ፈልግ

ፖላንድ፣ ካሊኖውካ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ መስቀል ፖላንድ፣ ካሊኖውካ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ መስቀል  

ፖላንድ ‘ኤሴ ሆሞ’ የተሰኘ 5ኛውን መንፈሳዊ ቃል ኪዳን ያላቸው ወጣቶች ጉባኤ ማዘጋጀቷ ተነገረ

በፖላንድ፣ ሊቼን ከተማ ውስጥ ለአራት ተከታታይ ቀናት የተከበረው አምስተኛው መንፈሳዊ ቃል ኪዳን ያላቸው ወይም የገቡ ወጣቶች ጉባኤ በዋናነት የኅብረት እና የሰው ልጅ ክርስቶስን የመምሰል ልምድ እንደገና የሚያገኝበት የወጣቶች ክብረ በዓል እንደሆነ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሊቸን የተካሄደው ይህ የአራት ቀናት የወጣቶች ጉባኤ ከ500 በላይ የሚሆኑ መንፈሳዊ ቃል ኪዳን የገቡ ወይም ያላቸው ወጣት ወንዶችን እና ሴቶችን ከመላው ፖላንድ አንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን፥ በእነዚህም ቀናት የተለያዩ የጸሎት መርሃግብሮች፣ ጉባኤዎች እና ምስክርነቶች እንደቀረቡበት አዘጋጆቹ አመላክተዋል።

ከጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ አንዷ የሆኑት ሲስተር ማሪያና ታርኮውስካ ለቫቲካን ሬድዮ እንደተናገሩት ከተሳታፊዎቹ አንፃር፣ በጣም አስፈላጊው ገጽታ መንፈሳዊ ቃል ኪዳን ያላቸው ሰዎች መካከል ያለው የማህበረሰቡ ልምድ እንደነበር ገልጸው፥ በአከባቢው ምንም እንኳን የመንፈሳዊ ጥሪ ችግር ያለ ቢመስልም እና አንዳንድ ተቋማት ጥቂት አዳዲስ አባላት ቢኖራቸውም በፖላንድ የምትገኘውን ቤተክርስቲያን በስፋት ሲመለከቱ ሌሎች ወጣቶችም ክርስቶስን በተቀደሰ ሕይወት ለመከተል የሚፈልጉ በርካታ ወጣቶች እንዳሉ ይገነዘባሉ ሲሉ አስረድተዋል።

እህት ማሪያና አክለውም የህብረት ስሜት የሚመጣው ሁለቱንም የደስታ እና የችግር ወቅቶችን በጋራ በመካፈል እንደሆነ በአጽንዖት ገልጸው፥ በዚህ ዝግጅት ወጣቶቹ የህይወት ልምዳቸው በጣም ተመሳሳይ መሆኑን እንደተገነዘቡ እና ይህም መሆኑ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ፥ ምክንያቱም አንዳንድ የህይወት ሸክሞችን ብቻቸውን እንደማይሸከሙ እና ሌሎች ብዙ ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ እየተጓዙ እንደሆነ ስለሚያሳይ ነው በማለት አስረድተዋል።

የታደሰ የሰብዓዊነት ራእይ

‘ኤሴ ሆሞ’ የተሰኘው የጉባኤው ጭብጥ ሁለት እውነታዎችን ለማንፀባረቅ ቦታ እንደከፈተ የገለጹት ሲስተር ማሪያና፥ በመጀመሪያ፣ ፍጹም ሰው የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማሰላሰል እድል የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸው፥ በአባ ቶማስ ኖዋክ የተመራው የጉባኤው የመክፈቻ ርዕሰ ጉዳይም ይሄንኑ እንደሚያንጸባርቅ እና ይሄም የራሳችንን ሰብአዊነት እንድናሰላስል መነሻ ይሆነናል በማለት ገልጸዋል።

የጉባኤው አስተባባሪ የሆኑት እህት ማሪያና የተቀደሱ ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ እራሱ የሰው ልጅ የሚቀረፅበት እና ጥልቅ የሆነበት ቦታ መሆኑን አስምረውበት፥ “ኢየሱስን በመከተል እና እሱን በመምሰል እናድጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ሰብዓዊነት የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ይገለፃል
የጉባኤው ፍሬዎች በእያንዳንዱ ተሳታፊ በግል መዋሃድ እንዳለባቸው የገለጹት እህት ማሪያና፥ በስብዕና ስለምንለያይ እና በተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥ ስለምንኖር ሁሉም ሰው የራሱን መንገድ ማግኘት እንዳለበት ከገለጹ በኋላ፥ ከሁሉም በላይ ስለራስ እውነቱን ለማወቅ ያለማቋረጥ መፈለግ አስፈላጊ መሆኑ እና ይህም መሠረታዊ እንደሆነ ጠቅሰው፥ በእምነት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት የበለጠ ትክክለኛ ለመሆን ከጉባኤው የተገኙ ልምዶችን ወደ ዕለታዊ ህይወት ለመተርጎም ተጨባጭ እርምጃዎች ናቸው በማለት አስረድተዋል።

ከግማሽ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች
የዘንድሮው መንፈሳዊ ቃል ኪዳን የገቡ ወይም ያላቸው ወጣቶች  ጉባኤ 97 ወንዶችን ከ18 ተቋማት እንዲሁም ከዓለማዊ ተቋማት እና ገዳማዊያት ደናግላን አባላትን ጨምሮ ከ62 ጉባኤዎች የተውጣጡ 442 ሴት ገዳማዊያትን ያካተተ፥ በአጠቃላይ 539 ተሳታፊዎችን በአንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን፥ የሚቀጥለው ጉባኤ የሚካሄድበትን ቀን እና ቦታ የመወሰን ሥራ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጀመር ተገልጿል።

24 Sep 2025, 13:25