ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ መስዋዕታ ቅዳሴ ሲያሳርጉ - ምስል ከማህደር ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ መስዋዕታ ቅዳሴ ሲያሳርጉ - ምስል ከማህደር  

ጥቅምት 13/2018 ዓ. ም. ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የተዘገቡ ዜናዎች

በዚህ ሳምንት ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ለቫቲካን ዜና ከደረሱ ዜናዎች መካከል፥ ብፁዕ ካርዲናል ላቪጄሪ መታወሳቸው፣ የሶሪያ ሊቀ ጳጳስ ዣክ ሙራድ ሽልማት እንደተበረከተላቸው እና የጥንቷ የአርመን ቤተ ክርስቲያን መታደሱ የሚገልጹ ዜናዎች ይገኙባቸዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ለብፁዕ ካርዲናል ላቪጄሪ ክብር የተደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ
ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም. የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የቅዱስ ሄኔ ቤተክርስቲያን ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ላቪጄሪ የተወለዱበትን ሁለት መቶኛ ዓመት ለማስታወስ የተደረገውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩ ሲሆን፥ የ ‘ዋይት ፋዘርስ’ ማህበር መስራች እና የ ‘ሉቭር ዲ ኦሪየንት’ የመጀመሪያ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ብፁዕ ካርዲናል ላቪጌሪ በምስራቁ እና በምዕራቡ አቢያተ ክርስቲያናት መካከል ህብረት እንዲኖር ትልቅ ሚና የተጫወቱ አባት ናቸው።

ብፁዕ ካርዲናል ላቪጌሪ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተለይም እ.አ.አ. በ 1860 ዓ.ም. በሊባኖስ እና በሶርያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ጭፍጨፋ ከደረሰ በኋላ በመላው የኦቶማን ኢምፓየር በመዞር ሰብአዊ እርዳታን በቁርጠኝነት በማቅረብ የሚታወሱ ሲሆን፥ የምስራቅ ህዝቦችን ለማገልገል ያሳዩት ቁርጠኝነት የበጎ አድራጎት እና የእምነት ተምሳሌት ሆኖ እንደሚኖርም ተገልጿል።

ሊቀ ጳጳስ ዣክ ሙራድ መታወሳቸው
በሆምስ የሶርያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ዣክ ሙራድ ለሶርያ ሰላምና ዕርቅ እንዲሰፍን ላሳዩት ቁርጠኝነት ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በቫቲካን የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ፋውንዴሽን ሽልማት የተቀበሉ ሲሆን፥ የደማስቆ ሐዋርያዊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ዘናሪ በተገኙበት በዚህ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ሊቀ ጳጳስ ሙራድ ‘በሃይማኖት ተቋማት እና በተለያዩ ባሕሎች መካከል የሚደረግ ውይይት አማራጭ ሳይሆን ለዘመናችን እጅግ አስፈላጊ ነገር መሆኑን’ በአጽንዖት ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ እ.አ.አ. በ 2015 በጽንፈኛ የአይኤስ ቡድን ታግተው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት በጦርነት በፈራረሰችው ሶሪያ ፈውስን እና አንድነትን ለማስፋፋት በትጋት እያገለገሉ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በሄርሄር የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መቀደስ
ከዚህም በተጨማሪ በሶሪያ፣ በቫዮት ድዞር ክልል የሚገኘው የሄርሄር መንደር በቅርቡ ታድሶ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን የመባረክ እና የመቀደስ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።

የመንደሩ መንፈሳዊ መነቃቃት ምልክት የሆነው ይህ የአምልኮ ቦታ ሃገሪቷ በሶቪየት ህብረት ግዛት ሥር በነበረችበት ወቅት ወደ እህል ማጠራቀሚያነት ተቀይሮ እንደነበር ታሪክ የሚያስታውስ ሲሆን፥ እድሳቱ የተከናወነው በቫዮት ድዞር ሀገረ ስብከት፣ መንግሥታዊ ባልሆነው የማህበረሰብ ልማት እና የፈረንሳይ የእርዳታ ማህበር በሆነው ‘ሎቭር ዲኦሪየንት’ ድጋፍ እንደሆነ ተገልጿል። ሥነ ስርዓቱ በባህላዊው የ ‘ፖፖክ’ ፌስቲቫል መድመቁን የቀጠለ ሲሆን፥ ለዕለቱም ሞቅ ያለ እና ማራኪ ስሜትን መፍጠሩ ተገልጿል።

24 Oct 2025, 14:47