በዚህ የፍራንቺስካዊያን ወር የአሜሪካ ኮሌጆች የአገልግሎት እና የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የብሩክሊኑ ፍራንቺስካዊ ወንድም ግሪጎሪ ሴሊኒ በብሩክሊን በሚገኘው የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ኮሌጅ ውስጥ ያለውን ተልዕኮው ሲያብራራ ቃላቶቹ ምስጋና እና ዓላማውን የሚያንጸባርቁ ሲሆን፥ በቅዱስ ፍራንቺስኮስ ውስጥ በማገልገሉ በጣም እንደተባረከበት በመጥቀስ፥ በተልዕኮ፣ በአገልግሎት እና በሃይማኖት ተቋማት ውይይት ጽህፈት ቤት ውስጥ ያከናወነውን ሥራ ሲገልጽ፥ ይህ ቡድን በሁሉም የከፍተኛ ተቋማት ህይወት ውስጥ የፍራንቺስካዊያንን መንፈስ ለማስተጋባት በትጋት ሲሰራ የነበረ ቡድን መሆኑን አመልክቷል።
በቅዱስ ፍራንቺስኮስ እና በቅድስት ክላራ እሴቶች ላይ የተመሰረተው ይሄ መንፈስ አሁን ከኮሌጁ ግድግዳዎች ባሻገር እንደሚዘልቅ የገለጸው ወንድም ግሪጎሪ፥ እንደ አንድ አነስተኛ የዩኒቨርሲቲ ተነሳሽነት የተጀመረው ይህ ንቅናቄ እያደገ መጥቶ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ለመሆን የበቃው የፍራንቺስካዊያን ወር የቅዱስ ፍራንቺስኮስን የአኗኗር ዘይቤ ለመኖር እና ለመካፈል የሚያነቃቃ ወር መሆኑን ገልጿል።
የፍራንቺስካዊያን ወር አጀማመር
ወንድም ግሪጎሪ ስለ ፍራንቺስካዊያን ወር አጀማመር ለቫቲካን ዜና እንደገለጸው፥ ሐሳቡ “በመንፈስ ቅዱስ” መነሳሳቱን ጠቅሶ፥ ‘ለሰኞ ስለደረስን እግዚአብሔር ይመስገን’ የሚለው ለረጅም ጊዜያት የዘለቀውን የራዲዮ ፕሮግራሙን በሚያስተናግድበት ወቅት እንደ ‘የጥቁር ታሪክ ወር’ ወይም ‘የሴቶች ታሪክ ወርን’ የመሳሰሉ የትኩረት ጊዜን ለአስፈላጊ ጭብጦች የመመደብን ኃይል በራሱ ማየቱን ገልፆ፥ “መንፈስ ቅዱስ ‘የፍራንቸስኮ ወር’ የሚለውን ሀሳብ በውስጡ እንዳሳደረ በማስታወስ “አስደናቂ የ800 ዓመት ታሪክ እና ባህል ቢኖረንም ለእኛ የተሰጠ ወር አልነበረም” ብሏል።
እ.አ.አ. በ 2023 ዓ.ም. ይህ ተነሳሽነት በቅዱስ ፍራንቺስኮስ ኮሌጅ ውስጥ ቅርፅ መያዙን የጠቀሰው ወንድም ግሪጎሪ፥ በአንድ ወቅት የቅዱስ ክላራ እና የቅዱስ ፍራንሲስ ሳምንት የነበረው ወደ ሙሉ ወር የአስተንትኖ፣ የማህበረሰብ እና የፈጠራ ስራ የሚከናወንበት በመሆን እየተስፋፋ መምጣቱን ገልጿል።
የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ለቅዱስ ፍራንቺስኮስ የሚውለው ቀንስ ዬትኛው ነው? የሚለው ሀሳብ ወደ እኔ የመጣ ሲሆን፥ ይህ ሃሳብ የእነዚህ ዝግጅቶች መነሻ ነበር ያለው ወንድም ግሪጎሪ፥ ከዝግጅቶቹ በተጨማሪ፣ ‘ሁሉም መልካም ነገሮች’ የሚባል ድህረ ገጽ በጥቅምት ወር ውስጥ ዕለታዊ አስተያየቶችን ለማካፈል እንደተፈጠረ ገልጿል።
በዚያው ዓመት በኒውዮርክ ከተማ አካባቢ ከሶስት አህጉረ ስብከት እንዲሁም ከኒው ጀርሲ ከሶስት አህጉረ ስብከት ጋር ትብብር መፈጠሩን በመግለጽ፥ በዚህ አካሄድ ወደፊት የመስፋፋት ተስፋ አለው ብሎ ማመኑን የተናገረ ሲሆን፥ በወቅቱ በጎረጎሳዊያኑ 2025 ዓ.ም. ላይ ሀገራዊ ክብረ በዓል የማዘጋጀት ዓላማ እንደነበረው ገልፆ፥ በ 2026 ደግሞ ቅዱስ ፍራንቺስኮስ ወደ ገነት የሄደበትን 800ኛ ዓመት በማክበር ዓለም አቀፋዊ እንሆናለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብሏል።
የቅዱስ ፍራንቼስኮ የሰላም ጸሎት
ወንድም ግሪጎሪ ከቅዱስ ፍራንቺስኮስ ጋር ያለው ጥልቅ ግንኙነት ከልጅነት ጀምሮ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፥ የቅዱሱን ሐውልት፣ የወፍ መታጠቢያ ገንዳ ተብሎ የሚታወቀውን ስፍራ፣ በክሊቶን ኒው ጀርሲ የሚገኘውን የቤተሰቡን የአትክልት ስፍራ ያስጌጥ እንደነበረ በማስታወስ “ልጅ ሆኜ ቅዱስ ፍራንቺስኮስ ሁልጊዜ የአእዋፍ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ አስብ ነበር ብሏል።
