የጥቅምት 22/2018 'የሁሉም ቅዱሳን' አመታዊ መታሰቢያ በዓል ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተኖ
የእለቱ ንባባት
1. ራይ 7፡2-14. 9-14
2. መዝሙር 23
3. 1ዩሐ. 3፡13
4. ማቴዎስ 5፡1-12
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
አንቀጸ ብፁዓን
ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ አፉንም ከፍቶ እንዲህ ብሎ አስተማራቸው፤
በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መፅናናትን ያገኛሉና።
የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።
ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ይጠግባሉና።
ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና።
ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና።
ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።
ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
“ሲሰድቡአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።”
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
ዛሬ የምናከብረው የሁሉም ቅዱሳን አመታዊ በዓል እኛ ሁላችን ወደ ቅድስና ሕይወት እንደ ተጠራን ያስታውሰናል። ዛሬ ሁላችንም የምናከብራቸው ቅዱሳን በቀላሉ እንዲሁ ምልክት ሆነው ያለፉ፣ ከሰው ልጅ ታሪክ ርቀው የሚገኙ እና ተደራሽ ያልነበሩ ሰዎች አይደለም። በተቃራኒው፣ እንደ ማነኛችንም ሰዎች በእግራቸው መሬት ላይ የኖሩ ሰዎች ናቸው፣ ሁሌም ለመነሳት እና ጉዞው ለመቀጠል የሚያስችል ጥንካሬን በጌታ በማግኘት በእየለቱ ከሚያጋጥማቸውን ውድቀቶች እና ስኬቶች ጋር መኖር የተለማመዱ ሰዎች ነበሩ።ከዚህ በመቀጠል ቅድስና በአንድ ሰው ጥንካሬ ብቻ ሊከናወን የማይችል ግብ መሆኑን የተረዱ ሲሆን፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋ ፍሬ እና ለእርሱ ያለንን ነፃ ምላሽ የምንገልጽበት መሆኑንም ተረድተው ነበር። ስለዚህ ቅድስና ስጦታ እና ጥሪ ነው።
የእግዚአብሔር ጸጋ ማለትም ስጦታው፣ እኛ ልንገዛው ወይም ልንለውጠው የምንችለው ነገር አይደለም፣ ነገር ግን ከጥምቀታችን ቀን ጀምሮ በውስጣችን በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ እና በተመሳሳይ መልኩም በመለኮታዊ ሕይወት ውስጥ በመሳተፍ የሚገኝ ነገር ነው። ወደ ክርስቶስ የተሸጋገርን፣ አንድ የወይን ቅርንጫፍ ከግንዱ ጋር እንደ ተወሃደ ሁሉ እኛም የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን ከእርሱ እና ከእርሱ ጋር ብቻ መኖር መቻል ይኖርብናል። እናም ቅድስና አሁን በእዚህ ምጽሐተኛ በሆንበት ምድር ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ሙሉ ህብረት ፈጥሮ መኖርን ያመለክታል።
ቅድስና ስጦታ ከመሆኑ በተጨማሪ በጋራ የክርስቶስ ሐዋርያ እንድንሆን የቀረበልን መንፈሳዊ ጥሪ ተብሎ ይጠራል፣ ወደ መጨረሻ ግብ ማለትም ወደ ዘላለም ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ህብረት ከእግዚአብሔር ጋር እያንዳንዱ ክርስቲያን በእምነት እንዲከተል የተጠራው ምልአት ያለው መንገድ ነው። ስለዚህ ቅድስና እግዚአብሔር ላቀረበልን ጥሪ የምንሰጠው ምላሽ ነው። በዚህ አተያይ፣ በሕይወታችን ሁኔታዎች እና ግዴታዎች ሁሉ ውስጥ፣ በሁሉም ነገር ውስጥ በፍቅር እና በርኅራኄ ለመኖር በመሞከር በእዚህ መልኩ በመጓዝ ለመቀደስ ከባድ እና ዕለታዊ ቁርጠኝነትን መውሰድ አስፈላጊ ነው።
