በካልካታ ያሉ ክርስቲያኖች ለሁሉም ሰው ክብር ያለው የቀብር ቦታ የማግኘት ተነሳሽነት ማስጀመራቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
‘የሁሉም ነፍሳት ቀን’ ተብሎ በየዓመቱ የሚከበረው የዘንድሮ መታሰቢያ ቀን በህንድ ካልካታ ለሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰብ ከአንድ ቀን በላይ የሚቆይ መርሃ ግብር ያለው ሲሆን፥ በዘንድሮው የመታሰቢያ ቀን “ሻማን ሳማዲ” ወይም ‘የተከበረ የቀብር ሥነ ሥርዓት’ የተሰኘ ማንኛውም ሰው በሚሞቱበት ጊዜ ክብር ያለው የቀብር ሥነ ስርዓት እንዲደረግለት የሚያግዝ ተነሳሽነት ማስጀመራቸው ተገልጿል።
በካልካታ የክርስቲያን የቀብር ሥነ ስርዓት ቦርድ መሠረት ይህ አዲስ የተጀመረው ፕሮጀክት “የርህራሄ እና የአካታችነት ምልክት” እንዲሆን ታስቦ የተነደፈ ተነሳሽነት ሲሆን፥ በውስጡም የተለያዩ የክርስቲያን ቤተ እምነቶች ተወካዮችን እንድ ላይ እንዳሰባሰበ ተነግሯል።
ሁሉም በክብር መቀበር ይገባቸዋል
ከዚህም በተጨማሪ የክርስቲያን የቀብር ሥነ ስርዓት ቦርድ እንዳሳወቀው “ሻማን ሳማዲሂ” የተሰኘው ተነሳሽነት ዋና ግቡ ማንኛውም ሰው ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ዳራ እና ሁኔታ ውስጥ ቢሆን፣ ምንም ይሁን ምን ክብር ያለው እና ነፃ የመቃብር ቦታ እንዲሰጠው ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን ገልጿል።
‘አጀንዚያ ፊደስ’ የተሰኘው የቫቲካን የጳጳሳዊ ተልዕኮ ማኅበራት የመረጃ አገልግሎት እንደዘገበው በሞሊክ-ባዘር ከተማ የሚገኘው የካልካታ ታሪካዊ የክርስቲያን መቃብር ቦታ አካል የሆነው ይህ የመቃብር ስፍራ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወጪዎችን መሸፈን ለማይችሉ ቤተሰቦች የተዘጋጀ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ይህ አካባቢ ወዳጅ እና ዘመድ የሌላቸው ተጥለው የተገኙ አስከሬኖችን ለመቀበል ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል።
የማህበረሰብ ተልዕኮ
በእማሆይ ቴሬዛ የተመሰረተው የበጎ አድራጎት ሚሲዮናውያን ማህበርም አንዱ የተልዕኳቸው አካል በማድረግ በዚህ ተነሳሽነት ውስጥ እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህ ተልዕኳቸው ውስጥ የሞት ጣር ውስጥ የሚገኙትን እና የተረሱትን ሰዎች መርዳትንም እንደሚጨምር ተነግሯል።
የበጎ አድራጎት ሚሲዮናውያን ማህበሩ ቀብር ክብር ያለው፣ ሰላማዊ እና የተከበረ በመሆኑ ምክንያት “የሻማን ሳማዲሂ” ተነሳሽነትን በመደገፋቸው የርህራሄ ተልዕኮዋቸውን እንዳሳደገው የገለጹ ሲሆን፥ የካልካታ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ፕሮጀክቱን በደስታ እንደሚቀበል ገልፆ፥ በአካባቢው የልማት ፈንድ በኩል ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።
ለዚህ ተነሳሽነት የተወሰነው የመቃብር ሥፍራ ሁለት ቦታ በመከፈል ወደ መቃብር ስብስቦች እንደተካተተ የተገለጸ ሲሆን፥ አንደኛው ቦታ ለአዋቂዎች፣ ሌላኛው ደግሞ ከሶስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የሚያገለግል እንደሆነ ተነግሯል።
የክርስቲያን የቀብር ሥነ ስርዓት ቦርድ የመቃብር ስፍራውን የመንከባከብ ኃላፊነት መውሰዱ የተገለጸ ሲሆን፥ በካልካታ ውስጥ የሚገኙ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ነዋሪዎች “በርህራሄ፣ በአክብሮት እና በዜጋዊ ሃላፊነት” ለማገልገል በቁርጠኝነት እና በትጋት እንደሚሰራ እና በጎረጎሳዊያኑ አቆጣጠር በ 2026 መጀመሪያ ላይ ሌላ የመቃብር ቦታ በቶሊ-ጉንጌ ከተማ እንደሚያዘጋጅ ቦርዱ አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የክርስቲያን የቀብር ቦርድ አሁን ያሉት ቦታዎች ከእንግሊዞች አገዛዝ ዘመን ጀምሮ የነበሩ እና ሙሉ በሙሉ የተያዙ ስለሆኑ አዲስ የክርስቲያን መቃብር ለመገንባት የከተማውን አስተዳደር ቦታ መጠየቁ ተገልጿል።