በኮንራድ ኤን ሒልተን ፋውንዴሽን የካቶሊክ እህቶች ተነሳሽነት መሪ የሆኑት ሲስተር ጄን ዋካሂዩ በዛምቢያ በፋውንዴሽኑ የሚደገፍ ፕሮጀክትን ሲጎበኙ በኮንራድ ኤን ሒልተን ፋውንዴሽን የካቶሊክ እህቶች ተነሳሽነት መሪ የሆኑት ሲስተር ጄን ዋካሂዩ በዛምቢያ በፋውንዴሽኑ የሚደገፍ ፕሮጀክትን ሲጎበኙ  

የካቶሊክ እህቶች በዓለም ላይ የክርስቶስ ‘ሥራዎች እና መገኘት’ ተምሳሌት ናቸው ተባለ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተቀደሰ ህይወት ኢዮቤልዩ እያከበረች በምትገኝበት ወቅት ሲስተር ጄን ዋካሂዩ እንደገለጹት ገዳማዊያን እህቶች በሁሉም የዓለም ማዕዘናት ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለመርዳት የሚያደርጉትን ተልዕኮ የኮንራድ ሂልተን ፋውንዴሽን ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከ16,000 በላይ ገዳማዊያት እና ገዳማዊያን፣ መነኮሳት እና ከ100 ሀገራት የተውጣጡ የዓለማዊ ተቋማት አባላት ለተቀደሰ ሕይወት ኢዮቤልዩ ዘላለማዊ ከተማ ተብላ በምትታወቀው ሮም እንደተሰበሰቡ ተገልጿል።

ከመስከረም 28 እስከ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚከበረው የተቀደሰ ህይወት ኢዩቤሊዩ ላይ የሚሳተፉት መንፈሳዊ ነጋዲያኑ በጳጳሳዊው ባሲሊካ ቅዱስ በሮች በኩል የሚያልፉ ሲሆን፥ ሐሙስ ዕለት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚከናወነው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።

ከመንፈሳዊ ነጋዲያኑ መካከል የኮንራድ ኤን ሒልተን ፋውንዴሽን ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በተቋሙ የካቶሊክ እህቶች የፕሮግራም ስራዎች ኃላፊ የሆኑት ሲስተር ጄን ዋካሂዩ ሲሆኑ፥ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የተስፋ ኢዮቤልዩ “ተሃድሶን የሚያበረታታ፣ ከእምነት ጋር ጥልቅ ትስስር እንዲኖረን እና ለዓለም የተስፋ ብርሃን እንድንሆን የሚያበረታታ ቅዱስ በዓል ነው” ብለዋል።

“በዚህ በተቀደሰ የህይወት ኢዮቤልዩ ወቅት እንደ ሃይማኖተኛ ተገናኝተን መወያየታችን መልካም ነው” ያሉት ሲስተሯ፥ በምናገለግልበት የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ የፍቅር እና የተስፋ ምስክሮች ሆነን እናገለግላለን ብለዋል።

አሜሪካዊው የሆቴል ንግድ ስራ ፈጣሪ የሆነው ኮንራድ ሂልተን ለገዳማዊያት እህቶች ጥልቅ አክብሮት እና ፍቅር እንደነበረው የተነገረ ሲሆን፥ በኑዛዜው መሰረት የፋውንዴሽኑን የዳይሬክተሮች ቦርድ ለበጎ አድራጎት ተብሎ ከሚመደበው ገንዘብ አብዛኛውን ክፍል የካቶሊክ እህቶችን ሥራ ለመደገፍ እንዲውል መጠየቁ ይገለፃል።

የካቶሊክ እህቶች ተነሳሽነትን የሚቆጣጠሩት ሲስተር ዋካሂዩ ለቫቲካን ዜና እንደገለጹት የሂልተን ፋውንዴሽን የሀይማኖት እህቶች በትምህርት፣ በአረጋዊያን እና በጤና እንክብካቤ፣ በዘላቂ አደረጃጀት እና ቀጣይነት ባለው ምስረታ እራሳቸውን እንዲደግፉ ግብአቶችን በማቅረብ እንደሚረዳ የገለጹ ሲሆን፥ ገዳማዊያቱ በችግር ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን፣ ወጣቶችን እና ቤተሰቦችን ለመርዳት በሁሉም የዓለም ሀገራት እንደሚገኙ አብራርተዋል።

“እየተሰሩ ባሉ የድጋፍ ሥራዎች ላይ ባለሙያ ከሆኑ እህቶች ጋር አብረን እንሰራለን” ያሉት ሲስተር ዋካሂዩ፥ በተለይም በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ለመደገፍ ለሚሰሩት ሥራ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ እና ይህም ሲሆን የሰው ልጅ ክብር ከፍ እንዲል ይረዳል ብለዋል።

