የዘንድሮው የዓለም የድሆች ቀን መሪ ሃሳብ፥ “ዕዳን ወደ ተስፋ መቀየር” የሚል መሆኑ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቤተ ክርስቲያን ዘጠነኛውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀንን በምታከብርበት በዚህ ወቅት፥ የአውሮፓ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አሊያንስ (ELSiA)፥ የአውሮፓ ኅብረት ድህነትን ለማጥፋት የሚደረጉ ጥረቶችን እና ዘላቂ ልማትን የሚያደናቅፈውን ዓለም አቀፍ የዕዳ ቀውስ ለመፍታት እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2018 ዓ. ም. የተመሠረተው የአውሮፓ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” አሊያንስ (ELSiA)፥ የር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳንን በአውሮፓ ውስጥ ሕያው ለማድረግ በጋራ የሚሠራ “ካሪታስ አውሮፓን ጨምሮ ሰባት የካቶሊካዊ ድርጅቶች አንድነት ሲሆን፥ የኅብረቱ ተልዕኮ፥ በፖሊሲ ተሟጋችነት እና በዘላቂ የአኗኗር ዘይቤዎች ተግባራዊ ተነሳሽነቶች “በቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራዊ ትምህርት ላይ የተመሠረተ ሥነ-ምህዳራዊ ፍትህን ማስፋፋት ነው” ሲሉ በካሪታስ አውሮፓ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ የትብብር ሃላፊ ሉዊሳ ፎንዴሎ ገልጸዋል።
“ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ራዕይ ለፍጥረት እና ለድሆች እንክብካቤ፥ በአውሮፓ ፖሊሲዎች እና ማኅበረሰቦች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ተጨባጭ እንዲሆን ለማድረግ ጥምረት ፈጥረናል” ሲሉ ሉዊሳ ፎንዴሎ አስረድተዋል።
በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2017 ዓ. ም. የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “እኔ ወድጄሃለሁ” በሚለው የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ምክረ-ሃሳብ በድጋሚ የተረጋገጠ እና ኅብረቱ የአውሮፓ ፖሊሲ አውጪዎች የሰውን ልጅ ክብር በኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ማዕከል እንዲሆን የሚያቀርበውን ጥሪ ለማደስ ዕድል እንደሚሰጥ ታውቋል።
በታሪክ እጅግ የከፋው የዕዳ ቀውስ
የአውሮፓ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አሊያንስ ጥሪ ማዕከል የሆነው ዓለም አቀፍ የዕዳ ቀውስ፥ ከመቶ በላይ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን አገራት የሚነካ፥ በታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋ እንደ ሆነ ሉዊሳ ፎንዴሎ ገልጸዋል።
“በአሁኑ ጊዜ 3.4 ቢሊዮን ሰዎች በጤና አጠባበቅ ወይም በትምህርት ከሚከፈል የወለድ ክፍያዎች በላይ በሕዝብ ዕዳ ላይ በሚከፍሉ አገሮች ውስጥ ይኖራሉ” ሲሉ ገልጸው፥ ይህም የድህነት ቅነሳ ጥረቶች በከፍተኛ ሁኔታ እያዳከመው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ድህነት በገንዘብ እጦት ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ አፅንዖት የሰጡት ሉዊሳ ፎንዴሎ፥ እንዲሁም ለሰብዓዊ ክብር አስፈላጊ የሆኑ የትምህርት፣ የጤና አጠባበቅ እና የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን እንደሚያካትት አስረድተው፥ “ድህነትን በስፋት ከተመለከትን የዕዳ ቀውስ በአውሮፓ ኅብረት አጀንዳ ውስጥ ግንባር ቀደም መሆን እንዳለበት ግልጽ ይሆናል” ብለዋል።
የአውሮፓ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አሊያንስ ዓለም አቀፍ የድሆች ቀንን በማስመልከት ባወጣው መግለጫው፥ የአውሮፓ ኅብረት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ዲሞክራሲያዊ እና ግልጽ የሆነ ዓለም አቀፍ የዕዳ መፍቻ መንገድ መፍጠርን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርቧል። እንዲህ ዓይነቱ ማዕቀፍ ጥምረቱ እንደሚለው፥ የዕዳ ድርድሮች በፍትሃዊነት እና በሲቪል ማኅበረሰብ ተሳትፎ እንዲካሄዱ የሚያረጋግጥ እና ይህም ከፋይናንስ ገበያዎች ይልቅ ለሰዎች ፍላጎት ቅድሚያን እንደሚሰጥ ተገልጿል።
የኢዮቤልዩ ዓመት የፍትህ ጥሪ
