ፈልግ

በብራዚል በተካሄደው የኮፕ 30 ጉባዔ ላይ የሃገሬው ተወላጅ የአየር ንብረት ተሟጋች  በብራዚል በተካሄደው የኮፕ 30 ጉባዔ ላይ የሃገሬው ተወላጅ የአየር ንብረት ተሟጋች   (AFP or licensors)

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋማት በኮፕ30 ጉባዔ ላይ ለፍትህ እና ለአየር ንብረት ፋይናንስ ግፊት እንደሚያደርጉ ተጠቆመ

በብራዚል ቤሌም እየተካሄደ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ኮፕ30 ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋማት ተደራዳሪ አካላት ፍትህን መሰረት ያደረገ የአየር ንብረት ፋይናንስ እንዲከታተሉ በማሳሰብ፥ “የምድራችንን እና የድሆችን ጩኸት” ያስተጋቡ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ካፎድ የተሰኘው ተቋም የአየር ንብረት ተጽዕኖ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ካስገባቸው ማህበረሰቦች ጋር የሚሰሩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አጋሮቹን ልምድ ለጉባዔው ተሳታፊዎች ማካፈሉ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የውጪ ሃገራት የልማት ኤጀንሲ (CAFOD) የጥብቅና እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ኔይል ቶርንስ ተቋማቸውን ወክለው በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን፥ ከእሳቸውም በተጨማሪ ሰፊ ጥምረት ያለው ከብሄራዊ የካቶሊክ የአየር ንብረት እና አካባቢ ጉዳይ ጽህፈት ቤት (NCCEAs) ተወካዮች እንዲሁም የቅድስት መንበር ልዑካን በጉባዔው ላይ ተገኝተዋል።

አቶ ቶርንስ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት በዘንድሮው ጉባዔ የተቀናጀ የካቶሊክ ተሳትፎ አስፈላጊነትን በመግለጽ፥ የካቶሊኩ ዓለም እዚህ ጉባዔ ላይ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እምነቱ እንዳላቸው እና በዚህ የላውዳቶ ሲ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ቅድስት መንበር እንደ አንድ የመንግስት ፓርቲ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባት ትችላለች ብለዋል።

ቶርንስ አክለውም የካቶሊክ ቤተክርስቲያ ዋና ተዋናዮች የሆኑት ብፁዓን ካርዲናሎች እና ጳጳሳትን ጨምሮ በላውዳቶ ሲ ውስጥ የተነሱትን ስጋቶች ወደ ድርድር ቦታዎች እያመጡ እንደሆነ ገልጸው፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች “የምድራችንን እና የድሆችን ጩኸት” በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ጉባዔዎች ላይ ለውይይት ማቅረባቸውን አስታውሰው፥ ይህ ትልቅ ተነሳሽነት እንደሆነ አብራርተዋል።

የተስፋ መልዕክት በላውዳቶ ሲ'
የካቶሊክ ተቋማት የቤተክርስቲያኗን የስነ-ምህዳር ስጋቶች በኮፕ 30 ላይ እየተካሄደ ካለው የዲፕሎማሲ ስራ ጋር እንዴት እንደሚያገናኙት የተጠየቁት ቶርንስ፥ የተለያዩ እርምጃዎችን ለማነሳሳት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ ደብዳቤዎች ያላቸውን አቅም ጎላ አድርገው በመግለጽ፥ በዚህም ላውዳቶ ሲ ትልቅ ተስፋ እንደሚያመጣ እና እውነተኛ የተስፋ መልዕክት እንደነበር ገልጸው፥ “ምንም እንኳን መፍትሄዎቹ ከልብ መለወጥ እና ትክክለኛ ግንኙነቶች መሆናቸውን ብናውቅም አሁንም ድረስ ዓለም በችግር ውስጥ ነች” ካሉ በኋላ፥ ‘ሆኖም ግን ይሄንን ልንቀይረው እንችላለን’ ብለዋል።