ሲስተር ዋካሂዩ ተቋማቸው በተለያዩ ሃገራት ማለትም በኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ማላዊ፣ ህንድ፣ ሜክሲኮ እና ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ በሲስተሮች የሚመራውን “ወጣቶችን የማጎልበት ተነሳሽነት” እንደሚደግፍ ገልጸው፥ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ የካቶሊክ እህቶች ተነሳሽነት ከ60,000 በላይ እህቶችን መርዳቱን የጠቆሙ ሲሆን፥ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በክህሎት ማዳበር፣ በሥራ ፈጠራ እና በግብርናው ዘርፍ በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ ማስቻላቸውን ገልጸዋል።

ትውልደ ኬንያዊቷ ሲስተር ዋካሂዩ በማከልም ሂልተን ፋውንዴሽን በዩናይትድ ስቴትስ ድንበር ላይ በምትገኘው የሜክሲኮ ከተማ በሆነችው ቲጁአና ውስጥ ለሚኖሩ የሄይቲ ስደተኞችን ለመርዳት የቋንቋ እና የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ለሚገኙ አሥር ሀይማኖታዊ ጉባኤዎችን እየረዳ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የተቋማቸው ሥራ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚኖሩ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ተስፋ መስጠት እና መንገድ ማሳየት እንደሆነ የገለጹት ሲስተሯ፥ ይህም ሲሆን የበለጠ ዘላቂ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ሊኖራቸው እንደሚችል ጠቁመው፥ “ከሚሰቃዩት ጋር በመተባበር በሥራችን ውስጥ ቁልፍ የሆነውን የቤተክርስቲያኗን ድሆችን ተቀዳሚ ያደረገ ሥራ እንተገብራለን” ብለዋል።

ሲስተር ዋካሂዩ የቅድስት መንበር የመገናኛ ጽህፈት ቤት ከሂልተን ፋውንዴሽን የካቶሊክ እህቶች ተነሳሽነት ጋር በመተባበር “የጴንጤቆስጤ ፕሮጀክት” ተብሎ በሚታወቀው ፕሮግራም በኩል እህቶችን በጋዜጠኝነት በማሰልጠን የጉባኤያቸውን የሚስዮናዊነት ሥራ ታሪክ እንዲናገሩ ማስቻሉን ገልጸው፥ ፕሮጀክቱ ከ40 በላይ እህቶችን ሮም ወደሚገኘው የጽህፈት ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤት በማምጣት የሥራ ላይ ሥልጠና እንዲወስዱ፣ እንዲሁም በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች የተለያዩ ስልጠናዎች ማቅረቡን ገልጸዋል።

ተግባቦት ወይም ኮሚዩኒኬሽን ኅብረትን የማጠናከሪያ እና ወንጌልን የማሰራጫ መንገድ እንደሆነ ጠቁመው፥ እህቶች በሁሉም ሃገራት ውስጥ የሚገኙ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ እና ይህ ፕሮጀክት እህቶች ጥሩ ጥሩ ወንጌላውያን እንዲሆኑ ብሎም፥ ለሚያገለግሉት ሰዎች ምሥራቹን የሚያደርሱ ሰዎች እንዲሆኑ ክህሎቱ እንዲኖራቸው ማድረጉን አብራርተዋል።

ሲስተር ዋካሂዩ የጴንጠቆስጤ ፕሮጀክት ላይ የተሳተፉ የካቶሊክ እህቶች ስልጠናውን ከጨረሱ በኋላ ወደ አገራቸው ወይም ተልዕኮዋቸው መመለሳቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ‘የተስፋ ታሪኮችን፣ የፍቅር ታሪኮችን እና በዳርቻ ላይ የሚኖሩ እህቶችን ህይወት የሚያካፍሉ ታሪኮችን’ ለመፃፍ እንደ ዩክሬን፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ሱዳን ወይም ማይናማር ያሉ በጦርነት በተከሰተባቸው ቦታዎች ጭምር ለአገልግሎት እንደሚሰማሩ ገልጸዋል።

ሲስተር ዋካሂዩ በመጨረሻም “በእነዚህ አከባቢዎች የእህቶች መገኘት ለማገልገል ብቻ ሳይሆን ለማበረታታት እና ተስፋ ለመስጠት ብሎም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስፍራው የመገኘት ተምሳሌት" ሆነው ጭምር እንደሆነ በማስታወስ አጠቃለዋል።

09 Oct 2025, 16:06