ሉዊሳ ፎንዴሎ ኅብረቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. ያቀረበውን የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት አውድ ጥሪን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ በተለምዶ ከእርቅ እና ከተሃድሶ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለድሃ አገራት ዕዳቸውን መቀነስ የኢዮቤልዩ በዓል አንዱ አካል አድርገው ማየታቸውን የገለጹት ሉዊሳ ፎንዴሎ፥ አሁን ደግሞ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክት መደገሙን አስታውሰዋል።
“የአውሮፓ ኅብረት ይህን የኢዮቤልዩ ዓመት በቁም ነገር እንዲመለከተው እንፈልጋለን” ያሉት ሉዊሳ ፎንዴሎ ዓመቱ ምሳሌያዊ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ እና ድሆችን መርዳት እና ለዕዳ ቀውስ መፍትሄን ማግኘት የበጎ አድራጎት ጥያቄ ከመሆኑ በፊት የፍትህ ጉዳይ ነው” ሲሉ አስረተዋል።
ለኅብረተሰቡ የሞራል ፈተና መሆን
የዓለም የድሆች ቀን ለሉዊሳ ፎንዴሎ እና ለአውሮፓ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አባላት ዓመታዊ መታሰቢያ ብቻ ሳይሆን የሞራል መለኪያ እንደ ሆነ ታውቋል። “ማኅበረሰቦቻችን እና ፖሊሲዎቻችን ድህነት፣ መድልዎና ጭቆና የሚያጋጥማቸውን ሰዎች የሚይዙበት መንገድ ማንነታችንን በብዙ መንገድ ይገልጻል ያሉት ሉዊሳ ፎንዴሎ፥ “ለኅብረተሰብ መሠረታዊ የሞራል ፈተና ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የኅብረቱ መግለጫ ይህንን እምነት ያስተጋባል ያሉት ሉዊሳ ፎንዴሎ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “እኔ ወድጄሃለሁ” በሚለው የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ምክረ-ሃሳባቸው፥ “ደካሞችን በመደገፍ ወሳኝ እና ሥር ነቀል ምርጫ ያድርጉ” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን በማስታወስ፥ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች የሰው ልጅ ዋጋን በመገንዘብ በትብብር፣ በማካተት እና በጋራ ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ ባለብዙ ወገን ሥርዓት በመገንባት እንዲመሩ ያሳስባል።
“አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎቶች ለሃብታም አበዳሪዎች ከፍተኛ ወለድ ያላቸውን ብድሮች ለመክፈል ስለሚገደዱ መምህራን እና ነርሶች እየተሰዉ ነው” ያለው መግለጫው፥ ያለ ማሻሻያ የዕዳ አለመመጣጠንን መጨመር፥ የአየር ንብረት እርምጃን በማዳከም ልማትን ማደናቀፍ እንደሚቀጥል በማስጠንቀቅ፥ ይህም ሁሉንም ሀገራት የሚነካ የድህነት ዑደት እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ለሞራል አመራር ጥሪ
የአውሮፓ ኅብረት እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መንገድም ሆነ የሞራል ኃላፊነት እንዳለበት አጥብቀው የተናገሩት ሉዊሳ ፎንዴሎ፥ “አውሮፓ ህብረት በተባበሩት መንግሥታት ደረጃ የዕዳ መፍትሄ ማዕቀፍ እንዲቋቋም በመደገፍ እውነተኛ አመራርን ማሳየት ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል። “ይህ ሁሉም ሰው መኖሪያ ቤት፣ ምግብ፣ የጤና አጠባበቅ እና ትምህርት አገልግሎት ወዳለበት የወደፊት ጊዜ ለመድረስ ትልቅ እርምጃ ይሆናል” ብለዋል።
በዚህ የአውሮፓ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አሊያንስ የዓለም የድሆች ቀን ጥሪ፥ “የፍትህ እና የሰላምን መንገድ በመምረጥ ከረሃብ፣ ከድህነት እና ከስቃይ ጋር በሚታገል ዓለም ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹን መንከባከብ ከወንጌል ግዴታ ጋር የሚስማማ መሆኑን አስረተዋል።
ዕዳን ወደ ተስፋ መለወጥ
“ዛሬ ሊቋቋሙት የማይችሉት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ነገር ግን ካሪታስ አውሮፓ እና አጋሮቿ የሕዝብን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ዕድገትን ለማስፋፋት እና ዕዳን ወደ ተስፋ ለመቀየር ዘመቻ የጀመሩት ለዚህ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“በተስፋ እንመራለን” ያሉት ሉዊሳ ፎንዴሎ፥ “በዚህ ዓመት ዕድገት ማየታቸውን፥ ተጨማሪ ፖለቲከኞች ስለ ዕዳ ጉዳይ እያወሩ መሆናቸውን እና እንደ አፍሪካ ኅብረት ያሉ ተቋማት በተባበሩት መንግሥታት የዕዳ መፍትሄ ላይ ድጋፍ እያደረጉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በዓለም ዙሪያ ላሉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ክፍት የሆነው ዘመቻ፥ ዜጎች ፍትሃዊ የዕዳ ሥርዓትን ለመደገፍ የቀረበውን ጥሪ እንዲፈርሙ በመጋበዝ፣ በፍትህ እና በአንድነት የሚያምን ሁሉ ዘመቻውን መቀላቀል ይችላል” ሲል ሉዊሳ ፎንዴሎ በማከል፥ turndebtintohope.caritas.org የሚለውን ድረ-ገጽ በቀላሉ የሚያገኙት መሆኑንም አስረድተዋል።