ወንድና ሴት «በእግዚአብሔር አምሳል» መፈጠራቸውን የምንገነዘበው እንዴት ነው?
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መባርቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
እግዚአብሔር ወንድና ሴትን የፈጠረው ለምን ዓላማ ነው?
እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ለሰው ጥቅም ፈጠረ፤ ሰዎች የተፈጠሩት ደግሞ እግዚአብሔርን እንዲያውቁ፣ እንዲያገለግሉና እንዲወዱ፣ የዚህን ዓለም ፍጥረት ሁሉ መልሰው ለእርሱ በምስጋና መልክ እንዲያቀርቡና በሰማይ
ከእርሱ ጋር ወደ ሚኖራቸው ሕይወት ከፍ እንዲሉ ነው።
የሰው ልጅ ምስጢር እውነተኛ ትርጉም የሚኖረው ሥጋ በለበሰው ቃል ምሰጢር ብቻ ነው። ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ «የማይታይ አምላክ ፍጹም አምሳያ» (ቆላ. 1፡15) ነው። ወንድና ሴትም የዚህን አምሳያ ለመፍጠር ከመጀመሪያው የታጩ ናቸው።
የሰው ዘር አንድ የሆነው ለምንድነው?
የጋራ መገኛው እግዚአብሔር ስለሆነ የሰው ዘር በሙሉ አንድ ነው። እግዚአብሔር «ሕዝቦችን በሙሉ ከአንድ የዘር ሐረግ ፈጠረ» (የሐዋ. 17፡26)። ሁሉም አንድ አዳኝ ብቻ አላቸው፣ ሁሉም በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ደስታ እንዲካፈሉ ተጠርተዋል።
ነፍስና ሥጋ በሰው ውስጥ አንድ የሚሆኑት እንዴት ነው?
የሰው ልጅ በአንድ ላይ ሥጋዊም መንፈሳዊም ነው። በሰው ውስጥ መንፈስና ቁስ አንድ ባህርይ ይኖራቸዋል። ይህ አንድነት እጅግ መሠረታዊ ከመሆኑና ነፍስ ከሆነው ከመንፈሳዊው መምሪያ የተነሣ ቁሳዊ የሆነው ሥጋ ሕያው
የሰው አካል ሆኖ ከእግዚአብሔር አምሳል ክብር ይጋራል።
ነፍስ ከየት መጣች?
ረቂቅ ነፍስ የምትገኘው ከወላጆች ሳይሆን ወዲያውኑ በእግዚአብሔር የተፈጠረችና ዘለዓለማዊት ናት። ነፍስ በሞትጊዜ ከሥጋ ስትለይ አትጠፋም፣ በመጨረሻ ትንሣኤ ጊዜም ተመልሳ ከሥጋ ጋር ትዋሐዳለች።
እግዚአብሔር በወንድና በሴት መካከል የመሠረተው ወዳጅነት ምንድነው?
ሁለቱም ሰዎች በመሆናቸው ወንድና ሴት እኩል ክብር ያላቸው የእግዚአብሔር ፍጡራን ናቸው። ተባዕትና እንስት በመሆናቸውም የተፈጠሩት በመደጋገፍ እንዲኖሩ ነው። ሰብአዊ ህብረት ፈጥረው እንዲኖሩና አንዳቸው ለሌላው እንዲሆኑ እግዚአብሔር ፈቀደ። በተክሊል «አንድ ሥጋ» (ዘፍ.2፡24) ሆነው ሰብአዊ ሕይወትን ለሌላ እንዲያስተላልፉ ተጠርተዋል። እንደዚሁም እንደ እግዚአብሔር «ባለሟልነታቸው» ምድርን እንዲገዙ ተሰይመዋል።
በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት የሰው ልጅ የመጀመሪያ ሁኔታ ምን ነበር?
እግዚአብሔር ወንድና ሴትን ሲፈጥር በቅድስናና በጽድቅ በእሱ መለኮታዊ ሕይወት ውስጥ በልዩ ሁኔታ እንዲሳተፉ ፈቅዶላቸው ነበር። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት መሠቃየት ወይም መሞት አልነበረባቸውም። ከዚህ በተጨማሪ፣ በራሱ በሰው ውስጥ፣ በፍጥረትና በፈጣሪ መካከል፣ በወንድና ሴት መካከል፣ በመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስትና በመላው ፍጥረት መካከል ፍጹም ስምምነት ነበር።
ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካጸደቁት፣ በአጭሩ ከተጻፈው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ከዋናው ከላቲን ቅጂ ከተተረጎመው መጽሐፍ ከአንቀጽ 340-384 ላይ የተወሰደ።