ከጥቅምት 16 እስከ ታህሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በሮም ሙዚየም ለጎብኚዎች እንዲታይ የቀረበው ጥንታዊው እና በጣም ታዋቂው የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ምስል ቅጂ ከጥቅምት 16 እስከ ታህሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በሮም ሙዚየም ለጎብኚዎች እንዲታይ የቀረበው ጥንታዊው እና በጣም ታዋቂው የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ምስል ቅጂ 

የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ቅሪተ አካል ወደ ኢትዮጵያ መጣ

እ.አ.አ በ 1182 ዓ.ም. በጣሊያን ሃገር አሲሲ በምትባል ከተማ የተወለደው ቅዱስ ፍራንቺስኮስ ቅሪተ አካሉ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሲሆን፥ ቅሪተ አካሉም በዓመታዊው የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ክብረ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ለህዝብ ይፋ ተደርጓል።

  አዘጋጅ እና አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ይህ የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ቅሪተ አካል የተገኘው ቅዱሱ የሞተበትን ሰባት መቶኛ ዓመት ኢዮቤልዩ ለማከብር እ.አ.አ. በ1926 ዓ.ም. ከዋናው የቅዱሱ ቅሪተ አካል ተወስዶ ለአማንያን ሁሉ በተለይም አሲሲ በመገኘት የቅዱሱን ቅሪተ አካል ለማክበር ላልታደሉ እንዲደርስ እና እንዲጸልዩበት ታስቦ ለቅዱስ ፍራንቺስኮስ ትላልቅ አድባራት ከተበረከተው እንደሆነ ተገልጿል።

እ.አ.አ. በ 2017 ዓ.ም. የዚህ እና መሰል በርካታ ቅዱስ ቅሪተ አካላት በኔዘርላንድ ካፑቺን አውራጃ በመገኘቱ፥ ለበርካታ ዓመታት በሮም የካፑቺን ማኅበር ቤተ መዘከር አለቃ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ካፑቺን ወንድም አባ ዮሐንስ ተክለማሪያም ባቾ ቅዱስ ቅሪተ አካላቱን ወደ ዋናው ቤተ መዘከር እንዲዛወሩ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህ በኋላ ከነዚህ ቅዱሳት ቅሪተ አካላት አንዱ ለኢትዮጵያ ካፑቺን ማኅበር ‘ኪዳነምሕረት አውራጃ’ እንደ ስጦታ ለአውራጃው አለቃ ለአባ ወርቁ ዮሐንስ መስከረም 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ማበርከታቸው ተገልጿል።

ይህ ቅዱስ ቅሪተ አካል በቅርስነት ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ሕያው መታሰቢያ እንዲሆን ታስቦ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ የቅዱሱን የትህትና፣ የሰላም እና የእግዚአብሔር ፍጥረታትን ሁሉ የመውደድ መንፈስ እንድንከተል የሚጠራን ትልቅ ሰማያዊ በረከት እንደሆነ እና መላው ምዕመናን ቅሪተ አካሉን ደርሰው በመሳለም፣ በቅሪቱ አካሉ ፊት ተገኝተው በመጸለይና እና ቡራኬ በመቀበል በረከቱን እንዲካፈሉ ተጋብዘዋል።

የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ቁምስና ቆሞስ የሆኑት ክቡር አባ ፍስሃ ታፈሰ እንደገለፁት የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ቅሪተ አካል በቁምስናው በቋሚነት የሚቀመጥ እንደሆነ እና መላው ምዕመናን በዚህ በመገኘት በቅዱሱ አማላጅነት ጸሎታቸውን ወደ ፈጣሪ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ታሪክ
በልጅነቱ ዮሃንስ ተብሎ ይጠራ የነበረው ፍራንቺስኮስ አባቱ የትውልድ ሃገሩ የሆነችውን ፈረንሳይን እጅግ አድርጎ ይወድ ስለነበር ‘ፍራንቺስኮስ’ ብሎ እንዲጠራ መወሰናቸው እና ትርጓሜውም ‘ትንሹ ፈረንሳዊ’ ማለት እንደሆነ ይገለፃል።

