ፈልግ

በጄኒን የተቃጠለው የገና ዛፍ በጄኒን የተቃጠለው የገና ዛፍ 

የኢየሩሳሌም እና ፍልስጤም ሐዋርያዊ ልዑክ ‘ክርስቲያኖች ተስፋ አይቆርጡም’ ማለታቸው ተነገረ

በእስራኤል የቅድስት መንበር ተወካይ እንዲሁም የኢየሩሳሌም እና የፍልስጤም ሐዋርያዊ ልዑክ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አዶልፎ ቲቶ ኢላና በቅርቡ በዌስት ባንክ ጄኒን ከተማ በሚገኘው ሆሊ ሬዲመር ቤተክርስቲያን የገና ዛፍ ላይ ስለደረሰው የእሳት ቃጠሎ ጥቃት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የገና በዓል ሊከበር ጥቂት ቀናት ብቻ በቀረበት ሰኞ ታኅሣሥ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በዌስት ባንክ ጄኒን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ሆሊ ሬዲመር ቤተክርስቲያን ለብርሃነ ልደቱ በተዘጋጀው የገና ዛፍ ላይ አክራሪ ናቸው በተባሉ ወጣት ሙስሊሞች በተፈጸመው የጥፋት ድርጊት ሙሉ በሙሉ መቃጠሉ ተነግሯል።

ሆኖም ግን ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የአከባቢው ማህበረሰብ በኢየሩሳሌም የላቲን መንበረ ፓትርያርክ ኃላፊ ከሆኑት ከብፁዕ አቡነ ዊልያም ሾማሊ እና ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በመሆን አዲስ የገና ዛፍ በስፍራው ማኖራቸው ተገልጿል።

በእስራኤል የቅድስት መንበር ተወካይ እንዲሁም የኢየሩሳሌም እና የፍልስጤም ሐዋርያዊ ልኡክ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አዶልፎ ቲቶ ኢላና ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ይህ ድርጊት ሁሉም የክርስቲያን ማህበረሰቦች አልፎ ተርፎም የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ያልሆኑ ሰዎች በጦርነቱ እና በተለያዩ ምክንያቶች ከሁለት ዓመታት በኋላ ማክበር በጀመሩት የገና በዓል መንፈስ ደስታ ላይ ጥልቅ እና ከባድ ጥላ እንደሚያጠላ ገልጸዋል።

“እዚህ የምንኖረው በወንድማማችነት መንፈስ ስለሆነ ይህን የጥቃት ተግባር አጥብቀን እናወግዛለን” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ካቶሊኮች፣ ኦርቶዶክሶች እና ሌሎች ክርስቲያኖች የገናን በዓል ለማክበር እንዴት በጋራ እንደሚሰበሰቡ አስታውሰዋል።

ሊቀ ጳጳስ ኢላና በማከልም በራስ ወዳድነት አስተሳሰባቸው ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን መቀበል እንደማይችሉ ገልጸው፥ ይሄንን ድርጊት በጽኑ እንደሚያወግዙ እና ጥቃት አድራሾቹ የማህበረሰቡን ጥልቅ ደስታ እንዲሰርቁ እንደማይፈቅዱ አስረድተዋል።

ህዝቡን አንድ የሚያደርገው ተስፋ
ከሁለት ዓመት በኋላ ብርሃንን ማየታችን እና መተንፈስ መቻላችን ብቻ ሳይሆን፥ የገና በዓል እግዚአብሔር እንዳልተወን የሚያረጋግጥልንን መልዕክት የምናይበት በዓል እንደሆነ እናውቃለን ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ‘አምላካችን አልረሳንም፣ ሁሌም ከእኛ ጋር ነው፥ ይህ ደግሞ የደስታችን ምንጭ ነው’ ካሉ በኋላ፥ ይሄንን በዓል ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሙስሊሞች እና ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ሁሉ እንደሚያዩት እና እንደሚቀላቀሉ አስረድተዋል።

“የምንሰጠው ተምሳሌታዊ ተግባር እነሱንም ሊለውጣቸው ይችላል” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይህን የዓመፅ ድርጊት ለፈጸሙ ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ የጠየቁ ሲሆን፥ ተስፋ ለአካባቢው ህዝብ ቃል ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ የሆነ ነገር እንደሆነ አስታውሰው፥ “ተስፋ የምንተነፍሰው አየር ነው” ካሉ በኋላ በቤተሰቦቻችን እና በማህበረሰባችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዬትኛውም ሁኔታ ውስጥ የምንተነፍሰው አየር ነው” ብለዋል።

“ተስፋ ከእኛ ጋር ያለ እና እኛ የምናስብበት መንገድ ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ኢላና በመጨረሻም፥ “ከሁለት ዓመት በኋላ ያልዘነጋነው እና ደስታ በልባችን ውስጥ ያበበው በዚህ ምክንያት ነው” በማለት አጠቃለዋል።

24 Dec 2025, 13:33