በደቡባዊ ታይላንድ ሃት ያህ ከተማ ላይ የደረሰውን ታሪካዊ የጎርፍ አደጋ ተከትሎ የታይ ቤተክርስቲያን አስቸኳይ እርዳታ ማድረጓ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሶንግላ ግዛት ሥር የሚገኙ 16ቱም ወረዳዎች የአደጋ ቀጠና ተብለው የተፈረጁ ሲሆን፥ ከ465,000 በላይ ነዋሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የአካባቢው ባለስልጣናት ዘግበዋል።
የጎርፍ አደጋው በደቡባዊ ታይላንድ ውስጥ የተከሰተ ሰፊ አደጋ አካል መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የሃገሪቱ የአደጋ መከላከል እና ቅነሳ ዲፓርትመንት በአሁኑ ወቅት በዘጠኝ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ወደ 2.1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና 13 ሰዎች ደግሞ በአደጋው መሞታቸውን ገልጿል።
ድንገተኛ አደጋው ተሽከርካሪዎችን ማስመጡን እና ሆስፒታሎችን ማስተጓጎሉ
ህዳር 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት በሃት ያህ ከተማ የጎርፍ ውሃው ሌሊት ላይ ከዘነበው ከባድ ዝናብ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም የተነሳ በርካታ ሰፈሮች በጎርፉ መዋጣቸውን እና ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ በመስመጣቸው የነፍስ አድን ሰራተኞች ያለረዳት የቀሩ ቤተሰቦችን ለመድረስ እየታገሉ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የጎርፍ ውሃው በአካባቢው በሚገኙ የሆስፒታል ክፍሎች ውስጥ በመግባት ለአደጋ የተጋለጡ ህሙማን የሚደረገውን እንክብካቤ አስቸጋሪ እንዳደረገው፥ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የመብራት እና የኮሙዩኒኬሽን መቆራረጥ እንደተከሰተ የተነገረ ሲሆን፥ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የውሃው መጠን እስከ ሁለት ሜትር ከፍታ ላይ መድረሱን የአከባቢው ባለስልጣናት አመላክተዋል።
በ 25 ዓመታት ውስጥ የከፋ የተባለው የጎርፍ አደጋ የጅምላ መፈናቀል እንዲከሰት ማድረጉ
አውራጃው በሩብ ምዕተ ዓመት ውስጥ እጅግ የከፋ የተባለለት የጎርፍ አደጋ ስላጋጠመው ሰኞ ዕለት የሶንግላ ገዥ የሃት ሃይ ከተማ ነዋሪዎችን ወደ ጊዜያዊ መጠለያዎች በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን፥ የአከባቢው ባለሥልጣናት በ 300 ዓመታት ውስጥ አንዴ የሚከሰት የዝናብ ዓይነት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአደጋ በጣም ከተጎዱት መካከል ቱሪስቶች ዋነኞቹ ሲሆኑ፥ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦችን ጨምሮ በርካታ የታይላንድ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ከተማዋን ለቀው መውጣት እንዳልቻሉ እና መንገዶቹ በጎርፉ በመዋጣቸው ምክንያት መጓዝ ስላልቻሉ አንዳንዶቹ በሃት ያህ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ከሦስት ቀናት በላይ እንደቆዩ ተነግሯል።
ከዚህም በተጨማሪ ከቅዳሜ ጀምሮ በርካታ የማሌዢያ ቱሪስቶች ውሃ እና መብራት በሌለባቸው ሆቴሎች ውስጥ ማረፋቸው ተገልጿል።
