የዓለም የተልእኮ እሁድን አስመልክቶ ከተደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ በኋላ ተሳታፊዎች በጋራ የተነሱት ፎቶ የዓለም የተልእኮ እሁድን አስመልክቶ ከተደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ በኋላ ተሳታፊዎች በጋራ የተነሱት ፎቶ  (©Cardinal Bo / ©RVA Sgaw Karen)

የማይናማር ህፃናት የዓለም የተልዕኮ እሁድን ማክበራቸው ተገለጸ

በማይናማር ያለው የህዝቡ ስቃይ ቀጥሎ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከ1,500 የሚበልጡ የያንጎን ሃገረ ስብከት ህፃናት ልጆች የዓለም ተልዕኮ እሁድን ማክበራቸው የተነገረ ሲሆን፥ የማይናማር ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ በመርሃ ግብሩ ላይ ለህፃናቱ ባስተላለፉት መልዕክት በቅርቡ ቅድስናው እንደታወጀለት ወጣት እንደ ቅዱስ ካርሎ አኩቲስ ጌታን እንዲወዱ እና ምንም ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም በእምነት እና በደስታ የተሞላ ሚስዮናውያን እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሁድ ዕለት በተከበረው የዓለም የተልዕኮ ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር በሆነችው ማይናማር ላይ በሲቪሎች እና በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ በተፈፀመው የታጣቂዎች ጥቃት እና የአየር ድብደባ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸው፥ በማይናማር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ተማጽነዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በዓመፅና በችግር ለሚሰቃዩት ሁሉ ያላቸውን ቅርበት በመግለጽ “አፋጣኝ እና ውጤታማ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ልባዊ ጥሪዬን አቀርባለው” ያሉ ሲሆን፥ በማከልም የጦርነት መሳሪያዎች ሁሉን አቀፍ እና ገንቢ በሆነ ውይይት ለሰላማዊ አካላት ተላልፈው እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ምንም እንኳን በሃገሪቱ ውስጥ ስቃዮች እና ጉዳቶች ቢኖሩም የማይናማር ምዕመናን የዓለም ተልዕኮ እሁድን በሙሉ እምነት ያከበሩ ሲሆን፥ በተለይም 1,500 የሚሆኑ የያንጎን ሃገረ ስብከት ህፃናት ከዓለም የተልዕኮ ቀን አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጥቅምት 8 በየሞን መንደር በሚገኘው በቅዱስ ማርቆስ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ውስጥ በደማቅ ሁኔታ ዋዜማውን ማክበራቸው ተገልጿል።

የዓለም ተልዕኮ እሑድ ጥቅምት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. “በሕዝቦች መካከል የተስፋ ሚስዮናውያን” በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን፥ የያንጎን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዚህ ሰፊ ዝግጅት ከ32 ቁምስናዎች የተውጣጡ ወጣት ምዕመናን አንድ ላይ እንደተሰባሰቡ ገልጸው፥ ሕጻናት እና ወጣቶች ለተስፋ ሚስዮናዊነት ያላቸውን ተጨባጭ ሚና አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሰላምታ እና በረከት
ብፁዕ ካርዲናል ቦ የያንጎን ረዳት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኖኤል ሳው ናው፣ በማይናማር የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተወካይ የሆኑት ሞንሲኞር አንድሬ ፌራንቴ እና ከአስራ አምስት ካህናት ጋር በመሆን የተደረገውን መስዋዕተ ቅዳሴውን የመሩ ሲሆን፥ ሞንሲኞር ፌራንቴ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ለተሳተፉት ምዕመናን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሰላምታ እና ቡራኬን አቅርበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለዓመታዊው ክብረ በዓል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት በዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ የካቶሊክ ምዕመን በዓለም የተልዕኮ እሁድ ላይ እንዲሳተፍ ያሳሰቡ ሲሆን፥ ብፁዕ ካርዲናል ቦ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ለህፃናቱ ሞቅ ያለ ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ፥ ህፃናቱ እንደ ወጣት የቤተክርስቲያኑ ሚስዮናውያን ያላቸውን ወሳኝ ሚና አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፥ በዓሉ ግሪካዊው ሐኪም የነበረው እና ወደ ክርስትና የተለወጠ ታማኝ የክርስቶስ ወንጌላዊ ከሆነው ሃዋሪያው ቅዱስ ሉቃስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ጋር መጋጠሙን አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የማይናማር ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቦ እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ ካህናት፣ ገዳማዊያት፣ ካቴኪስቶች እንዲሁም ምዕመናን ሚስዮናዊ ለመሆን እንደተጠሩ አሳስበዋቸዋል።

ደስታ ወደ እግዚአብሔር መመልከት ነው
ከዚህም በላይ የማይናማሩ ብፁዕ ካርዲናል ቦ ከመሠዊያው አጠገብ የነበረውን በቅርብ ጊዜ ቅድስናው የታወጀለት የቅዱስ ካርሎ አኩቲስ ታዋቂ ምስል ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን፥ ካርዲናሉ በ 15 ዓመቱ በደረሰበት ህመም ምክንያት ህይወቱ ያለፈው ቅዱስ ምንም እንኳን ከባድ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ለኢየሱስ እና ለቅዱስ ቁርባን ያለውን ፍቅር እንዴት አድርጎ እንደገለጠ በአድናቆት ገልጸዋል።

“ደስታ ማለት ወደ እግዚአብሔር መመልከት ነው፣ ሀዘን ደግሞ ወደ ራስህ መመልከት ነው” በማለት የቅዱሱን ሃሳብ ደግመው የተናገሩት ካርዲናሉ፥ እውነተኛ ምሉእነት እና ሰላም ሙሉ በሙሉ ከጌታ እንደሚመጣ በአጽንዖት ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ቦ በመጨረሻም ወጣቶቹ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር በተግባር በማሳየት በተለይም ድሆችን እና የተገለሉትን በመውደድ የሚስዮናዊነትን መንፈስ እንዲያሳዩ ጥሪ በማቅረብ አጠቃለዋል።

22 Oct 2025, 13:50