ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ 'ሰማዕት በሆነችው ዩክሬን' ውስጥ የሰላም ጥረቶችን ማደስ ያስፈልጋል ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ 81ኛውን የጣሊያን ጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላላ ስብሰባ ለመዝጋት ወደ አሲሲ ከሚያደርጉት ጉብኝት ቀደም ብሎ ብፁዕ ካርዲናል ማትዮ ማሪያ ዙፒ የጣሊያን ጳጳሳት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያጠናክሩ እና የመገለል አደጋ ላይ ያሉትን ሰዎች እንዲከላከሉ አሳስበዋል።
የጣሊያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕረዚዳንት የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ ህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም. አሲሲ ከተማ ውስጥ የሚገኘው እና ‘ዶሙስ ፓሲስ’ ወይም ‘የሰላም ቤት’ ተብሎ በሚጠራው የሳንታ ማሪያ ዴሊ አንጄሊ ባሲሊካ የተጀመረውን 81ኛውን የጣሊያን ጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላላ ስብሰባ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር በመካሄድ ላይ ባሉ ዓለም አቀፍ ግጭቶች እንዲሁም በድሆች፣ በስደተኞች እና በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ላይ የሚደርሰው መገለል የሚያስከትለው ስቃይ ላይ በማጉላት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም የቦሎኛ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ “በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ሴቶች እና ወንዶች መካከል ያለውን እኩልነት ለመመለስ፣ እንዲሁም መብት እና እውነተኛ ፍትህ ለሁሉም ሃገራት እና ህዝቦች ተግባራዊ የሚሆንበትን ወቅት እንደገና ለማስጀመር” ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጉባዔውን ይዘጋሉ ተብሎ ይጠበቃል
ከህዳር 8 እስከ 11፥ ለአራት ቀናት የሚቆየው ይህ ስብሰባ ከመላው ጣሊያን የሚመጡ ብፁዓን ጳጳሳትን አንድ ላይ የሚያሰባስብ ሲሆን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ በቆይታቸው ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ ሃዋሪያዊ ሥራዎች፣ በሰብዓዊ ጥበቃ እና የካቶሊክ ትምህርት ላይ አተኩረው እንደሚወያዩ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ብፁዓን ጳጳሳቱ በውይይታቸው ወቅት በግንቦት ወር ላይ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሚጠናቀቀውን የሃዋሪያዊ መመሪያዎችን በሚያወጣው እና በቅርቡ ከተጠናቀቀው ‘የጣሊያን ሲኖዶሳዊ መንገድ’ ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚወያዩም ተነግሯል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሐሙስ፣ ህዳር 11 ከብፁዓን ጳጳሳቱ ጋር በሳንታ ማሪያ ዴሊ አንጄሊ ባዚሊካ ለመዝጊያ መርሃ ግብር እንደሚገናኙም ይጠበቃል።
ጦርነት በሚነሳበት ጊዜ ሰላምና ልማትን ለማበረታታት ጥሪ ማድረግ
ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ በንግግራቸው በቅድስት ሀገር እና በጋዛ የተደረጉትን የሰላም ተነሳሽነት በመጥቀስ ሰፊ የልማት ትብብርን ያበረታቱ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር በአውሮፓ እና በሜዲትራኒያን ባህር መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር አዲስ ጥረቶች እንዲደረጉ ጥሪ በማቅረብ፥ የአውሮፓን ዘላቂ የሰላም ዕቅድ በመቅረጽ ረገድ በአህጉሪቱ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ሚናቸውን በቁም ነገር እንዲወጡ አሳስበዋል።
የጣሊያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕረዚዳንት የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ በመጨረሻም በጦርነት አረንቋ ውስጥ የሚገኘውን ዓለም በማስታወስ ባደረጉት ንግግር “ሰማዕት በሆነችው ዩክሬን” ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበው፥ በአውሮፓ ለሚደረገው ስብሰባ በትክክል መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን በማጉላት “ክርስቲያኑ አውሮፓ ብዙ የሚናገረው እና የሚያሰላስልበት ነገር ይኖረዋል” በማለት አጠቃለዋል።