ፈልግ

ህዳር 4 ቀን 2018 ዓ. ም. ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የተዘገቡ ዜናዎች ህዳር 4 ቀን 2018 ዓ. ም. ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የተዘገቡ ዜናዎች  (AFP or licensors)

ህዳር 4 ቀን 2018 ዓ. ም. ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የተዘገቡ ዜናዎች

በዚህ ሳምንት ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ለቫቲካን ዜና ከደረሱ ዜናዎች መካከል፥ የሮማኒያ ግሪክ ካቶሊኮች አዲስ ሊቀ ጳጳስ ማግኘታቸው፣ ቱርክ ውስጥ የሚገኘው የክርስቲያን መንደር የጥንቱን አረማይክ ስሙን መልሶ ማግኘቱ እና የሶሪያ ክርስቲያኖች ወደ አል-ጋሳኒያህ መመለሳቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች ይገኙበታል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አዲሱ የሮማኒያ ዋና ሊቀ ጳጳስ
ሊቀ ጳጳስ ክላውዲዩ ሉቺያን ፖፕ አዲሱ የሮማኒያ ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆነው መሾማቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ የብፁዕ ካርዲናል ሙሬስያንን ሞት ተከትሎ በሃገሪቱ ብፁዓ ጳጳሳት ሲኖዶስ ጥቅምት 26 መመረጣቸው ተነግሯል።

እ.አ.አ. በ 1972 ዓ.ም. የተወለዱት ሊቀ ጳጳሱ፥ በ 1995 በኦራዲያ ሃገረ ስብከት ማዕረገ ክህነት መቀበላቸው እና በቡካሬስት ከተማ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኬሚስትሪን እና ፍልስፍናን እንዲሁም የሥነ መለኮት ትምህርታቸውን በሮም ከተከታተሉ በኋላ በፓሪስ የሮማኒያን ግሪክ-ካቶሊክ ተልዕኮን፣ ከዚያም ጳጳሳዊውን የሮማኒያ ኮሌጅን የመሩ ሲሆን፥ በ 2011 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ የጵጵስና እንደተሾሙ እና ከ 2021 ዓ.ም. ጀምሮ በሮማኒያ ሲያገለግሉ እንደነበር ግለ ታሪካቸው ያስረዳል።

አርቦ የአራማይክ ስሙን መልሶ ማግኘቱ
በቱርኪዬ የሚገኘው የአሦር-ሲሪያክ መንደር የሆነው የ‘አርቦ’ መንደር የጥንቱን ትክክለኛ የአረማይክ ስሙን በይፋ መልሶ ያገኘ ሲሆን፥ ለአንድ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ‘ታሽኮይ’ በሚል ቱርክኛ ስም ይታወቅ እንደነበር ተገልጿል።

በደቡብ ምስራቅ ቱርኪዬ በሚገኘው ኢዝሎ ተራራ ላይ የምትገኘው የአርቦ መንደር እ.አ.አ. በ 1915 ዓ.ም. በተከሰተው የአሦራውያን የዘር ማፅዳት ከመጀመሩ በፊት የበለፀገች መንደር እንደነበረች እና ከ 2006 ጀምሮ ከአውሮፓ የሚመለሱ ቤተሰቦች ቤታቸውን መልሰው መገንባት እንደጀመሩ፥ ይህም አሁን በስፍራው የሚገኘውን ነዋሪ ወደ 80 ማድረሱ ተገልጿል።

የመጀመሪያ ስሙን ለማግኘት ከቤቴ ኩስታን ቀጥሎ በቱርኪዬ ውስጥ ሁለተኛው የአረማይክ መንደር መሁኑም የተነገረ ሲሆን፥ “እንኳን ወደ አርቦ በደህና መጡ” የሚል ምልክት በአምስት ቋንቋዎች ማለትም በአራማይክ፣ በቱርክኛ፣ በኩርዲሽ፣ አረብኛ እና እንግሊዝኛ ተጽፎ መቀመጡ ተገልጿል።

የሶሪያ ክርስቲያኖች ወደ አል-ጋሳኒያህ መመለሳቸው
በሶሪያ ኢድሊብ አቅራቢያ የምትገኘው የአል-ጋሳኒያህ የክርስቲያን መንደር ነዋሪዎች በሀገሪቱ በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከአስራ ሶስት ዓመታት ተገደው ከተሰደዱ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤታቸው የተመለሱ ሲሆን፥ እነዚህ ክርስቲያኖች በጦርነቱ ምክንያት በፈረሰው ቤተ ክርስቲያናቸው ፊት ለፊት በተሰበሰቡበት ወቅት፣ የላታኪያ የግሪክ ኦርቶዶክስ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ አትናሴ ፋህድ “የመመለስን ተስፋ ስንጠብቅ ነበር… ዛሬ ተመልሰናል፥ በመሆኑም በዚህች ምድር ላይ ሁሌም ጸንተን እንኖራለን” ብለዋል።

14 Nov 2025, 13:09