የካቶሊክ ተዋናዮች የአየር ንብረት ለውጥ በተጋላጭ ማህበረሰቦች ላይ ያለውን ያልተመጣጠነ ተፅእኖ እና ቀውሱን የመፍታት እድልን በማንሳት፥ በዓለም ላይ ለሚገኙ ድሃ ማህበረሰቦች አሳሳቢ የሆነ ወሳኝ መልዕክት ያመጡ ሲሆን፥ ይህም ብቻ ሳይሆን ችግሮቹን ለመፍታት አንድ ነገር ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ የተስፋ መልዕክትም እንዳላቸው ገልጸዋል።

ይህ ተስፋ ለተደራዳሪዎቹም ጭምር የሚያገለግል እንደሆነ የጠቆሙት ቶርንስ፥ የሃይማኖት ሰዎች ያንን የእምነት ቋንቋ ተጠቅመው ለተደራዳሪዎቹ፣ ለሚኒስትሮች እና ለባለስልጣናት ተስፋ እንደሚሰጡበት እና ተጨማሪ እርምጃ እንዲወስዱ እንደሚያሳስቡበት ገልጸዋል።

በመሬት ላይ ያለ ተጽእኖ
አቶ ቶርንስ የካፎድ አጋሮች በመላው ኢስያ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ እንደሚሰሩ በማስታወስ፥ ይህም በመሆኑ የአየር ንብረት ቀውስን አስመልክቶ ያላቸው ልምድ ሰፋ ያለ ስለሆነ ይሄንን ልምድ በተለያዩ መንገዶች ወደ መድረክ ለማምጣት እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል።

የአየር ንብረት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፥ በዝናብ ላይ ብቻ ተማምነው እርሻቸውን የሚያርሱ ሰዎች ዝናቡ አስተማማኝ ስላልሆነ በዝናብ ላይ ብቻ መተማመን እንደማይችሉ፥ ወይም ደግሞ ዝናቡ ከመጣም በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚሆን ማሳቸውን እንደሚያወድምባቸው በመጥቀስ፥ የአየር ንብረት ለውጥ በባህሪው ልዩ ሁኔታ እንዳለው ገልጸው፥ ወቅታዊ የጎርፍ መጥለቅለቅን ለመቋቋም በባንግላዲሽ ውስጥ የሚገኙ ተንሳፋፊ የአትክልት ቦታዎችን ጨምሮ በካፎድ የሚደገፉ እና በማህበረሰብ የሚመሩ ማላመጃ ስፍራዎችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ተለዋዋጭ የአየር ጠባይ ባለባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ የመቋቋም አቅምን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ሃላፊው፥ ካፎድ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖሊሲ ለውጥን የሚፈልጉ ማህበረሰቦችን እንደሚደግፍ ገልጸው፥ በኮፕ ድርድሮች ውስጥ እውነተኛ ልምዶችን ማምጣት አስፈላጊ እንደሆነ እና በዚህም ከፍተኛ ለውጥ ስለሚያመጡ የአጋሮቻቸውን ድምጽ ወደ እነዚህ ማዕከላዊ ቦታዎች ማምጣት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ድርድሮች፡ የመጀመሪያው ሳምንት ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም ሁለተኛ ሳምንት ወሳኝ ነበር
አቶ ቶርንስ በጉባዔው የመጀመሪያዎቹ ክፍለ-ጊዜዎች እንደተለመደው ልዑካኑ ዘንድ አንዳንድ አለመመቸቶች እንዳጋጠማቸው በማስታወስ፥ “የመጀመሪያው ሳምንት የኮፕ ድርድር ሁሌም ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ እና ሚኒስትሮቹ ከመምጣታቸው በፊት ዝርዝር ነገሮችን ለመቀልበስ ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ገልጸዋል።

የመጀመርያው ሳምንት የተመራው ጥብቅ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሚደራደሩ የቴክኒክ ኃላፊዎች ሲሆን፥ ሁለተኛው ሳምንት ግን የተለያዩ ሃሳቦችን ለመስማት ዝግጁ በሆኑ ሚኒስትሮች እንደሆነ አስረድተዋል።

የአየር ንብረት ፋይናንስ እና የፈጠራ አስፈላጊነት
የሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ሃገራት በዚህ ዓመት ለመደራደር የበለጠ ፈቃደኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ የተጠየቁት ሃላፊው፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ አደጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ጠቁመው፥ ሰዎች ይህ የሙቀት መጨመር ማህበረሰቦችን በጣም እየጎዳ መሆኑን እየተመለከቱ እንደሆነ እና በዚህም ምክንያት ፋይናንስ በኮፕ ጉባዔ የሁሉም ነገር ማዕከል እንደሆነ አመላክተዋል።