መጀመሪያ ላይ በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ውስጥ ይሠራ የነበረው ወንድም ግሪጎሪ፥ የፍራንቺስኮስን ታሪክ ሙሉ በሙሉ ሳይረዳ በየጊዜው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄድ እንደነበር ገልጿል።
“ቅዱስ ፍራንቼስኮ እዚያ የሚሆነው የአትክልት ቦታዎችን ለመጠበቅ ብቻ ነው ብዬ አስብ ነበር” ያለው ወንድም ግሪጎሪ፥ የፍራንቺስካዊያን ወንድም ከሆነ በኋላ ግን የቅዱሱን ጥልቅ መንፈሳዊነት እና ተልእኮ የተረዳ ሲሆን፥ ለእርሱ በተሰጠው የሰላም ጸሎት ውስጥ በተካተቱት “የተስፋ፣ የእምነት፣ የመስጠት፣ የመካፈል፣ የመውደድ እና የይቅርታ ቃላት እሱን መረዳት ችያለው ብሏል።
ቅዱስ ፍራንቺስኮስ በ 1206 ዓ.ም. የተቀበለውን ጥሪ ያነሳው ወንድም ግሪጎሪ፥ “ፍራንቺስኮስ ጥገና ያስፈልጋት የነበረውን ቤተክርስቲያኔን እንደገና ገንብቷል” ካለ በኋላ፥ ዛሬ ላይ እድሳት የሚያስፈልጋት ዓለማችን በተመሳሳይ ሁኔታ ለሃይማኖት መስዋዕት መሆን እያንዳንዱን ሰው፣ በተለይም ወጣቱን ትውልድ እየተፈታተነ ያለ ነገር እንደሆነ እንደሚሰማው ገልጿል።
እምነትን በተግባር
ወንድም ግሪጎሪ ወደ ሃገር አቀፍ ክብረ በዓልነት የተሻገረው በዚህ አስደናቂ የጥቅምት ወር ተነሳሽነት ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ወደ 20 የሚጠጉ የፍራንሲስካውያን መሪዎች ተነሳሽነቱን መቀላቀላቸውን የገለጸ ሲሆን፥በዘንድሮው ዝግጅት እያንዳንዱ ትምህርት ቤት በቅዱስ ቁርባን ጸሎት ላይ እንዲሳተፉ እንደሚፈልግ እና በመላ ሀገሪቱ በአንድነት ስለ ሰላም እንዲጸልዩ እንፈልጋለን ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የቅድስት ክላራ ገዳማትን እና ሃይማኖታዊ ጉባኤዎችን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የፍራንቺስካዊያን ማህበረሰቦች እየተሳተፉ እንደሆነ ገልጿል።
ወደፊት መመልከት
የፍራንቺስካዊያን ወር የወደፊት እጣ ፈንታ መንፈሱ ትሑት እንደሆነ ሁሉ በጣም ትልቅ እንደሆነ ያመላከተው ወንድም ግሪጎሪ፥ እ.አ.አ. ለ 2026 ዓ.ም. የታቀዱት ዕቅዶች በ 2027 በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋት በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ቀጣይነት ያለው አገልግሎት መስጠትን እንደሚያጠቃልል ገልጿል።
የፍራንቺስካዊያን ወር ዋና ዓላማው የቅዱሱን ሙሉ ታሪክ የማያውቁ ሰዎችን ለመድረስ ሲሆን፥ “ቅዱስ ፍራንቺስኮስ በእውነት ለካቶሊኮች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ለአይሁዶች፣ እስላሞች፣ ቡዲስቶች፣ ሂንዱዎች፣ ሌላው ቀርቶ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ እምነት የሌላቸው ሰዎች ሳይቀር ለሁሉም ሰው እንደቆመ ያስረዳው ወንድም ግሪጎሪ፥ ብዙ ሰዎች የፍራንቺስካዊያንን የአኗኗር ዘይቤ ቢቀበሉ ዓለም በጣም የተሻለ ቦታ ላይ እንደምትሆን አምናለሁ ብሏል።
የጥቅምት ወር የፍራንቺስኮስ ወር መሆኑን ሁሉም ሰው፣ በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች እንዲያውቁ እንፈልጋለን ያለው ግሪጎሪ፥ በመጨረሻም ሁሉም ሰው በጥቅምት ወር ብቻ ሳይሆን በዓመት ውስጥ በሚገኙ በሁሉም ቀናት በፍራንቺስካዊያን የአኗኗር ዘይቤ እንዲመሩ እና እንዲነቃቁ እንፈልጋለን በማለት አጠቃሏል።