ከባንኮክ በስተደቡብ በ900 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የሶንግህላ ግዛት ዋና አውራጃ የሆነችው ሃት ያህ የደቡቡ ክልል የንግድ እና የመጓጓዣ ማዕከል ስትሆን፥ ቅዳሜ እና እሁድ የማሌዢያ ተጓዦች ዋና መዳረሻ እንደሆነች ተገልጿል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአደጋ ጊዜ ምላሽን ማስተባበሯ
ለዚህ አስከፊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የሱራት ታኒ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፖል ትሬይሮንግ ሙልትሪ በቤተክርስቲያን የሚመሩ የእርዳታ ስራዎችን በክልሉ ዙሪያ ለማሰባሰብ ማክሰኞ ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት ቡድኑ አፋጣኝ የድርጊት መርሃ ግብር በመዘርዘር የንፁህ መጠጥ ውሃ ስርጭት፣ የምግብ አቅርቦቶች፣ የህክምና ድጋፍ፣ የነፍስ አድን እርዳታን እና የምግብ ማቅረቢያ ማዕከልን ለማዘጋጀት ከካቶሊክ የአደጋ ጊዜ እርዳታ እና ስደተኞች ቢሮ (COERR) ጋር በመተባበር ወደ ተግባር መግባቱ እና ከዚህም በተረፈ ዕቅዶቹ የጎርፍ ውሃው ከቀነሰ በኋላ የተቀናጀ የእርዳታ ፓኬጆችን ማቅረብን እንደሚያካትት ተነግሯል።
ብፁዕ አቡነ ፖል ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ለሊካስ ኒውስ እንደተናገሩት የእርዳታ ቡድኑ ረቡዕ ጠዋት ከካቶሊክ የአደጋ ጊዜ እርዳታ እና ስደተኞች ቢሮ ጋር በመሆን የመጠጥ ውሃ እና አስፈላጊ ነገሮችን ለተጎዱ ሰዎች ማቅረብ እንደሚጀምር ገልጸው፥ ከባንኮክና ከሌሎች ሃገረ ስብከቶች ተጨማሪ ዕቃዎች በቅርቡ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የእርዳታ ጥሪዎች መጨመራቸው
የባንኮክ ካህናት እና ምዕመናን አደጋው ወደተከሰተበት የሃገሪቱ ደቡብ ክልል ለማድረስ መዋጮ ማሰባሰብ እንደጀመሩ የተነገረ ሲሆን፥ የባንኮክ ሃገረስብከት ካህን የሆኑት አባ ቾናፓት ሱካናቴ በፌስ ቡክ ገፃቸው ባቀረቡት አስቸኳይ የእርዳታ ጥሪ ‘በተለምዶ እርዳታ እንደማያሰባስቡ ገልጸው’ ነገር ግን በሃት ያህ በደረሰው ከባድ የጎርፍ አደጋ ምክንያት ሐሙስ ዕለት የመጠጥ ውሃ፣ የታሸጉ ምግቦችን፣ የዱቄት ወተት፣ ዳይፐር፣ ልብስ፣ መድኃኒት፣ የዝናብ ካፖርት፣ ጃንጥላ እና የመሳሰሉትን በመያዝ ወደ ሱራት ታኒ ሀገረ ስብከት እንደሚሄዱ ገልጸው ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በሃገሪቱ ደቡባዊ ክልል አሁንም አስቸጋሪ ሁኔታ መኖሩ
በሰሜን እና በማዕከላዊ ክልሎች የጎርፍ መጠኑ እየቀነሰ መሆኑ ቢነገርም፥ በደቡቡ ክልል ከፍተኛ የዝናብ መጠን በመቀጠሉ ክልሉ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ የመንግስት ኤጀንሲዎች አስጠንቅቀዋል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጠባብ እና ቁልፍ የትራንስፖርት መስመሮች በመቋረጣቸው ምክንያት ወደስፍራው ለመድረስ አስቸጋሪ ስለሚሆን፥ የሚቀጥሉት 48 ሰአታት አሁንም ድረስ እየጨመረ በሚሄደው ውሃ ተይዘው ለሚገኙ በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ወሳኝ እንደሚሆን ባለሥልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በቤተክርስቲያን ላይ የተመሰረቱ የእርዳታ ድርጅቶች፣ የመንግስት ኤጀንሲዎች እና የአካባቢ በጎ ፈቃደኞች ብዙዎቹ ከጊዜ ጋር የሚደረግ ውድድር ብለው በገለጹት በጣም የተቸገሩትን ለመድረስ የማስተባበር ሥራቸውን እንደቀጠሉ ተገልጿል።