ለነፍሳችን ደኀንነት እናስብ
የነፍሳችን ደኀንነት ከሁሉ የላቀና አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ነው። ለምድራዊ ጉዳይ ብለን መንፈሳዊ ጉዳያችንን ችላ ልንለው አንችልም። ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?" (ማቴ 16፣26-27) እያለ ስለ ነፍሳችን ደህንነት እንድንጠነቀቅ በመንቀጥቀጥ ያስተምረናል። ቅዱስ ጳውሎስም ለፊሊጵስዩስ ሰዎች ሲጽፍ «በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ (ፊል 2፣ 12) ይላቸዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ቅዱስ አምብሮስዮስም «አእምሮ ያለህ ከሆንም የነፍስህ ደኀንነት ከሁሉ የበለጠና የላቀ ግዴታ እንደሆነ አስብ ይለናል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ (ልሳነ) ወርቅ ደግሞ "ሰይጣን ነፍሳችንን ለማጥፋት ብዙ ሲተጋና ነቅቶ ሲዋጋ እኛ ግን ስለ ነፍሳችን ደህንነት እንደዚህ ያለ ስንፍና ማሳየት ትልቅ ሞኝነት ነው" እያለ ይወቅሰናል። የነፍሳችን ደኀንነት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ደህና አድርገን ብንገነዘብ ኖሮ ችላ የማንለውና ጊዜ የማንሰጠው ዋናው ሐሳባችን አድርገን በተመለከትነው ነበር።
ኦቶነ የሚባለውን ንጉሥ አንድ ቀን ኒሎስ የሚባል አንድ ትልቅ ቅዱስ ሊጎበኘው ሄደ። ከእርሱ ጋር ረጅም ውይይት ካካሄደ በኃላ በመጨረሻ ሲሰናበተው የሰማው ንግግር ደስ ስላለው ገጸ በረከት ሊያደርግለት ፈለገ። ቅዱሱ ግን ስለመልካም ሐሳቡ እያመሰገነ የሚያስፈልገው ነገር እንዳልነበረና በድህነቱ ተደስቶ እንደሚኖር አስረዳው። ንጉሡ «የእኔን ስጦታ ካልፈለግህ ለአንተ የሚያስፈልግህንና ደስ የሚያሰኝህ ነገር ካለ ንገረኝ አደርግልሃለሁ አለው። እርሱ ደግሞ «ይህንንስ እሺ፣ ነገር ግን እኔን ሊያስደስተኝ የሚችል አንድ ነገር ብቻ አለና እንድትሰማን እለምንሃለው፣ ንጉሥ ሆይ! ዘለዓለማዊ ደኀንነትን በሚመለከት ትልቅ የነፍስህ ጉዳይ በማሰብ ነፍስህን አድን። ምንም እንኳ ንጉስ ብትሆን እንደሌላው ተራ ሰው ሞት አይቀርልህም፣ ከሞትክ በኃላ ደግሞ በሕይወትህ ዘመን ያደረግኽው ደግና መጥፎ ሥራህ በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ ይቀርባል፣ የዚህ ጥብቅ ቁጥጥርና ሀሳብህን ለእግዚአብሔር ታቀርባለህ እያለ ስለ ዘለዓለማዊ ደኀንነቱ እንዲያስብ አስጠነቀቀው፣ አደራም አለው።
ንጉሡም ጠቃሚ ምክሩን በደስታ ተቀብሎ ፈጸመው። እኛም ይህንን አደራና ምክር ተቀብለን ነፍሳችንን እናድን፣ እርስዋ የአምላክ ስጦታ ናት። በጸጋዎቹ የተሸለመችና ያጌጠችም ናት። እግዚአብሔር ነፍሳችንን በጣም ይወዳታል። ስለዚህም ከሰይጣን ባርነትና ቀንበር ሊያድናት ፈልጐ አንዲያ ልጁን ለሞት አሳልፎ ሰጠ። እንዲሁም በምድር ዘወትር እየጠበቃት እንዲኖር ብሎ ቅዱስ ቁርባንን ሠራላት። ነፍሳችን አንዲት ናት፣ እርስዋም ከጠፋች ለዘለዓለሙ ጠፋች ማለት ነው፣ ለጠፋች ነፍስ ደግሞ መድኃኒት የለም ተፈልጐም አይገኝም።
የሮም ርእሰ ሊቃነ ጰጳሳት በነዲክቶስ 12ኛ "ሁለት ነፍሶች ቢኖሩኝ ኖሮ አንዷን ለእኔ አስቀርቼ ሁለተኛይቱን ስላንተ አጠፋት ነበር ነገር ግን አንዲት ነፍስ ብቻ ስላለችኝ አንተን ለማስደሰት ብዬ ኃጢአት ሠርቼ ላጠፋት አልፈልግም" እያሉ የፈረንሣይ ንጉሥ ለነበረው ለፊሊጶስ 6ኛ መለሱለት"።
አንድ ዓይናችን፣ ጆሮአችን፣ አጃችንና እግራችን ቢጐድልብን ሌላው ይቀረናል። ነፍስ ግን አንዲት ብቻ ናት፣ መተኪያ የሌላትና ከጠፋች ልትመለስ የማትችል ናት። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ዋጋ ሊከፍል ይችላል" (ማቴ. 16፣ 26) እንዳለ እናስተውል።
ቅዱስ ቶማስ ሙር የሚባል አንድ እንግሊዛዊ ሄንሪኮርስ 8ኛ (Henry Viii) መጥፎ ሥራ እንዲሠራ አዞት ትዕዛዙን ተቃውሞ እምቢ ስላለ ሞት ፈረደበት። ወዳጆች በተለይም ሚስቱ ስለ እርስዋና ስለ ልጆቹ ብሎ ሕይወቱን እንዲያድንና የንጉሱን ትዕዛዝ እንዲፈጽም ለመኑት። እርሱ ግን በአምላክ ፍቅር የተቃጠለ ስለነበረ "ለንጉሱ ብታዘዝ ስንት ዓመት የምኖር ይመስልሻል" ሲል ጠየቃት። እርሷንም ከሃያ ዓመት የበለጠ እንደሚኖር ብትነግረው "አንቺ ሞኝ ለጥቂት ዓመታት ስል ለዘለዓለም ነፍሴን ላጥፋት? ለሃያ ዓመታት ብዬ ነፍሴን ልሸጣትን" እያለ ገሰጻት። ለዘለዓለም እንዳይኰነን ብሎ ሃያ ዓመታትን ናቀ።
እንደ ቅዱስ ቶማስ ሙር ለነፍሳችን ደህንነት ደህና አድርገን እናስብ፣ ዋና ሐሳባችንና ጥረታችን አንዲቷን ነፍሳችንን ለማዳን ይሁን። ሰይጣን ዓለምና ሥጋችን በአንድነት ሆነው ለሥጋዊ ነገር ብቻ እንድናስብ፣ ነፍሳችንን ግን እንድንረሳ ሲፈትኑን ለዚህ የማይረባና ለማይጠቅም ኃላፊ ለሆነ ቁሳቁስ ነገር ስል ለዘለዓለም ልኰነን? ለዘለዓለም ነፍሴን ወደ ገሃነመ እሳት ላውርዳት? እያልን በርትተን እምቢ እንበለው ለነፍሳችን ደህንነት ብቻ እናስብ።