አቶ ቶርንስ በተጨማሪም አገራዊ የአየር ንብረት ዕቅዶችን መተግበር እና ከከባድ አደጋዎች ለማገገም ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልፀው፥ ካፎድ የብድር እፎይታ እና የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያዎችን የሚያካትቱ ሀሳቦችን ማቅረቡን ተናግረዋል።

                       “የአየር ንብረት ቀውስ ያስከተሉ ሀገራት ተጠናክረው ድጋፍ ማደግ አለባቸው”

የአየር ንብረት ፋይናንስ እንደ ፍትህ ጉዳይ
አቶ ቶርንስ ‘ለችግር የተጋለጡ ሃገራት በበለጸጉ ሃገራት ፊት አቤቱታ አቅራቢ ሆነው መቅረብ አለባቸው’ የሚለውን ሐሳብ እንደማይቀበሉ ገልጸው፥ በዚህ ችግር እየተሰቃዩ የሚገኙት ለአየር ንብረት ለውጥ አነስተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ማህበረሰቦች መሆናቸውን ጠቁመው፥ ይህ ጩኸት የፍትሕ ጉዳይ እንጂ፣ የእርዳታ ጩኸት መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል።

በአማዞን ውስጥ እና አጎራባች የሚገኙትን የአገሬው ተወላጅ ማህበረሰቦችን እውቀት እና አመራር በማንሳት፥ እነዚህ ሰዎች መፍትሄዎቹን ስለሚያውቁ ይህንን ችግር ሌት ተቀን እየፈቱ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ ‘የአየር ንብረት ፋይናንስ ይሄንን የፍትህ እና የኃላፊነት ግንዛቤ መከተል አለበት’ ብለዋል።

ምርጫዎች እና ሞራላዊ አመራር
አቶ ቶርንስ ለወታደራዊ ወጪዎች የገንዘብ አቅርቦት እንደልብ መገኘት እና የአየር ንብረት ፋይናንስን ለማሰባሰብ ባለው አስቸጋሪነት መካከል ያለውን አለመጣጣም በማንሳት፥ ይህ የምርጫ ጉዳይ እንጂ በዓለም ላይ በቂ ገንዘብ እንዳለ ጠቁመው፥ ሃገራት ከፈለጉ ይሄንን ሊያደርጉት እንደሚችሉ አመላክተው፥ በአህጉራት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሰጡትን መግለጫ በመጥቀስ የስነ ምግባራዊ አመራርን አስፈላጊነት አጉልተዋል።

የኮፕ ጉባዔዎች አሁንም ድረስ ለምን አስፈላጊ ሆኑ?
አቶ ቶርንስ ምንም እንኳን አዝጋሚ መሻሻል እና ያልተሟሉ ግዴታዎች ስጋት ቢኖርም የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ዓለም አቀፍ ስምምነትን ሂደት የመጠበቅ አስፈላጊነት አበክረው በመግለጽ፥ “እድገት የምታመጣበት ብቸኛው መንገድ የመገናኘት ባህል በሆነው በውይይት ነው” ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ መልቲላተራሊዝም ወይም መድብላዊ አሰራር አስፈላጊ ሆኖ እንደሚቆይ ጠቅሰው፥ ሆኖም ግን አንዳቸውም ፍፁም እንዳልሆኑ እና የምንፈልገውን ያህል አስቸኳይ እድገት እያመጡ እንዳልሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን ችላ ከተባለ ነገሮችን ለመመለስ ዓመታት እንደሚወስድ አሳስበዋል።

አቶ ቶርንስ በመጨረሻም አንዳንድ የግል ፍላጎት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ለሂደቱ መፋረስ ሃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው አስጠንቅቀው፥ ነገር ግን እድገት ሊመጣ የሚችለው ሰዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ሆነው ተመሳሳይ ውይይት ሲያደርጉ እንደሆነ እና ይሄም ዋናው ፍላጎታቸው እንደሆነ በመግለጽ አጠቃለዋል።

18 Nov 2025, 13:47