የማር ቶማ ቤተ ክርስቲያን ታድሶ ክፍት በተደረገበት ወቅት የማር ቶማ ቤተ ክርስቲያን ታድሶ ክፍት በተደረገበት ወቅት  

ከ8 ዓመታት በኋላ በሞሱል የሚገኙ ሁለት ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት በራቸው መከፈቱ ተነገረ

በሰሜናዊ ኢራቅ በምትገኘው ጥንታዊቷ ከተማ ሞሱል ፖለቲከኞች፣ ካህናት፣ እና የምዕመናን አባላት እስላማዊ መንግስት ተብሎ በሚጠራው የአይ ኤስ አስተዳደር የወደሙ የማር ቶማ እና የአል-ታሂራ አብያተ ክርስቲያናትን እንደገና ታድሰው በተከፈቱበት መርሃ ግብር ላይ መሰባሰባቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. በ 2014 ዓ.ም. አይ.ኤስ ሰሜናዊውን የኢራቅ ክልል ተቆጣጥሮ ስልጣኑን በያዘበት ወቅት በጥንቷ የነነዌ ከተማ ፍርስራሽ ላይ በተገነባችው እና የኢራቅ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው ሞሱል ውስጥ የነበሩ ሁለት ጥንታዊ አቢያተ ክርስቲያናትን ማውደሙ ይታወሳል።

በእነዚህ ጊዜያት በኢራቅ የሚገኙ የበርካታ አናሳ ቡድኖች ማለትም የክርስቲያኖች እና ያዚዲስቶች እንዲሁም የሌሎች ቡድኖች ንብረት የሆኑ ቅዱሳት ቦታዎች በእነዚህ ሃይላት ወድመው እና ረክሰው እንደነበሩ የሚታወቅ ሲሆን፥ በርካታ አማኞችም ከሃገራቸው ለመሰደድ መገደዳቸው ይታወሳል።

በመጨረሻም ከተማዋ ከአንድ ዓመት ከበባ በኋላ እ.አ.አ. በ 2017 ዓ.ም. ነፃ ስትወጣ ተሰደው የነበሩ ጥቂት ነዋሪዎች ወደቄያቸው ሲመለሱ ቤቶቻቸው እና ሃይማኖታዊ ሕንፃዎች ወድመው እንደጠበቋቸው ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

"የተስፋ ምልክት"
ከተማዋ ከነዚህ ሃይሎች ነፃ ከወጣች በኋላ በነበሩት ጊዜያት ከተለመደው የግንባታ ሂደት በተለየ ሁኔታ አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ ግንባታው ያላለቀ ረጅም እና እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት አድካሚ የሆነ የመልሶ ግንባታ ሂደት የነበር ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ ጥቅምት 5፣ ረቡዕ ዕለት በጥንታዊቷ ሞሱል ከተማ እምብርት ከውድመቱ በኋላ የታደሱ ሁለት ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ተገልጿል።

የኢራቅ ካልዳውያን ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑት ፓትርያርክ ሉዊ ራፋኤል ሳኮ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ‘እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መሰረቶቻቸው እና ታሪካቸው’ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ይህም በመሆኑ ምክንያት በእንክብካቤ መጠበቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በ 7 ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው የማር ቶማ የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውን የአል-ታሂራ የካልዳውያን ቤተክርስቲያን በአዲስ መልክ ታድሰው ሲከፈቱ የአካባቢው ፖለቲከኞች፣ ክርስቲያን ካህናት እና የምዕመናን አባላት በስፍራው ተገኝተው እንደነበር ተገልጿል።

የቀድሞው እስላማዊ መንግሥት እየተባለ በሚጠራው የአይ ኤስ ቡድን እነዚህን አቢያተ ክርስቲያናት እንደ እስር ቤት ይገለገልበት እንደነበር የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ‘የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት በር’ ተብሎ የሚታወቀውን እና በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአካባቢው ከነበረው እምነበረድ ተቀርፆ የተገነባውን ጥንታዊ የመግቢያ ግንብ ማፍረሳቸው ተገልጿል።

የ27 ዓመቱ ፋዲ የመግቢያ በሩን እድሳት ከሰራው የፍራንኮ-ኢራቂ ቡድን አንዱ ሲሆን፥ የሞሱል ክርስቲያን እና ነዋሪ የሆነው ፋዲ በፕሮጀክቱ ላይ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ለሦስት ዓመታት ያክል ሥልጠና መውሰዱን ገልጿል።

“አብያተ ክርስቲያናቱ እንደገና መከፈታቸው የተስፋ ምልክት ነው” ሲል ለቫቲካን ዜና የተናገረው ፋዲ፥ ይህ ክስተት በውጭ አገር የሚኖሩ ክርስቲያኖች በአሁን ወቅት የተሻለ ነገር እንዳለ እና ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉ ያሳያል በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።

እድሳት
የማር ቶማ ቤተ ክርስቲያን ባለፈው ሳምንት በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ዳግም ተቀድሶ ክፍት መደረጉ የተነገረ ሲሆን፥ የአል-ታሂራ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ለሐሙስ ዕለት ቀጠሮ መያዙ ተገልጿል።

በሌላ መልኩ አሁን የተደረጉት የማስጀመሪያ መርሃ ግብሮች የአብያተ ክርስቲያናት በሮች በይፋ ለሞሱል ህዝብ መከፈታቸውን እና እ.አ.አ. በ 2022 የተጀመረውን የተሃድሶ ፕሮጀክት ማብቃቱን የሚያሳይ ዓለማዊ መርሃ ግብር እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወተው በዓለም ዙሪያ ያሉ ባህላዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ እና ለማደስ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመው ‘አሊፍ’ (ALIPH) የተሰኘ ተቋም መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ አሊፍ የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት እድሳት ያከናወነው በዋነኛነት ትኩረቱን በመካከለኛው ምስራቅ ያሉትን ክርስቲያኖች በማገልገል ላይ ካደረገው የፈረንሳዩ ካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት ‘ሎውቭር ዲ ኦሪየንት’ ጋር በመተባበር እንደሆነ ተነግሯል።

“ዛሬ ለሞሱል ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነዋሪዎቿ ታላቅ በዓል ነው” ያሉት የሎውቭር ዲ ኦሪየንት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሁጉስ ደ ዎይሌሞንት፥ በዚህ ስፍራ ክርስቲያናዊ አምልኮ እንደገና እንደሚጀመር ገልጸው፥ የሆነ ወቅት ላይ ድምፃቸው በጣም የታወቀ የሞሱል ከተማ መለያ የነበሩት የቤተክርስቲያኑ ደወሎች እንደገና ድምጽ ማሰማታቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።

17 Oct 2025, 13:30