ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በማርያም አይን ማየት ሰዎች እና ባህሎች በሰላም እንዲራመዱ ይረዳል አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
“የእግዚአብሔርን እና የታሪክን ምሥጢር በማርያም ውስጣዊ እይታ ማሰላሰላችን አንዳቸውም ቢሆኑ ጠቃሚ እና ቁጣን የሚያበርዱ ቃል ሊያቀርቡ ከማይችሉት የተዛባ ፕሮፓጋንዳ፣ ርዕዮተ ዓለም እና መርዛማ መረጃ ይጠብቀናል” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የማርያም እይታ ሰዎች፣ ብሔሮች እና ባሕሎች በሰላም አብረው እንዲሄዱ የሚያስችል ብቸኛው እና እውነተኛ መንገድ ለሆነው ለመለኮታዊ ጸጋ ያዘጋጀናል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በ 26ኛው ዓለም አቀፍ የሥነ ማሪያም አስተምህሮ (ማሪዮሎጂ) ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የእግዚአብሔርን ቃል ማዳመጥ ቤተክርስቲያንን ለሲኖዶሳዊነት እንዴት እንደሚከፍት በአጽንዖት በመግለጽ የጉባኤውን ቁልፍ መሪ ሃሳቦች እና ውጤቶች በመዳሰስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከነሃሴ 28 እስከ ጳጉሜ 1፣ ለአራት ተከታታይ ቀናት ሮም በሚገኘው የቅዱስ አንቶኒ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ ውስጥ የተካሄደው ይህ ጉባኤ የተዘጋጀው በጳጳሳዊ ዓለም አቀፍ የማሪያም አስተምህሮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ጉባኤው በአራት ቀናት ቆይታው ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ወደ 600 የሚጠጉ የሥነ ማሪያም አስተምህሮ ወይም የማሪዮሎጂ ሊቃውንት የጉባኤው ጭብጥ በሆነው “ኢዩቤልዩ እና ሲኖዶሳዊነት፡ የእመቤታችን ቅድስት ማሪያም ፊት እና ልምምድ ያለባት ቤተ ክርስቲያን” በሚለው ዙሪያ ሰፋፊ ምርምሮችን ማድረጋቸው ተገልጿል።
ሁለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምድቦች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የኮንግረሱ ርዕስ ራሱ የጌታን እናት ጥሪ እና ተልእኮ የሚገልጹ ሁለት “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምድቦች” የሆኑትን ኢዩቤልዩ እና ሲኖዶሳዊነት እንደሚያንጸባርቅ ጠቅሰው፥ በእሷ ውስጥ “የቤተክርስቲያኗን ጥሪ እራሱ ማንበብ እንችላለን” ብለዋል።
ይህም በመሆኑ እመቤታችን ድንግል ማርያም ለቤተክርስቲያን አርአያ ትሆናለች ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፥ “የቤተ ክርስቲያን እናት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ቅዱሳን ሰዎች መሆን የምንችልበትን መንገድ ታስተምረናለች” በማለት አብራርተዋል።
ከዚህ ተምሳሌትነት በመነሳት፥ የጳጳሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሙ አስፈላጊነት እራሱ በእጅጉ እንደሚነሳ አስታውሰው፥ ይህም “ቤተክርስቲያኑ ሁል ጊዜ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ገጽታ እና የተግባር መንገድ እንዳላት ያስታውሰናል” ብለዋል።
የ “ኢዮቤልዩ ሴት”
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በማከልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “የኢዩቤልዩ ሴት” መሆኗን ጠቅሰው፥ ምክንያቱም ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ከማዳመጥ እንደገና ትጀምራለች ያሉ ሲሆን፥ ይህንንም የምታደርገው ‘10ኛው የኑዛዜዎች መጽሃፍ’ በሚለው የቅዱስ አጎስጢኖስ መጽሃፍ ላይ በተገለጸው አመለካከት መሰረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም እራሷ የምትፈልገውን መልስ በመጠበቅ ሳይሆን ከእግዚአብሔር የምትሰማውን በመሻት እንደሆነ አስታውሰዋል።
እመቤታችን ድንግል ማርያም የምስራቹን መልዕክት በሰማች ጊዜ “ይህ እንዴት ይሆናል?” ብላ እንዳለችው፣ ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ወይም አስቸጋሪ እና ፍፃሜ ያላገኙ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ፈጽሞ ልትታክት አይገባም ብለዋል።
“ሲኖዶሳዊ ሴት”
ከዚህም ባለፈ ማርያም “ሲኖዶሳዊት ሴት” ናት ያሉት ብጹዕነታቸው፥ ምክንያቱም ደግሞ “በምሉእነት እና በእናትነት ስሜት በመንፈስ ቅዱስ ተግባር ውስጥ በመሳተፏ እንደሆነ ገልጸው፥ መንፈሱ በጋራ አለመተማመንም ይሁን ግልጽ በሆነ ጠላትነት በአንድ ወቅት የተከፋፈሉትን እንደ ወንድም እና እህት አብረው እንዲጓዙ ሁልጊዜ ጥሪ ያደርጋል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በማከልም ማርያም “ፍጹም የመንፈስ ቅዱስ ተባባሪ ናት” ያሉ ሲሆን፥ በሮችን መክፈት፣ ድልድይ መስራት፣ ግድግዳዎችን ማፍረስ እና የሰው ልጅ በልዩነት ውስጥ በሰላም እና በስምምነት እንዲኖር መርዳት በጭራሽ አታቋርጥም በማለት በአጽንዖት ገልጸዋል።
የማሪያም ገጽታ ያላት ቤተክርስቲያን
ከእነዚህ ከሁለቱ ባህሪያት ማለትም ከኢዩቤልዩ እና ሲኖዶሳዊነት የማሪያም ልብ ያላት ቤተክርስቲያን ተልእኮ ይፈሳል ያሉት ብጹእነታቸው፥ እንዲህ ያለች ቤተ ክርስቲያን ምክንያትና ስሜትን፣ ሥጋንና ነፍስን፣ ዓለም አቀፋዊና አከባቢያዊን፣ ግለሰብንና ማኅበረሰብን፣ ሰብዓዊነትን እና ዓለማዊነትን በማዋሃድ የእምነትን እውነተኛ ተዋረድ ያለማቋረጥ ይገነዘባል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው በማከልም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቅድስና እና ልምምድ የቤተክርስቲያኗን የበጎ አድራጎት ተልእኮ ሁሉንም የሰው ልጅ ህይወት፣ በተለይም የድሆችን እና የተገለሉትን በቁም ነገር በመውሰድ ወደ ተጨባጭ እውነታ እንደሚያመጣ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ማሪያም፡ ለባህላዊ ውይይት መንገድ ናት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም ጉባኤውን ወደ ጸሎተ ማሪያም የአምልኮ ጊዜ ከመምራታቸው በፊት ጳጳሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሙ የኢየሱስ ክርስቶስን እናት ምስል እና መልዕክትን በባህሎች መካከል የመገናኘት እና የመወያያ መንገድ አድርጎ በማቅረብ ስላበረከተው ጠቃሚ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በማመስገን አጠቃለዋል።