ዛሬ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ የምናከብራቸው ቅዱሳን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሕይወታቸው ውስጥ ይህ መለኮታዊ ብርሃን እንደሚያስፈልጋቸው አምነው ተቀብለው በሕይወታቸው ውስጥ ተግብረው አልፈዋል። በመሆኑም አሁን ፣ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት (ራዕ 7: 15 ን ተመልከት) ፣ ክብሩን ለዘላለም ይዘምራሉ። እኛ ትክክለኛ ግባችን ብለን በተስፋ የምንጠብቀውን “ቅድስቲቷን ከተማ” ይመሠርታሉ፣ እኛ አሁን ምድራዊ በሆነው ከተማችን ውስጥ በምናደርገው አሰችጋሪ ጉዞ ውስጥ በተሰፋ እንድንጓዝ ይረዱናል። ሕይወታቸውን በመመልከት እነሱን ለመምሰል እንበረታታለን። በእኛ መካከል የሚኖሩ በሮቻችን አጠገብ ይሚገኙ የእግዚኣብሔር ተስፋ መገለጫ እና ነጸብራቅ የሆኑ ብዙ ቅዱሳን ምስክሮች አሉ።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣
በተጨማሪም በዛሬው ሥርዓተ አምልኮ ከማቴ. 5: 1-12 ተወስዶ የተንበበው ምንባብ ስለ ብጹዓን ይናገራል። በዚህ ምዕራፍ በቁጥር ሦስት ላይ የተጻፈው መሠረታዊ መሆኑን እንመለከታለን። እንዲህም የሚል ነው፥ ‘በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብጹዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና’ (ማቴ. 5: 3)።
ለመሆኑ የመንፈስ ድሆች እነማን ናቸው? በመንፈስ ድሆች የሆኑት በራሳቸው መመካት የማይችሉ፣ ራሳቸውን ችለው የማይኖሩ እና ‘በእግዚአብሔር ፊት ለማኞች’ ሆነው የሚኖሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚያስፈልጋቸው የሚሰማቸው፣ እንዲሁም መልካም የሆነው ሁሉ ከእርሱ ዘንድ በጸጋ ስጦታ እንደሚሰጣቸው የሚገነዘቡት ናቸው። በመንፈስ ድሆች የሆኑት ከእግዚአብሔር የሚቀበሉትን ስጦታ ያከብሩታል፣ ዋጋንም ይሰጡታል። ስለዚህ ምንም ዓይነት ስጦታ እንዲባክንባቸው አይፈልጉም። በዛሬው አስተምሮዬ በዚህ የመንፈስ ድህነት ዓይነተኛ ገጽታዎች ላይ በማትኮር፣ ስጦታን አለማባከን የሚለውን መመልከት እወዳለሁ። በመንፈስ ድሆች የሆኑት ምንም ዓይነት ስጦታ እንዲባክንባቸው አይፈልጉም። ኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ ያለማባከን አስፈላጊነትን አሳይቶናል። ለምሳሌ ተርበው ለነበሩ በርካታ ሰዎች አምስት የገብስ እንጀራ እና ሁለት ዓሣ ባርኮ በበቂ መጠን እንዲመገቡ ካደረጋቸው በኋላ ምንም ነገር እንዳይባክን፣ የተረፈው ምግብ እንዲሰበሰብ ጠይቋል። ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ‘አንድም እንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቁርስራሽ አከማቹ’ አላቸው (ዮሐ. 6:12) አለማባከን የራሳችንን፣ የሰዎችን እና የነገሮችን ዋጋ እንድናደንቅ ያስችለናል። ይሁን እንጂ ይህ ብዙውን ጊዜ ችላ የተባለበት መርህ ነው። በተለይ በበለጸጉ ማኅበረሰቦች ዘንድ የማባከን እና የመጣል ባሕል ይታያል። ሁለቱም ጎጂዎች ናቸው። ስለዚህ በከንቱ የማባከን እና የመጣል አስተሳሰብ የሚቃረኑ ሦስት ተግዳሮቶችን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።
የመጀመሪያው ተግዳሮት፥ ስጦታዎች የሆንን እኛ እራሳችን መባከን የለብን። እያንዳንዳችን አንዳችን ለአንዳችን መልካም ስጦታዎች ነን። እያንዳንዱ ሰው፣ ወንድ ወይም ሴት በችሎታው ብቻ ሳይሆን በሰዓዊ ክብሩ ሀብታም ነው። እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር የተወደድን እና ዋጋ ያለን ውድ ስጦታዎች ነን። ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ባለን ሃብት ሳይሆን በማንነታችን የተባረክን እንደሆንን ይናገራል። ስለዚህ አንድ ሰው ይህን ካለመረዳት የተነሳ ራሱን በሚጥልበት ጊዜ እራሱን ያባክናል ማለት ነው። እራሳችንን ‘የማንጠቅም ወይም ለምንም ብቁዎች ያልሆንን’ ከማለት፣ የተሳሳትን እና በሐዘን እንድንወድቅ የሚያደርጉ ፈተናዎችን በእግዚአብሔር ዕርዳታ ለማሸነፍ ጥረት እናድርግ።
