ፈልግ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምዕመናን በጎማ በሚገኘው የኖትሬ ዳም ዲ አፍሪክ ቤተክርስቲያን አብረው ሲጸልዩ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምዕመናን በጎማ በሚገኘው የኖትሬ ዳም ዲ አፍሪክ ቤተክርስቲያን አብረው ሲጸልዩ   (AFP or licensors)

የአሜሪካ ብፁአን ጳጳሳት ከአፍሪካ ቤተክርስቲያን ጋር ያላቸውን ጠንካራ አጋርነት በድጋሚ ገለፁ

የዩናይትድ ስቴትስ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁአን ጳጳሳት ከአፍሪካ አህጉር ብፁአን ጳጳሳት እና ምዕመናን ጋር ያላቸውን ጠንካራ አጋርነት በማደስ የመንግስት ባለስልጣናት እና መላው ህዝብ ሰላም፣ ፍትህ እና ደህንነትን ለማምጣት ተባብረው መስራት እንዲችሉ ጸሎት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአህጉሪቱ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባሉ የተለያዩ ግጭቶች መካከል ለሰው ልጅ ህይወት እና ክብር ጥልቅ ምስክርነት ለዓለም እየሰጡ ለሚገኙት ለአፍሪካ ብፁአን ጳጳሳት እና ምዕመናን ያለንን አጋርነት በድጋሚ እንገልፃለን ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ብፁአን ጳጳሳት፥ ለአህጉሪቱ ቤተክርስቲያን የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በአሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁአን ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) የዓለም አቀፍ ፍትህ እና ሰላም ኮሚቴ ሊቀ መንበር ብፁእ አቡነ ኤልያስ ዛይዳን ይህንኑ ስሜት የአሜሪካ ጳጳሳትን ወክለው የገለጹ ሲሆን፥ ብፁእ አቡነ ዛይዳን ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ በአፍሪካ አህጉር የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸውና ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

አብዛኛው የአፍሪካ ህዝብ በግጭት፣ በሀይማኖት እና በጎሳ ስደት፣ በኢኮኖሚ ችግር እና በአካባቢያዊ ችግሮች ምክንያት እንደሚሰደድ በመግለጫው የገለጹት ጳጳሱ፥ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በኢትዮጵያ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በናይጄሪያ እና በሳህል ክልል የተከሰቱት ግጭቶች እና ሰብአዊ ቀውሶች በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን እየቀጠፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የሁሉም እምነት ተከታዮች በጅምላ ግድያና አፈና እንዲሁም በግዳጅ መፈናቀል እየደረሰባቸው መሆኑን የጠቆሙት ብፁእ አቡነ ዛይዳን፥ በተለይ በቅርብ ሳምንታት እና ወራት ውስጥ በናይጄሪያዋ ሚድል ቤልት እና በሰሜናዊ ክልሎች እንዲሁም በምስራቅ ኮንጎ የተጨፈጨፉትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያን ሲቪሎችን አስታውሰዋል።

ብፁእ አቡነ ዛይዳን በማከልም በአህጉሪቱ የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናት እና የሁሉም እምነት ተከታዮች ለአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ፍትህ እና ደህንነት ሲሉ አብረው እንዲሰሩ የዩናይትድ ስቴትስ ብፁአን ጳጳሳት ጸሎት እንደሚያደርጉ ብሎም ለአህጉሪቱ የሚያደርጉትን ይሄንን ጸሎት ሁሉም ሰው እንዲቀላቀል ጋብዘዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ብፁአን ጳጳሳት የአሜሪካ መንግስት እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሰብአዊ እርዳታ ተጨባጭ አጋርነታቸውን የማሳየት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያላቸውን እምነት አረጋግጠው፥ የአሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁአን ጳጳሳት ጉባኤ በ 2016 ዓ.ም. በአህጉሪቱ ላሉ የካቶሊክ ድርጅቶች በ32 ሀገራት 96 የሃዋሪያዊ ሥራ ፕሮጄክቶችን ለመደገፍ 2.6 ሚሊዮን ዶላር የሚሰጠውን “በአፍሪካ ለሚገኙ ቤተክርስቲያን የአጋርነት ፈንድ” የተሰኘ ዓመታዊ ዘመቻ እያካሄደ እንደሚገኝ ተነግሯል።

የዩናይትድ ስቴትስ ጳጳሳት ይህ የአብሮነት ፈንድ የአሜሪካ ካቶሊኮች በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ጋር ያላቸውን የአንድነት መንፈስ እንዲገልጹ ዕድል እንደሚሰጥ እምነቱ እንዳላቸው የገለጹት ብፁእ አቡነ ዛይዳን በመጨረሻም፥ የሰላም ንግሥት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በአመጽ እና በግጭት የተጎዱትን ሁሉ እንድታጽናና፣ እንዲሁም በማኅበረሰባቸው እና በአገሮቻቸው መካከል ሰላምን ማስፈን እንዲችሉ ብርታቱን እንድትሰጣቸው ጸሎት እንደሚያደርጉ በመግለጽ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እንዳሉት እያንዳንዱ ማኅበረሰብ አንድ ሰው በውይይት ጠላትነትን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል የሚማርበት፣ ፍትህ የሚተገበርበት እና ይቅርታ የሚከበርበት ‘የሰላም ምንጭ’ እንዲሆን በመጸለይ መግለጫውን አጠቃለዋል።

26 Sep 2025, 15:38