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሕግ ታራሚዎች ኢዮቤልዩ ላይ መስዋዕተ ቅዳሴ ሲመሩ   (@Vatican Media)

የሕግ ታራሚዎች ኢዮቤልዩ በቫቲካን በተከበረበት ወቅት ታራሚዎችን ማስታወስ የወንጌል አካል መሆኑ ተነገረ

ታኅሳስ 05 ቀን 2018 ዓ.ም የሕግ ታራሚዎች ኢዮቤልዩ በቫቲካን የተከበረ ሲሆን፥ የኢዮቤልዩ ተሳታፊ የነበሩት የህግ ታራሚዎች ይህ በዓል መከበሩ በቤተክርስቲያኒቷ ማዕከል ውስጥ እንደ አንድ ጠንካራ የአካታችነት ምልክት ይታያል ማለታቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተከበረው የሕግ ታራሚዎች ኢዮቤልዩ ላይ የተገኘው ጆሹዋ ስታንስል በዚህ ክብረ በዓል ላይ መገኘት በህይወት ዘመን ውስጥ ብዙ ጊዜ የማይገኝ ተሞክሮ መሆኑን ገልፆ፥ በሰሜን ካሮላይና ማረሚያ ቤት ውስጥ እያለ ከአሥርት ዓመታት በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ለህግ ታራሚዎች በተዘጋጀው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ እገኛለው ብሎ ፈጽሞ ሃሳቡ እንዳልነበረው ገልጿል።

ጆሹዋ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የካቶሊክ የማረሚያ ቤት አገልግሎት ጥምረት ክፍል በሆነው የ ‘ክሬቲቭ ኮንቴንት’ ቡድን ሃላፊ እና ከማረሚያ ቤት ወደ ህብረተሰቡ ለሚቀላቀሉ ሰዎች ድጋፍ እና ግብዓቶችን የሚያቀርበው ‘በእምነት መኖር’ የተሰኘ ተነሳሽነት መስራች ሲሆን፥ በ 2006 ዓ.ም. ከመለቀቁ በፊት 18 ዓመታትን በማረሚያ ቤት አሳልፏል።

ታህሳስ 5 ከዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር በተለየ ሁኔታ ለታራሚዎች በተዘጋጀው ለመጀመርያው የኢዮቤልዩ ዝግጅት ላይ የተገኘው ጆሹዋ፥ አካታችነት ታሪካዊ እና እጅግ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ገልጿል።

“ያልተጣለ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ያካተተ”
በሦስተኛው የስብከተ ገና ሳምንት በተካሄደው የህግ ታራሚዎች ኢዮቤልዩ ዝግጅት ወቅት ከቫቲካን ዜና ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገው ጆሹዋ፥ በእስር ላይ ለነበሩ ሰዎች ጠንካራ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፥ በርካታ የቀድሞ ታራሚዎች ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ የሚሰማቸው ዘላቂ ቁስል በቋሚነት ሊሰማቸው እንደሚችል አረጋግጦ፥ “ከማረሚያ ቤት ስትወጣ በግንባርህ ላይ ‘ከማረሚያ ቤት የተለቀቀ’ የሚል ምልክት እንዳለ ነገር ቢያንስ በአሜሪካ ውስጥ የመገለል ስሜት ይሰማሃል” በማለት ከገለጸ በኋላ፥ ወደ ቤተክርስቲያን እንኳን መመለስ የማይፈቀድልህ ይመስልሃል ብሏል።

የታራሚዎች ኢዮቤልዩ ይህን አመለካከት በቀጥታ እንደሚቀይር የገለጸው ጆሹዋ፥ በዚህ ዝግጅት በተወሰነ ቦታ ብቻ ሳይሆን በቤተክርስቲያኒቱ እምብርት ውስጥ መካተታቸውን እንደተነገራቸው ገልፆ፥ በተለምዶ የደስታ ምልክት በሆነው በሦስተኛው የስብከተ ገና ሳምንት መከበሩ ደግሞ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ጠቁሞ፥ ‘አልተጣልክም’ ከመባል እና ‘ጅማሮህ በእውነት አዲስ ጅምር ነው’ ከመባል የበለጠ ምንም የሚያስደስት ነገር ዬለም ብሏል።

መርሃ ግብር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር የመገናኘት ዕድል ነው
ጆሹዋ በማረሚያ ቤት ያሳለፈውን ዓመታት በማሰላሰል ለመንፈሳዊ እድገት እድሎች ብዙውን ጊዜ ከተቋማዊ አሰራር ይልቅ በግል ግንኙነት ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ በመግለጽ፥ በመንግስት በሚተዳደሩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ስለ ሃይማኖት ብዙ ጥርጣሬዎች እንዳሉ እና አብዛኛውን ጊዜ እውነተኛ መንፈሳዊ እድገት የሚመጣው ከአንድ ካህን፣ ገዳማዊያት እህቶች ወይም በጎ ፈቃደኛ ሰው ጋር በተደጋጋሚ ስትገናኝ እንደሆነ አስረድቶ፥ ይህ ሁኔታ የገጠመው በድንገት እርሱን መጎብኘት በጀመሩ የካቶሊክ ምዕመናን አባላት አማካኝነት እንደሆነ በመግለጽ፥ በማረሚያ ቤት ውስጥ የአንድን ሰው ማንነት የሚቀይረው ነገር ፕሮግራም ወይም ፕሮጀክት ሳይሆን ‘ራሳቸው በክርስቶስ የተለወጡ ሰዎችን ማግኘት’ እንደሆነ አብራርቷል።

         “በእስር ቤት ውስጥ በእውነት የሚቀይረው ነገር እራሳቸው በክርስቶስ የተለወጡ ሰዎችን ማግኘት ነው”

