እህት ሜሪ ሉቺያ ኪም ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ምስጋናቸውን አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የተሰጠኝ ሃላፊነት ትልቅ ቢሆንም ያለኝ አቅም ትንሽ እንደሆነ የሰማኛል” ያሉት እህት ሉቺያ ኪም፥ቢሆንም ግን ቤተ ክርስቲያንን እና ማኅበሩን እንዳገለግል የጠራኝን ጌታ እና የማኅበር እህቶቼን ለጸሎታቸው እና ለእምነታቸው አመሰግናለሁ” ብለዋል።
የ60 ዓመቷ ኮሪያዊት እህት ሜሪ ሉቺያ ኪም የማኅበራቸው 110ኛ ዓመት መታሰቢያ በተከበረበት ሐሙስ መስከረም 22/2018 ዓ. ም. 2ኛዋ የቅዱስ ጳውሎስ ልጆች የገዳማውያት ማኅበር አዲስ የበላይ አለቃ ሆነው ከተመረጡ በኋላ አዲሱን ሚናቸውን በማስመልከት ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ በተመረጡበት ማግሥት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋርም ተገናኝተዋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ ጋር መገናኘት
አዲስ የተመረጡት የቅዱስ ጳውሎስ ልጆች ገዳማውያት ማኅበር ጠቅላይ አለቃ ከቅዱስነታቸው ጋር የነበራቸውን ቆይታ በማስመልከት ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለሱት፥ “ወደ ሰማዩ አባታችን እንድንመለከት፣ በመንፈስ ቅዱስ እንድንነሳሳ እና ራሳችንን በታሪክ ውስጥ እንድናስገባ ጋብዘናል” ብለዋል። በማኅበራዊ መገናኛ አማካይነት ስብከተ ወንጌልን በማድረግ ላይ አጽንኦት የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የማኅበሩ መሥራች የብጹዕ አባ አልበሪዮን ራዕይ በማስታወስ፥ “የቅዱስ ጳውሎስ ልጆች ገዳማውያት በዓለም ዙሪያ ወንጌልን የማስፋፋት ተልዕኮአችሁን እንድትቀጥሉ” በማለት ቅዱስነታቸው መንፈሳዊ መመሪያዎችን መስጠታቸውን እህት ሜሪ ሉቺያ ኪም ገልጸዋል።
“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ምክሮች በጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤያችን ወቅት መሪ ብርሃን ሆኖናል” ያሉት እህት ሜሪ ሉቺያ ኪም፥ “መንፈስ ቅዱስ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኩል የነገረንን በልባችን አጥብቀን ለመያዝ እና ከፊት ለፊታችን ያለውን መንገድ በታማኝነት ለመጓዝ እንፈልጋለን” በማለት ለጉዞአቸው የጸሎት ድጋፍን ጠይቀዋል።
የዓለማዊነት እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈተናዎች
በተጨማሪም እህት ሜሪ በደቡብ ኮሪያ ስለምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሲናገሩ፥ “በደቡብ ኮሪያ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን እያደገች የምትገኝ ቢሆንም ነገር ግን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ዓለማዊነት እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” አዳዲስ ፈተናዎች ገጥሟታል” ሲሉ አስረድተው፥ እንደ ጎርጎጎሮሳውያን በ 2027 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በጉጉት በመጠባበቅ ላይ እንደምትገኝ እና ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል።
ለተሃድሶ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ
የቅዱስ ጳውሎስ ልጆች ገዳማውያት ጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤ ለእህት ሜሪ ኪም በጥልቅ የመታደስ ፍላጎትን፣ ወንድማማችነት እንዲታደስ እና በድጋሚ እንዲበራ የሚያደርግ ስጦታን እንዳቀረበላቸው ተገልጿል። ዛሬ ከ2000 በላይ የቅዱስ ጳውሎስ ልጆች ገዳማውያት በአምስት አህጉራት በሚገኙ 52 አገራት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፥ ከ200 በላይ የማኅበር ቤቶች የሚተዳደሩ ማተሚያ ቤቶችን፣ የመጻሕፍት መደብሮችን፣ የመልቲሚዲያ ማዕከላትን በመምራት፥ በማኅበራዊ መገናኛዎች አማካይነት ወንጌልን ለዓለም በመስበክ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።