ሁለተኛው ተግዳሮት፥ ያሉንን ስጦታዎች አለማባከን የሚል ነው። ብዙ ሰዎች በረሃብ እየሞቱ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ በዓለማችን ውስጥ በየዓመቱ ከጠቅላላው የምግብ ምርት ውስጥ አንድ ሦስተኛው እንደሚባክን ይነገራል። በዚህ መንገድ የተፈጥሮ ሀብቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ አይችሉም። ማንም ሰው ለዕለታዊ ሕይወቱ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንዳይጎድልበት፣ የመገልገያ ዕቃዎች እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። ያለንን ከማባከን ይልቅ የፍትህ፣ የቸርነት እና የሥነ-ምህዳር ባሕልን ማስፋፋት ይኖርብናል።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ተግዳሮት፣ ሰዎችን ማግለል እና በብቸኝነት እንዲሰቃዩ ማድረግ የሚል ነው። የመጣል ባሕል እንዲህ ይላል፥ ‘የምታስፈልገኝን ያህል እጠቀምብሃለሁ! ከዚያ በኋላ ግን ሰለማታስፈልገኝ ወደ ውጭ አውጥቼ እወረውርሃለሁ!’ በተለይም በጣም የደከሙት፣ ገና ያልተወለዱ ሕጻናት፣ አዛውንት፣ የተቸገሩት እና ለድህነት ሕይወት የተዳረጉት ይህ ዕድል ያጋጥማቸዋል። ነገር ግን ሰዎች እንደ ዕቃ ሊጣሉ እና ለድህነት ሕይወት ሊዳረጉ አይገባም። ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው የተቀደሰ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በዕድሜ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የሰው ልጅ መናቅ እና ከማኅበራዊ ሕይወት መወገድ የለበትም። በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ልዩ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ስለዚህ ሕይወት ሁል ጊዜ ክብር እና እንክብካቤ ሊሰጠው ይገባል እንጂ ሊጣል ወይም ሊረሳ አይገባም።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! አንዳንድ ጥያቄዎችን እራሳችንን እንጠይቅ፥ ከምንም በላይ የመንፈስ ድህነትን እንዴት እኖረዋለሁ? ለእግዚአብሔር ቦታ መስጠት እንዳለብኝ አውቃለሁ? እሱ መልካም፣ እርሱ እውነተኛ እና ታላቅ ሀብቴ መሆኑን አምናለሁ? እግዚአብሔር እንደሚወደኝ አምናለሁ? ወይንስ የእርሱ ስጦታ መሆኔን እየረሳሁ እራሴን በሐዘን እጥላለሁ? ላለማባከን እጠነቀቃለሁ? ንብረቶችን ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ በተጠያቂነት እጠቀማቸዋለሁ? ያሉኝን ነገሮች ከሌሎች ጋር ለመካፍል ፈቃደኛ ነኝ ወይስ ራስ ወዳድ ነኝ? በመጨረሻም፣ አቅመ ደካሞች ውድ የእግዚአብሔር ስጦታዎች መሆናቸውን በመገንዘብ፣ እርሱ በጠየቀኝ መሠረት እንከባከባቸዋለሁ? የተለያዩ ዕድሎችን የተነፈጉ ድሆችን አስታውሳለሁ?
ሕይወት ውድ የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነች እና እኛም እራሳችንን የእግዚአብሔር ስጦታዎች አድርገን እንድናቀርብ እና ይህ ሁሉን ቅዱሳን የምናስብበት ቀን ዐይናችንን ወደ ሰማይ ከፍ እንድናደርግ ይመራናል፣ የምድርን እውነታዎች ለመርሳት ሳይሆን ይልቁንም በምድር ላይ የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች በድፍረት እና በተስፋ መጋፈጥ እንድንችል ይረዳናል። የመጽናና እና እርግጠኛ ተስፋ ምልክት የሆነችው ቅድስት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናትነት አማላጅነቷ ከልጇ ዘንድ እንድታማልደን ልንጸልይ ይገባል።
ምንጭ፤ የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ፣ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት)-ቫቲካን