ይህ የጸና እምነት በአሁኑ ወቅት በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የማረሚያ ቤት አገልግሎትን ለመደገፍ እና ለማስፋፋት ጥረት እያደረገ ከሚገኘው የካቶሊክ የማረሚያ ቤት አገልግሎት ጥምረት ጋር እየሰራ ያለውን ሥራ እንዳመቻቸለት የገለጸው ጆሽዋ፥ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ታስሬ ጠይቃችሁኛል” ብሎ የተናገረውን በማስታወስ፥ “የማረሚያ ቤት አገልግሎት ብዙውን ጊዜ የተረሳ የምሕረት ሥራ ነው” በማለት ተናግሯል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እና የሞራል ግልጽነት
ለሕግ ታራሚዎች ኢዮቤልዩ በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ባደረጉት ንግግር ከመጠን በላይ መጨናነቅ እና የተሃድሶ ፕሮግራሞች አለመኖርን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የማረሚያ ቤት ስርዓቶችን የሚነኩ መንፈሳዊ እይታ እና መዋቅራዊ ችግሮችን ያነሱ ሲሆን፥ ጆሽዋ ይሄንን አስመልክቶ እንደተናገረው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይሄንን ሲናገሩ ‘የሞራል ግልጽነት’ እንዳላቸው ጠቅሶ፥ቅዱስነታቸው የሚናገሩትን ነገር በጥልቀት አስበውበት እንደሆነ መናገር ይቻላል ብሏል።

የማካተት መልዕክት
ጆሹዋ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን የአካታችነት መልዕክት በመጥቀስ የእስረኞች ስቃይ ከአጠቃላይ የቤተክርስቲያኑ ሕይወት መለየት እንደማይቻል በአጽንዖት ገልፆ፥ ‘አንዱ የቤተክርስቲያኑ ክፍል እየተሰቃየ ከሆነ፣ በአንዳንድ መልኩ ቤተክርስቲያኒቷ ራሷ እየተሰቃየች መሆኑን’ እንደሚያሳይ በማስታወስ፥ ሆን ተብሎም ይሁን ባለማወቅ ችላ ማለቱ ዘላቂ ቁስሎችን እንደሚያስከትል አስጠንቅቋል።

ማረሚያ ቤት ውስጥ ያሉትን ችላ ማለት የወንጌልን ማዕከላዊ ሃሳብ መቃወም እንደሆነ ያስረዳው ጆሽዋ፥ የትኛውንም ቡድን ማግለል መላውን ሰውነት እንደሚያዳክም፣ ብሎም የቤተክርስቲያንን የምሕረት፣ የፈውስ እና የኅብረት ጥሪን እንደሚያደበዝዝ ገልጿል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን ቃል በማስተጋባት ሁሉም ሰው ሊወድቅ እንደሚችል እና ሁሉም ሰው እንደገና እንዲነሳ መፍቀድ እንደሚገባ በድጋሚ በማስታወስ፥ “እንደ ታራሚዎች ያሉ ሰዎችን ችላ ማለት ከክርስቲያናዊ መልዕክት ጋር ይቃረናል” ብሏል።

                 “እንደ እስረኞች ያሉ ሰዎችን ማግለል ከክርስቲያናዊ መልእክት ጋር የሚጋጭ ነው”

ፈታኝ የሆነ መገለል፣ ሕያው ቤዛነት
ጆሹዋ ከዓመታት በፊት የቅጣት ፍርዱን ቢጨርስም፥ መገለል አሁንም ድረስ እንደሚሰማው በማስታወስ፣ ይህ ስሜት በቀላሉ እንደማይጠፋ ጠቅሶ፥ ብዙውን ጊዜ የንስሃ አንዱ ክፍል በቀላሉ ከሃጥያት መራቅ መሆኑን ገልጿል።

“በቂ ንስሐ እንደገባሁ ማንም ጠይቆኝ አያውቅም” ያለው ጆሹዋ፥ ወዳጅነት በቀላሉ እንደሚቀርብ እና ይህም ሁሉንም ነገር እንደሚለውጥ ገልፆ፥ ይህ ተመሳሳይ መርህ በሰሜን ካሮላይና ከረዥም እስራት በኋላ እንደገና ወደ ህብረተሰቡ ለሚቀላቀሉ ወንዶች ጊዜያዊ ቤቶችን የሚያቀርበውን የራሱን አነስተኛ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት እንደሚመራ ገልጿል።

የቤተክርስቲያን ሁለንተናዊነት
ጆሽዋ ወደ ቤቱ ሲመለስ የኢዮቤልዩ ዘላቂ አሻራ የቤተክርስቲያን ሁለንተናዊነት መሆኑን እንደተረዳ ገልፆ፥ በሕይወት ዘመኑ የተለያየ ዘር፣ ቋንቋ እና ባህል ያላቸው ይሄን ያህል ሰው አይቶ እንደማያውቅ ተናግሯል።

የህግ ታራሚዎች ኢዮቤልዩ በማረሚያ ቤት ላሉትም ሆነ በቅርብ ጊዜ ለተፈቱት የተስፋ ምልክት ብቻ ሳይሆን ለመላው ቤተክርስቲያን ማሳሰቢያ እንደሆነ የገለጸው ጆሽዋ፥ በመጨረሻም፥ “ለታራሚዎች የሚሰጥ የተስፋ መልዕክት ውሎ አድሮ ለሁሉም ሰው የተስፋ መልዕክት ነው” በማለት አጠቃሏል።

       “ለታራሚዎች የሚሰጥ የተስፋ መልእክት ውሎ አድሮ  ለሁሉም ሰው የተስፋ መልእክት ነው”

16 Dec 2025, 14:23