ፍራንቺስኮስ ገና ወጣት እያለ እሱ የተወለደበት አሲሲ እና ፕሩጊያ የምትባል ሌላ ከተማ በጠላትነት ይዋጉ እንደነበርና በጦርነቱም የአሲሲ ከተማ በመሸነፏ ምክንያት ፍራንቺስኮስ ከሌሎች ሰዎች ጋር እስረኛ ሆነው ወደ ፕሩጊያ ተወስደው ወደ እስር ቤት ተጥለዋል። በእስር ቤት እያለ ጊዜያት ባለፉ ቁጥር እግዚያብሄር ከእሱ የሚፈልገው ነገር እንዳለ የተረዳው ፍራንቺስኮስ ራሱን ከጓደኞቹ እና ከዓለማዊ ህይወት ገለል በማድረግ፣ ከሌሎች ሃሳቦችም ይልቅ እግዚያብሄርን ማገልገል የሚለው ሃሳብ በልቡ ውስጥ እያደገ እና ስር እየሰደደ በመሄዱ መንፈሱን አንድ ምኞት ብቻ ሞልቶት የእግዚያብሄርን ፍላጎት ማወቅ እና እስከ መጨረሻው እሱን መከተል የሚል ጽኑ ፍላጎት አደረበት።

ፍራንቺስኮስ በኮረብቶች እና በወይን እርሻዎች መካከል መንሸራሸርን ይወድ እንደነበር እና በአንድ ብቸኛ ዋሻ ውስጥ ሆኖ መጸለይ፣ ማዘን፣ እና መሪ ብርሃን ከሰማይ እንዲገለጥለት መለመንን ያዘወትር እንደነበር ይገለፃል።

የእግዚያብሄር ፍቅር የፍራንቺስኮስን ልብ እንደ እሳት ያቃጥለው እንደነበር እና ጸሎቶቹ በሙሉ በእግዚያብሄር ፍቅር የተሞሉ ሲሆን፥ ሲጸልይም ጌታ ኢየሱስ ፍቅሬ ሆይ አንተን እናፍቃለሁ፣ አንተን አቅፌ እንድሞት አድርገኝ፣ ልቤ ለሁለት ተከፍሎ ይነዳል ይል እንደነበር ይገለፃል።

በልቡ ውስጥ አንድ ፍላጎት የነበረው ፍራንቺስኮስ፥ እሱም አምላክን አለመጠን ማፍቀር እና መውደድ ሲሆን፥ ዘወትር ጌታ ሆይ ልቤን በነበልባላዊ እና በጣፋጭ የፍቅር ሃይል ሙላው፣ በፍቅርህም እንድሞት ልቤን ከዓለማዊ ነገሮች ላይ ንቀልልኝ እያለ ይጸልይ ነበር።

ፍራንቺስኮስ ሁለት ንብረቶች ብቻ የነበሩት ሲሆን፤ እነሱም ለእግዚያብሄር ያስረከባቸው ነፍሱን እና ስጋው ናቸው።

ቅዱስ ፍራንቺስኮስ እ.አ.አ. በ 1212 ዓ.ም. የታናናሽ ወንድሞች ማህበርን የመሰረተ ሲሆን፥ የአባላቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ የመተዳደሪያ ህግ ማውጣት አስፈላጊ ስለነበረ የማህበሩን የመተዳደሪያ ደንብ አውጥቷል።

ቅዱስ ፍራንቺስኮስ መላዕኩ ቅዱስ ሚካኤልን ይወደው እና ያከብረው ስለነበር ለዓመታዊ በዓሉ ለመዘጋጀት እ.አ.አ. በ 1224 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ አልቬርኖ ወደሚባል ተራራ በመውጣት አርባ ቀን እና ሌሊት በፆም ጸሎት በማሳለፍ፥ በእነዚህም ቀናት ውስጥ ለአምላክ ብዙ መስራት እና መሰቃየትን በመሻት ያለመሰልቸት የእግዚያብሄርን ፈቃድ ለማወቅ ቅዱሳት መፃህፍትን አንብቧል። አብሮት የነበረው ወንድም ሊዮን የያዘውን መጽሃፍ ቅዱስ ሦስት ጊዜ ከፍቶ በማንበብ፥ ሦስቱንም ጊዜ ስለ ክርስቶስ ህማማት የሚናገሩ ጥቅሶችን አግኝቶ ማንበቡ የሚነገር ሲሆን፥ ቅዱስ ፍራንቺስኮስ ከዚህም ክስተት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራውን እንዲካፈል መፈለጉን በመረዳት ፍርሃትና ደስታ በተቀላቀለበት ስሜት የጌታውን ቃል የተቀበለ ሲሆን፣ ከዛን ጊዜ ጀምሮ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህማማት የዘወትር ሃሳቡ በመሆን ደሙን ለጌታ ለማፍሰስ በእውነተኛ ፍላጎት ይቃጠልም ጀመር።

የአሲሲው ፍራንቺስኮስ ከብዙ መልካም ሥራዎች እና የቅድስና ህይወት በኋላ ከዚህ ዓለም መከራ እና ስቃይ እ.አ.አ. ጥቅምት 3 ቀን 1226 ዓ.ም. ማረፉ ይታወቃል።

09 Oct 2025, 09:37